የካቲት 2010 ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ህዝቦች የህወሓት/ኢህአዴግን የግፍ አገዛዝ በመቃወም የሚያካሂዱት ትግል ባሁኑ ሰዓት ከፍተኛ ደራጃ ላይ ደርሷል። ይህ ለዴሞክራሲና ለአንድነት የሚደረግ ህዝባዊ ትግል በተለይም ከ 3 ዓመት ጀምሮ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በተጠናከረ መልክ እየተካሄደ ይገኛል። በዚህ የህዝብ ትግል የተዳከመው አምባገነናዊ አገዛዝ ተገዶ የተወሰኑ የፖለቲካ እስረኞችን ቢፈታም ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን አሰፋለሁ ያለውን ግን ተራ ማጭበርበር እንደሆነ በግልጽ እየታየ ነው። ይባስ ብሎም የህዝቡን ትግል ለመጨፍለቅ የአስቸዃይ ጊዜ አዋጅ ኣውጇል። አገዛዙ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲያውጅ ለመጀመሪያ ግዜ ባይሆንም፣ ያሁኑ ግን በኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ የታወጀ የጦርነት አዋጅ ነው።
አዋጁ መሰረታዊ የሆኑ ሰብአዊ መብቶችን የሚከለክልና ለወታደሩ በየትኛው ቦታና ጊዜ ኢትዮጵያውያንን የመግደልና የማሰር የማሰቃየት ትእዛዝ የሰጠ ነው። ይህ የህወሓት/ኢህአዴግ ወንጀል ባሁኑ ሰዓት በኦሮሞ ህዝባችን ላይ እየተፈጸመ ይገኛል። ትግሉ እየተፋፈመ ሲሄድም ወንጀለኞቹ የህወሓት/ኢህአዴግ ገዢዎች በተቀረው ህዝባችን ላይ የጀመሩትን ፍጅት መቀጠላቸው የማይቀር ነው።
ኢተውመ አገዛዙ የጦርነት አዋጅ አውጆ አገሪቷን ወደ አጠቃላይ ቀውስ እያስገባት መሆኑ ስለተገነዘብን ከተለያዩ ታዋቂ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ከጀርመን፣ ቤልጀም፣ ነዘርላንድ፣ ስውዘርላንድ፣ ዩኬ፣ አሜሪካና ካናዳ በቴለ ኮንፈረንስ ተገናኝተን በጋራ በጉዳዩ መክረን አገራችን ከተጋረጠባት አደጋ በተጠናከረ ትግልና አንድነት አድነን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ምን ማድረግ አለብን የሚለውን ኣብይ ጉዳይ አስመልክቶ ቀጥሎ የተቀመጠውን ጥሪ ለኢትዮጵያዊያን በሙሉ ያቀርባል።
ውድ የኢትዮጵያ ህዝቦች ሆይ፣
ህወሓት/ኢህአዴግለ27 ዓመታት በመካከላችን የጥላቻ መርዝ ሲዘራ ቆይቷል። የህወሓት መሪዎች በቀደዱልን የጥፋት ቦይ በመግባት እርስ በርስ እንዳንፋጅና ጥንታዊትና ታሪካዊት የሆነችው የጋራ አገራችን ወደመበታተን እንዳታመራ ባስቸኳይ ትግላችን ማስተባበርና አንድነታችን ማጠናከር ይኖርብናል። ኢትዮጵያን ከተደቀነባት አደጋ ለማዳን በአገር ቤትም ይሁን በውጭ ሀገራት ያላችሁ ሃቀኛ የተቃዋሚ ፓርቲዎችና የሲቪል ማህበራት ትግሉን የማስተባበርና የመምራት ታሪካዊ ሃላፊነት እንዳላችሁ ለማሳሰብ እንወዳለን። አባቶቻችንና እናቶቻችን የጋራ አገራቸውን ከባዕድ ጠላቶች በጋራ ተከላክለው ለኛ እንዳስረከቡን ሁሉ ዛሬ ከውስጧ የተፈጠሩ የውስጥ ጠላቶቿ እንዳይበታትኗት በጋራ መመከት ከምንም በላይ ቅድሚ ያሊሰጠው የሚገባ የጋራ ዜግነታዊ ግዴታችን ስለሆነ፣ አገራችንን ለማዳን በጋራ እንረባረብ እንላለን።
ውድ በአገርቤት በብሄርና በሌላ መልክ ተደራጅታችሁ አገዛዙን በመታገል ላይ ያላችሁ ወገኖቻችን፣
በየአከባቢያችሁ በብሄር ሆነ በሌላ መልክ ተደራረጅታችሁ እየታገላችሁ ያላችሁ ወገኖች ትግላቹ አገዛዙ ላይ ብቻ ያተኮረ እንዲሆን፣ በየክልሉ የሚኖሩ ከራሳችሁ ብሄር ውጭ የሆኑ ከአገዛዙ ጋር ትስስር የሌላቸው ንጹሃን የሌላ ብሄር ዜጎች እንደራሳችሁ ብሄር አባላት አይታችሁ ከማንኛውም ወገን በህይወታቸው ሆነ ንብረታቸው ላይ ሊሰነዘርባቸው ከሚችለው ጥቃት እንድትጠብቋቸው በታላቅትህትና እንጠይቃለን።
የትግራይ ህዝብንና ህወሓትን አንድ አድርጋችሁ በትግራይ ህዝብ ላይ ጥላቻ እየሰበካችሁ ያላችሁ ወገኖች፣ ህወሓት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ለሚፈጽመው ግፍ የትግራይ ህዝብ ተጠያቂ አይደለም። የትግራይ ህዝብ እንደ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ በህወሓት ኣገዛዝ ተጨቁኖ የሚሰቃይ ህዝብ ነው። ስለሆነም የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ ተቃዋሚ ነን እያላችሁ፣ ህወሓትና የትግራይ ህዝብን አንድ ላይ ጨፍልቃችሁ የምታዩና በትግራይ ህዝብ ላይ ጥላቻ እያሰራጫችሁ ያላችሁ ወገኖች በእጅ አዙር የህወሓት ስራ በመስራት እኩይ የህወሓት መሪዎች ዓላማ እያሳካችሁ መሆናችሁን አውቃችሁ ይህ ድርጊታችሁ እንድታቆሙና ትግላችሁን የመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ጠላት በሆነው በህወሓት/ኢህአዴግ ላይ ብቻ እንድታካሄዱ በጥብቅ እናሳስባችሁ አለን።
ውድ የትግራይ ህዝብ ሆይ፣
የህወሓት ባለስልጣኖች በስምህና ውድ ህይወታቸውን በከፈሉት ሰማዕታት ልጆችህ ስም የሚነግዱት የግፍ አገዛዛቸውን ለማጠናከርና ለማራዘም ነው። ለዘመናት ተፋቅረህና ተከባብረህ አብረኸው ስትኖር ከነበረው ሌላው ኢትዮጵያዊ ወገንህ ጋር እንዳትቀራረብና አንድነት እንዳትፈጥር ጥላቻን ሰብከዋል ፣ አስፋፍተዋል። ይህንን እኩይ ተግባራቸውን በመገንዘብ ተደራጅተህ ትግልህን ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በማስተባበር ራስህንና ኢትዮጵያን ለማዳን በሚደረገው ትግል ጉልህ ሚና እንድትጫወት ጥሪያችንን እናቀርባለን።
የትግራይ ምሁራንና ወጣቶች ሆይ፣
በህወሓት አፈና ምክንያት ድምጹን ማሰማት ላልቻለው የትግራይ ህዝብ ድምጽ ማሰማት ያለባችሁ፣በህዝቡ ላይ በህወሓት እየደረሰ ያለውን አፈና ለሌላው ኢትዮጵያዊ ማሳወቅ ያለባችሁ እናንተ የትግራይ ምሁራን መሆን እየተገባችሁ እስከ ዛሬ በጣት ከሚቆጠሩት ጥቂቶች ውጭ ብዙዎቻችሁ ዝምታን መምረጣችሁ በታሪክ የሚያስወቅስ ትልቅ ስህተትነው።አገር ቀውስ ውስጥ ገብታ መስቀለኛ መንገድ ላይ በምትገኝበት ባሁኑ ወቅት ዝምታ መፍትሄ ስለማይሆን በተለይ እናንተ በነጻው ዓለም የምትኖሩ የትግራይ ምሁራን ዝምታን ሰብራችሁ ለድምጽ አልባው የታፈነ የትግራይ ህዝብ ድምጽ እንድትሆኑት፣በፈለጋችሁት መንገድ ተደራጅታችሁ አገዛዙን እንድትታገሉ፣ ጥሪያችንን እናቀርብላችሁአለን።
ኢትዮጵያበተባበረ የልጆቿ ትግል ከውስጥ ጠላቶቿ የተደገሰላት የመበታተን አደጋትድናለች!!!