መጋቢት 2018
ህወሃት ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የኢትዮጵያን ህዝብ ረግጦ የገዛበት ምክንያትና ስልት ህዝቡን በፍርሃት ሸብቦ መያዝ መቻሉ ነበር። ባልታጠቀ ህዝብ መሃል እስከ አፍንጫው ታጥቆ የህዝቡል ልጆች በጠራራ ፀህይ እየገደለ፣ አንድ ለአምስት አደራጅቶ ወንድም ወንድሙን፣ ወላጅ ልጁን ልጅም ወላጁን እንዳያምን አድርጎ፤ ኢኮኖሚውን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ ህዝቡን አቅም በማሳጣት፤ ተቃዋሚ እንዳይነሳ ብቅ ሲሉ እያዳፈናቸው፤ ጋዜጠኞች የህዝብ ድምፅ ሲሆኑ በማሰር፣ በማሰደድ አይነኬ፣ አይደፈሬ ሆኖ ቆይቷል።
አዎ አምባገነኖች ዘለዓለማዊ እንዳልሆኑ በዓለምም በእኛም ብዙ ተምረናል። ህወሃት ጉልምስናውን ጨርሶ አረጀ። እሱ ጎልምሶ ጭካኔውን ባካሄደበት አፈር ላይ እሱን የሚያጠፋ አዲስ ትውልድ እንደ እንጉዳይ ፈላ። ይህ ትውልድ እንደትናንቶቹ የወያኔ ተቀናቃኞች ወያኔ በሰለጠነበት ስልት ሊገጥመው አልፈለገም። እንደማይሰራ አውቋልና። አምባገነኖችን የሚያምበረክከው የተቀናጀ ህዝባዊ አምፅ መሆኑን በሚገባ ቀስ በቀስ እየተለማመደ ፍቱንነቱን አይቷል። መጀመርያ ፍርሃትን ሰብሮ ዳግም ላያጎበድድ መቁረጡን ባለፉት ሶስት ዓመታት አስመስክሯል።
መግደል እንደማያስፈራው፡ የገዳዮች እጅ እስኪዝል እየሞተ አመፁን ቀጥሏል።
መታሰር እንደማያስፈራው፡ የግፎች ሁሉ ግፍ እየተፈፀመበት በአደባባይ፣ በፍርድ ቤት እያጋለጠ እስር ቤቶች እስኪጠቡ ወደ እስር ተምሟል። ከእስር የተፈቱ ጀግኖችን መሪዎቼ ናቸው ብሎ አደባባይ ሞልቶ ተቀብሏቸዋል።
አስቸኳይ አዋጅ እንደማያስፈራው፡ የታወጀ እለት ጀምሮ እምቢታውን በፓርላማው ሳይቀር አሳይቷል። በግልፅም ውድቅ አድርጎታል።
መከፋፈል እንዳያስፈራው፡ ዘረኝነትን ለሰበኩት ወያኔዎች አስታቅፏቸው ለሁሉም ለሆነች ኢትዮጵያ እንደሚዋደቅ በአንድነት ተነስቶ አሳይቷቸዋል።
ህዝቡ ይህንን ትግል ከአጠቃላይ ዘላቂ ድል በመለስ እንደማያቆም በቃሉም እየተናገረ፣ በድርጊቱም እያሳየ ቢሆንም ማሰብ ለአቆሙ አምባገነኖች የሚገባቸው አልሆነም።
በድምፃችን ይሰማ የሙስሊሞች ሰላማዊ ትግል፣ በወልቃይቶች የማንነት ጥያቄ፣ በአዲስ አበባ ዙርያ የኦሮሞዎች መሬት ዘረፋ ይቁም ሰላማዊ ጥያቄ የተሰጠው መልስ ግድያ፣ እስራት፣ ድብደባ፣ መፈናቀልና ሥደት ሆኗል። በዚህ ሶስት ዓመት ብቻ ሺዎች በጥይት ተጨፍጭፈዋል እስከ ትናንቱ የሞያሌ ዘር የማጥፋት ወንጀል። ከሚሊዮን የሚበልጡ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። በመቶ ሺዎች ታስረዋል። ይህም ሆኖ በህዝቡ ልብ ፍርሃትን መልሶ ማስገባት አልተቻለም። አንዲያውም ህዝቡ አዳዲስና አምባገነን ስርዓቱን ለፍፃሜ የሚያቀርቡት ስልቶችን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል። ትግሉም የትንሽ አካባቢዎች መሆኑ እየቀረ አገራዊ መልክ ይዟል።
ቤት ዘግቶ መቀመጥ፡ በኦሮምያ፣ በአማራ፣ በአዲስ አበባ ዙርያና በጉራጌ በሚገባ ተከናውነዋል። በነዚህ አካባቢዎችና በሌሎችም በተቀናጀ ሁኔታ መከናወን ቀጣዩ እርምጃ መሆኑን ስናስብ ስርዓቱን እንደሚያንገዳግደው እሙን ነው።
ግብር አለመክፈል፡ በአዲስ አበባ፣ በኦሮምያ፣ በአማራ ነጋዴዎች ሲያምፁ ስርዓቱን ብርክ እንዳስያዙት አይተናል። ይህ ድርጊት ከፍ ብሎ በአገር አቀፍ ደረጃ ገበሬውንም አካትቶ መተግበር የሚቻል በመሆኑ ሲጀመር ስርዓቱ ሊቋቋመው እንደማይችል ግልፅ ነው።
ትናንት የተጀመረው የነዳጅ እቀባ፡ የስርዓቱን የደም ዝውውር እንደሚያቆም ግልፅ አድርጓል። ይህ አድማ በጥቂት ሰዎች በተቀናጀ መልክ መከናወን የሚችል ከመሆኑም በላይ በምንም ዓይነት ኃይል ማስቆም የማይቻል፣ ሁሉንም የስርዓቱን ነርቭ ይሚነካ ትግል ነው። በጎንደር መተማ መንገድ በተወሰኑ ነዳጅ ጫኝ ቦቲዎች ላይ በተወሰደ እርምጃ እንቅስቃሴውን ማስቆም እንዳስቻለ አስመስክሯል።
ትጥቅ ማስፈታት፡ ይህ በተለይ በአማራው አካባቢ ስርዓቱ ሊያከናውነው ያቀደውና እየሞከረ ያለው ተግባር ነው። መጀመርያ የአማራውን በመሳርያው ላይ ያለውን ስነልቦና ካለመገንዘብ ነው ብዬ ባላምንም ከወያኔ አጥፊ ትዕቢቶች አንዱ ነው እላለሁ። እንደህወሃት አማራውን ጠላቱ አድርጎ በፕሮግራሙ ይዞ የተነሳና ላለፉት አርባ ዓመታት በተለያየ ስልት ሊያዳክመውና ሊያጠፋው ለተነሳ ህዝብ ግቡ እንዳይደርስ ያደረገው ህዝቡ የታጠቀ መሆኑ ነው። ስለሆነም ትጥቅ ማስፈታቱ እንዳይሳካ ህዝቡ ራሱን በቡድን እንዲጠብቅ ማሳሰብ ያስፈልጋል። የኢጣልያ ወራሪ ኢትዮጵያን ቅኝ እንዳይገዛ በዱር በገደሉ እያራወጡ ነፃ ያወጡን አባቶቹ ያቆዩትን ራስንና አገርን የመከላከል ስነልቦና ከቶም የባንዳ ልጅ ወያኔ አይሰብረውም። እንደጌቶቹ መጥፊያው ይሆነዋል።
በወያኔ ንብረትና ተቋማት ላይ ማቀብ፡ ጫካ ሆነውና በስልጣን ተቀምጠው በዘረፉት ሃብት ህዝቡን ማደህየትና ራሳቸውን ማጎልበት የቻሉት ከዳር ዳር ባቋቋሟቸው የዘረፋ ተቋማት በመሆኑ ስርዓቱ ቀስ በቀስ እየደማ እንዲሞት ማዕቀብ በማድረግ ማሽመድመድ ያስፈልጋል። በነሱ የተመረቱትን ባለመጠቀም፣ ጥሬ ዕቃና ገበያ እንዳያገኙ በማድረግ፣ አሰራራቸውን በስውር በማሰናከል ከጥቅም ውጭ ማድረግ ይጠበቃል።
ወንጀለኞችንና ወንጀላቸውን መዝግቦ መያዝ፡ ለበርካታ ዓመታት በብዙ ኢትዮጵያውያን ላይ ግፍ ሲፈፀሙ ስርዓቱን ጋሻና መከታ ያደረጉ ግለሰቦች ሆነ ቡድኖች በህብረተሰቡ መካከል ይገኛሉ። ሰባዊ መብት ጥሶ በድርጊቱም መኩራራት ባህል ያደረጉ ግለሰቦች በድርጊታቸው ሊያፍሩበት ብሎም ሊጠየቁበት ስለሚገባ የሰሩት ወንጀል ጊዜ፣ ቦታና ሁኔታ ተምዝግቦ መያዝ፣ ለሰባዊ መብት ተሟጋቾች፣ ለመገናኛ ብዙሃን፣ ለአክቲቢስቶች ማሳወቅ ተገቢ ነው።
የአካባቢን ሰላም መጠበቅ፡ ስርዓቱ እየተፍረከረከ መንግስታዊ ተቋሙም እየተዳከመ ሲሄድ የስርዓቱ ደጋፊዎች ሆነ አጋጣሚውን መጠቀም የሚፈልጉ ወንጀለኞች ህብረተሰቡን ሊጎዱ ስለሚችሉ ሁሉም ዜጋ በመተባበር የሚኖርበትን አካባቢ ሰላም በማስጠበቁ ተግባር መሰማራት አለበት። ይህ ለኢትዮጵያ ህዝብ እንግዳ አይደለም። ጠላት አገራችንን ሲወርር አምስቱን ዓመት፣ የኃይለስላሴ መንግስት ሲወድቅ ለበርካታ ወራት ህዝቡ ራሱን በሰላም አስተዳድሯል። በተለይም ደርግ ሲወድቅ ከነፍስ ወከፍ እስከ ከባድ መሳርያ የታጠቀ ሰራዊት ሲበተን ከዘጠና ከመቶ በላይ አገሪቱ አስተዳደሯ ፈርሶ ያለምንም ችግር ህዝቡ ራሱን እያስተዳደረ ቆይቷል። በተለይ በቄሮ፣ ፋኖና በሌላም መልክ የተደራጀው ወጣት በሃላፊነት ስሜት የህዝቡን ሰላም የመጠጠበቅ ተልዕኮ ሊወጡ ይገባል።
ቸር እንሰንብት!!