ምሁራን/አክቲቪስቶች ኦሮምኛ በአማራ ክልል በግእዝ ፊደል /በግርማ ካሳ/

ምሁራን/አክቲቪስቶች ኦሮምኛ በአማራ ክልል በግእዝ ፊደል /በግርማ ካሳ/

ምሁራን/አክቲቪስቶች ኦሮምኛ በአማራ ክልል በግእዝ ፊደል እንደ ትምህርት እንዲሰጥ ጠየቁ።

“በባዕዳን ፊደል የሚጽፉ አፍሪካውያን፣ በአውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች ሲገዙ የነበሩና ራሳቸው የፈለሰፏቸው የፊደላት አማራጭ ያልነበራቸው ሕዝቦች ናቸው። እኛ በጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ደምና አጥንት ነፃነታችን ተከብሮልን የኖርንና አኩሪ ቅርስ የሆነ የራሳችን ፊደል ያለን ሕዝቦች ቅኝ እንደተገዙትና እንደተዋረዱት ያልታደሉ ሰዎች ልንሆን አይገባም።” ሲሉ ታዋቂ ምሁራን እና አክቲቪስቶች፣ አሮምኛ በአማራ ክልል በግእዝ ፊደል እንዲሰጥ የሚጠይቅ ጥናታዊ ሰነድ አዘጋጅተው ለአቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአማራ ክልል ፕሬዘዳንት ጽ/ቤት እንዳስገቡ የደረሰን መረጃ ያመለክታል። የምሁራኑን ደብዳቤ ከአባሪ ሰነዶች ጋር እንደሚከተለው አቅርበናል፡

ጉዳዩ — ኦሮምኛን በአማራው ክልል በግእዝ ስለማስተማር
ጥር 30 ቀን 2010 ዓ.ም.

ለተከበሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአማራው ክልላዊ መንግስት ፕሬዘዳንት

ክቡር ፕሬዘዳንት ሆይ፡-

የአማራ ክልል ከኦሮሚያ ቀጥሎ ብዙ ሕዝብ የሚኖርበት ስፋት ያለው ክልል ነው። ከአማራ ክልል ውጭ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ አማርኛ ተናጋሪዎች እንደሚኖሩት፣ የአማራ ክልልም የሌሎች ብሄረሰቦች አባላት በስፋት ይኖሩበታል። ከዚህም የተነሳ በአማራው ክልል ሆነ በተቀረው የአገራችን ግዛቶች የተለያዩ ቋንቋዎች ይነገራሉ።
አንዳንዶች ቋንቋን የማንነት ምልክት አድርገው የማየት ዝንባሌ አላቸው። ሆኖም ግን ቋንቋ በዋናነት የመግባቢያ መሳሪያ ነው። አንድ ሌላ ቋንቋ የምናውቅ ከሆነ፣ አስተማሪ ወይም ሐኪም ሆነን ወይም በተለያዩ ሌሎች ምክንያቶች ቋንቋው የሚነገርበት አካባቢ ከሕዝቡ ጋር በቀላሉ የመግባባት እድል ይኖረናል። ቋንቋ ማወቅ ጠቃሚ ብቻ ሳይሆን ሊበረታታ የሚገባው ነው።

አንደኛ- ከአማርኛና እንግሊዘኛ ቀጥሎ ሌላ ሶስተኛ ቋንቋ ስለማስተማር
በአዲስ አበባና በአማራው ክልል (ከሚሴ ከተማ የሚገኝበት በአማራው ክልል የኦሮሚያ ልዩ ዞንን ሳይጨመር) በትምህርት ቤቶች የአማርኛና የእንግሊዘኛ ትምህርቶች ይሰጣሉ። በሌሎች ክልሎች ግን ዜጎች ሌላ ሶስተኛ ቋንቋ ይማራሉ። ለምሳሌ በትግራይ ክልል እንግሊዘኛ፣ አማርኛና ትግሪኛ፣ በደቡብ ክልል ሃዲያ ዞን ውስጥ እንግሊዘኛ፣ አማርኛና ሃዲይኛ፣ በሶማሌ ክልል እንግሊዘኛ፣ አማርኛና ሶማሌኛ ይማራሉ። የአዲስ አበባና የአማራው ክልል ተማሪዎች ግን ብዙ ቋንቋ አለማወቃቸው ጥቅሞች እንዲጎድልባቸው ሊያደርግ ይችላል ብለን እናስባለን።
ከአሥራ ዘጠኝ አመታት በፊት ፣ ሁሉም ክልሎች (ከአማራ ክልልና ከአዲስ አበባ በስተቀር) ከአማርኛ በተጨማሪ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸውን ስለሚማሩ፣ በአማራው ክልልና በአዲስ አበባ ግን የአፍ መፍቻና የፌደራሉ የስራ ቋንቋ አንድ በመሆኑ፣ የክልሉ ተማሪዎች አንድ የሀገር ውስጥ ቋንቋ ብቻ በመማር በወደፊት የስራ ህይወታቸው ላይ የሚደርሰውን ተግዳሮት ለመቀነስ፣ የክልሉ የትምህርት ቢሮ አንድ ጥናት አስጠንቶ ነበር። በዚህ ጥናት ዙሪያ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶ/ር በድሉ ዋቅጃራ፣ በፌስ ቡክ ገጻቸው፡ “በ1990 – የክልሉ ትምህርት ቢሮ ለጨረታ ያቀረበውን፣ የተጠቀሰውን ጥናት ያጠናነው እኔና ሁለት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የስነትምህር ባለሙያዎች ነበርን። በክልሉ በሳይንሳዊ መንገድ ናሙና በመውሰድ (ወላጆችን፣ የትምህርት አስተዳደር ሰራተኞችን፣ መምህራንንና ተማሪዎችን) በተደረገው በዚህ ጥናት የተገኘው ውጤት የኦሮምኛ ቋንቋ በክልሉ ትምህርት ቤቶች በሁለተኛ ቋንቋነት እንዲሰጥ በአንደኛነት መመረጡን ነው። ከዚህም ሌላ አጥኚዎቹ አዋሳኝ ቋንቋዎችን ከግምት ያስገባና ጥናቱን መሰረት ያደረገ ሀሳብ (recommendation) አቅርበን ነበር” ሲሉ ጽፈዋል። ዶ/ር በድሉ፣ ከሰማኒያ ሺህ ብር በላይና ወደ አንድ አመት ገደማ የፈጀው ጥናት ውጤት፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ባዘጋጀው መድረክ ቀርቦ ውይይት እንደተደረገበት ገልጸዋል። በመሆኑም ክብርነትዎ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የአማራው ክልል የትምህርት ፖሊሲ የሚሻሻልበትና ከአማርኛና ከእንግሊዘኛ ቀጥሎ በዜጎች ወይንም በወረዳው አስተዳደር ምርጫ ሶስተኛ የአገራችንን ቋንቋ የሚማሩበት ሁኔታ ቢመቻች ጥሩ ሊሆን ይችላል ብለን እሳስባለን። ያ ከሆነ አብዛኞቹ ወረዳዎች ምርጫቸው ኦሮምኛ ሊሆን ይችላል ብለን እናስባለን።

ይህ አሰራር በሰለጠኑት አገራት በተለይም በአውሮፓ የተመለደ አሰራር ነው። ለምሳሌ በፈረንሳይ የትምህርት ፖሊሲ እያንዳንዱ ዜጋ ከፈረንሳይኛና ከእንግሊዘኛ በተጨማሪ ሌላ ሶስተኛ ቋንቋ በምርጫ እንዲማር ይደረጋል። አንዳንዶቹ ጀርመንኛ አንዳንዶቹ ራሺያኛ፣ አንዳንዶቹ ጣሊያንኛ ይመርጣሉ።
ሁለተኛ – የግእዝ ፊደላትን መጠቀም የአገር ቅርስ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን የተሻለም ነው
ምእራባውያን ለጥቁር ህዝብ መሸጥና መዋረድ እንደ ምክንያት የሚጠቀሙበት አንዱና ትልቁ መከራከሪያቸው “ጥቁሮች የራሳቸውን ስነፅሁፍና ፊደል መቅረፅ ያልቻሉት ዝቅተኞች ስለሆኑ ነው” የሚለው ነው። ይሄን ትርክት ውድቅ ለማድረግ፣ ግእዝን ምናልባት የተሻለ ስምም ሰጥተን ኢትዮጲስ ወይም ሌላ ብለነው ወደቀረው አፍሪካ እንዲስፋፋ መታገል ነበረብን። ሆኖም በተለያዩ አገራዊ አጀንዳዎች በመወጠራችንና በሃገራችን የሰፈነው የማንነት ፖለቲካና ከኢትዮጵያ የተለየ ማንነት ይፈልጉ የነበሩ አክራሪ ብሄርተኞች አሉታዊ ጫና ምክንያት አላደረግነውም። እንኳን ወደ አፍሪካ አገሮች ግእዝን ልንወስድ ቀርቶ በአገራችን የነጮችን ፊደል፣ ላቲን፣ ለአንዳንድ ኢትዮጵያ ቋንቋዎች እየተጠቀምን ነው። አንዳንድ ወገኖች የግእዝ ፊደልን የአንድ ብሄረሰብ እርስት አድርገው የመቁጠር ዝንባሌ ሲኖራቸው አንዳንዶች ደግሞ የግእዝ ፊደል ብቃት እንደሌለው አድርገው ያስባሉ። የላቲን ፊደላት ተናጋሪው እንደሚናገረው አይጻፉም። ስፔሊንጉን ለማወቅ ችግር ነው። በኢትዮጵያ ፊደላት ግን ሰው እንደሚናገረው ስለሚጻፉ፣ የስፔሊንግ ስህተት ሊሠራባቸው አይችልም። ስለዚህም ከላቲን ፊደል ይልቅ ግእዝ የበለጠ ይመረጣል።

ኤርትራውያን መቼ የግእዝን ፊደል አንፈልግም አሉ? ከኢትዮጵያ ተገነጠሉ እንጂ መቼ ከፊደላችን ተገነጠሉ? እንዲያውም እነሱ ቀደም ሲል በጣልያን ቅኝ ግዛት ተገዝተው ስለነበር፣ በላቲን እንቸክችከው ቢሉ፣ ጥሩ ሰበብ በሆናቸው ነበር። ከላቲን ይልቅ ኢትዮጵያውያኑ ፊደላት ብዙ ጥቅሞች እንዳላቸው በመገንዘባቸው ግን ፊደሎቻችን ላይ ሙጭጭ ብለው ይዘዋቸው ሄዱ።

ግእዝ የአማራው ማህበረሰብ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያውያን ቅርስ ነው። ከአረብኛ ውጭ ብቸኛው የጥቁር ሕዝብ ፊደል ነው። አማርኛ፣ ትግሪኛ፣ ጉራጌኛ፣ ሃዲዪኛ፣ ከንባትኛ፣ ንዉርኛ፣ አኙዋክኛ፣ አገውኛ፣ አደሪኛ፣ ስልጢኛ… በአሁኑ ጊዜ የግእዝ ፊደላትን ነው የሚጠቀሙት። አደሪኛ ለአስር አመታት ላቲን ይጠቀሙ የነበረ ቢሆንም ግእዝ ይሻላል ተብሎ ወደ ግእዝ ዞሯል።

ኢትዮጵያ በአባቶቻችንና እናቶቻችን መስዋትነት ነጻነቷን ጠብቃ የኖረች አገር ናት። የራሷ ባህል፣ የራሷ ቋንቋዎች፣ የራሷ ፊደል፣ የራሷ ቅርሶች አሏት። በአገራችን የሌለ፣ ለአገር የሚጠቅም፣ ከባእድ አገር ብንወስድ ችግር አይኖረውም። ሆኖም ግን የተሻለ ነገር ከእኛ ጋር እያለ የሌሎችን ማምጣት ተገቢ አይደለም። ፊደል እንደሌለን፣ ቅኝ የተገዛን ይመስል፣ የኛን የተከበረ ፊደል ጥለን ላቲንን ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች መጠቀም ሊበረታታ አይገባም።

ሌሎች ክልሎች የተለየ መስመር ቢከተሉም የአማራው ክልል ግን የአገርን ቅርስ በማስጠበቅ አንጻር የመሪነት ሚናውን እንዲወጣም በአክብሮት እንጠይቃለን።

ሶስተኛ – የግእዝ ፊደላትን ለኦሮሞኛ ስለመጠቀም
አፋን ኦሮሞ በላቲንም በግእዝም ይጻፋል። በኦሮሚያ ክልል በተለይም ኢሕአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ የተወለዱ ወገኖች አፋን ኦሮሞን በላቲን ነው የሚጽፉትና የሚያነቡት። ሆኖም ላቲኑ በጣም ውስንነት አለው። በኦሮሚያ የሚኖሩ ሌሎች ማህበረሰባትና ከአርባ አመት በላይ የሆኑ ኦሮሞዎች ግእዝ ፊደልን ማንበብ ነው የሚቀናቸው። ቋንቋው በላቲኑ ምክንያት በኦሮሚያ ከተወሰኑ ወገኖች አጥር ውጭ ሊያድግ አልቻለም።

ዶ/ር ፍቂሬ ቶሎሳ፣ ለተከበሩ አቶ ለማ መገርሳ፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዘዳንት በታህሳስ ወር 2010 ዓ.ም. በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ከጻፉት ግልጽ ደብዳቤ፣ ለኦሮምኛ ከላቲን ይልቅ ግእዝን መጠቀም ምን ያህል በኢኮኖሚ፣ በትምህርት ቅልጥፍና፣ በሊንጉስቲክ (ቋንቋ ጥናት) እና በሳይንስ አንጻር የተሻለ መሆኑን አስነብበውናል። ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሶ የጻፉትን፣ ዶ/ር አበራ ሞላ ሌሎች በርካታ ምሁራን ያደረጉትን ጥናት በተወሰነ መልኩ ያካተተ ተያያዥ ሰነድ፣ በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በኦሮሞው ቄስ አባ ኦነሲሞስ ነሲቡ በግዕዝ ፊደላት መጫፈ ቁልቁሉ ተብሎ ከተተረጎመው የኦሮምኛ ቅዱስ መፅሃፍ ውስጥ የተወሰዱ ሁለት ገፆችን አብረን አያይዘናል።

ክቡርነትዎ ሆይ!
እርስዎ አንደሚገነዘቡት፣ በባዕዳን ፊደል የሚጽፉ አፍሪካውያን፣ በአውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች ሲገዙ የነበሩና ራሳቸው የፈለሰፏቸው የፊደላት አማራጭ ያልነበራቸው ሕዝቦች ናቸው። እኛ በጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ደምና አጥንት ነፃነታችን ተከብሮልን የኖርንና አኩሪ ቅርስ የሆነ የራሳችን ፊደል ያለን ሕዝቦች ቅኝ እንደተገዙትና እንደተዋረዱት ያልታደሉ ሰዎች ልንሆን አይገባም።

በእዚህና እላይ በተዘረዘሩት የአመክንዮ ምክንያቶች፣ እንዲሁም ስለ ክብራችንና ማንነታችን ሲባል እርስዎና የአስተዳደር ባልደረቦችዎ፣ አፋን ኦሮሞ የኢትዮጵያ ቋንቋ እንደመሆኑ በኢትዮጵያዊ ፊደል በግእዝ እንዲጻፍ ፈር ቀዳጅ ይሆኑ ዘንድ በአክብሮት እንጠይቅዎታለን። በአንድ ጊዜ ሁሉንም ማድረግ ባይቻልም፣ ቢያንስ በተወሰኑ ለኦሮሚያ ክልል ቅርበት ባላቸው ወረዳዎች በግእዝ የአፋን ኦሮሞ ትምህርት የሚሰጥበትን ሁኔታ ማመቻቸት ቢቻል በጣም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል ብለን እናስባለን።

በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት፣ በኦሮሞው ቄስ አባ ኦነሲሞስ ነሲብ፣ በግዕዝ ፊደላት “መጫፈ ቁልቁሉ” ተብሎ የኦሮምኛ ቅዱስ መጽሓፍ ተተርጉሟል። የዛሬ 120 ዓመት እንኳን፣ ቅዱስ መፅሐፍን የሚያህል በራሳችን ፊደላት መፃፍ ከቻልን፣ አሁንማ በዘመነ ኮምፒዩተር፣ በቀላሉ ኦሮምኛን ግዕዝ በሚባለው ኢትዮጵያዊ ፊደል ያለ ችግር መክተብ የማንችልበት ምንም ምክንያት አይኖርም። ዋናው ቀና ልቦና፣ በራስ ፊደል ኩራትና ፍላጎት ናቸው!!

ከታላቅ አክብሮት ጋር፣
1. ዶ/ር አበራ ሞላ
2. ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ
3. ፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ
4. ዶ/ር ባዬ ይማም
5. ፕሮፌሰር ሃይሌ ላሬቦ
6. አትሌት ገዛኸን አበራ
7. አቶ ግርማ ሰይፉ
8. አቶ ያሬድ ጥበቡ
9. አቶ ሰይፉ ኣዳነች ብሻው
10. አቶ ተፈራ ድንበሩ
11. አቶ ሙሉጌታ ዉዱ
12. አቶ አበባየሁ ደሜ
13. አቶ ብርሃኑ ገመቹ
14. አቶ አብርሃም ቀጄላ
15. አቶ ሃብታሙ ኪታባ
16. አቶ ግርማ ካሳ

ግልባጭ፣
ለአማራው ክልል የትምህርት ክፍል ቢሮ
ለአማራው ክልል የኮሚኒኬሽን መስሪያ ቤት
ለኦሮሚያ ክልል ፕሬዘዳንት ክብር አቶ ለማ መገርሳ
ለባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት

ኦሮምኛን በግዕዝ ፊደል መጻፍ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ከታሪክ፣ ከባህል፣ ከጠቀሜታና ከአመችነት አኳያ ያለው ጥቅም በስፋትና በዝርዝር ያስቀመጠ ጥናታዊ ሰነድ ከእዚህ በታች “ግእዝ ከላቲን ለምን እንደሚሻል የሚያመላክቱ ነጥቦች” በሚል ርዕስ ቀርቧል።

ግእዝ ከላቲን ለምን እንደሚሻል የሚያመላክቱ ነጥቦች

1. ከኢኮኖሚ አኳያ ግእዝ ከላቲን ይሻላል

የሚከተለውን የቁቤ ጽሁፍ ወስደን፣ ከግእዝና ከላቲን ፊደል የትኛው ይበልጥ ውጤታማና ብቁ እንደሆነ እንመለከታለን፦
Uummanni Oromoo ilmaan namaa biyya lafaa
ኡመኒ ኦሮሞ ኢልማን ነማ ብያ ለፋ
Kanarratti Uumaman kessaa tokkodha Biyyi
ከነረቲ ኡመመን ኬሳ ቶኮዳ ብዪ
Uumamaa fii jireenya issa Aafrikaa Bahaa
ኡመማ ፊ ጅሬኘ ኢሳ አፍሪካ በሃ
Gara kaabaatti Yemmuu ta’u Uummmata
ገረ ካባቲ የሙ ተኡ ኡመተ
Baha gaanfa Aafrikaatti argamu keessaa
ባሃ ጋንፋ አፍሪካቲ አርገሙ ኬሳ
Isa tokko Seenaan uummata kanaa akkuma
ኢሳ ቶኮ ሴናን ኡመተ ከና አኩማ
Seeraaf sirnaan qulqulleessee barreesse
ሴራፍ ሰርናን ቁልቁሌሲ በሬሴ
Jiraachun baatullee uummata seenaa
ጂራቹ ባቱሌ ኡመተ ሲና
Gudddaa fii gaarii qabu akka ta’e huba
ጉዳ ፊ ጋሪ ቀቡ አከ ተኤ ሁበ።
Chuun nama hin dhiba
ቹን ነመ ሕንድቡ።

ከላይ ከቀረበው ናሙና ውስጥ የተወሰኑ ቃላትን እየጠቀስን፣ ኦሮምኛን ለመጻፍ ከላቲኑ እና ከኢትዮጵያው ፊደል የትኛው ብቁና ቀልጣፋ፣ ጊዜና ገንዘብ ቆጣቢ እንደሆነ እንይ፤ Uummanni Oromoo ilmaan namaabiyya lafaa “Uumamaa” የሚለው ቃል በላቲን ሲጻፍ 7 ሆሄያት ፈጅቷል። በኢትዮጵያው ግን “ኡመማ” ተብሎ በ3 ፊደላት ይጻፋል። “oromoo” የሚለው ቃል በላቲን 6 ሆሄያት አሉት፤ በግዕዝ ግን “ኦሮሞ” ተብሎ በ3 ሆሄያት ይጻፋል። “ilmaan” የሚለው በላቲን 6 ሆሄያት አሉት፤ በግዕዝ ግን አራት በቂው ነው። “namaa፣ biyya፣ lafaa፣” የሚሉትም ቃላት፣ በላቲኑ እያንዳንዳቸው 5 ሆሄያት ፈጅተዋል። በግዕዙ ቢሆን ግን “ነማ፣ ቢያ፣ ለፋ” ተብለው እያንዳንዳቸው በ2 ፊደላት ይጻፋሉ።

ኡመኒ ኦሮሞ ኢልማን ነማ ብያ ለፋ Kanarratti Uumama kessaa tokkodha Biyyi የሚሉትን ደግሞ ስናይ “Kanarratti” በላቲን ሲጻፍ 10 ሆሄያት ያስፈልጉታል። በኢትዮጵያው ፊደል በግዕዙ ግን በ 4 ሆሄያት ይጻፋል። “Uumaman” በላቲን 7 ሆሄያት ያስፈልጉታል፡፡ በግዕዝ ግን 4 ሆሄያት ይበቁታል፡፡ “kessaa” የሚለው በላቲን 6 ሆሄያት ያስፈልጉታል። በራሳችን ፊደል ግን “ኬሳ” ተብሎ በ2 ፊደላት ይጻፋል። “Tokkodha” እና “Biyyi” የሚሉትም በላቲን እንደ ቅደም ተከተላቸው 7 እና 5 ሆሄያት ሲኖሯቸው በግዕዝ ግን 3 እና 2 ሆሄያት ብቻ ነው የሚኖራቸው። ነገሩ በገጽ ሲታሰብ፣ በላቲን 100 ገጽ የሚፈጅ ጹሁፍ፣ በግዕዝ ግን በ40 ገጽ ሊጻፍ ይችላል። ብዙ ሺ ኮፒ ሲታተም በላቲን ሲሆን አላግባብ የሚባክነውንና በግዕዙ ሲሆን ግን የሚቆጠበውን ስንትና ስንት ቶን ወረቀት አስቡት። ጊዜንና ገንዘብን በተመለከተም እንዲሁ ነው። ለምሳሌ ባለ 100 ገፅ በላቲን የተፃፈው መፅሃፍ በ100 ሳንቲም ቢታተም፣ በግዕዙ የተከተበው ግን 40 ሳንቲም ብቻ ይሆናል። ሂሳቡ በሺ ብር ቢሰላ፣ በላቲን ቢፃፍ 6000 ብር ማዳን ይቻላል ማለት ነው። የዚህን ሁሉ ትርፍና ኪሳራ አይተው እርስዎ ይፍረዱ።

2. ከታሪክ አኳያ – ኦሮምኛ በግእዝ ከጥንት ጀምሮ ይጻፍ ነበር

ለእኛ ለአሁኑ ዘመን ሰዎች አዲስ ነገር ይመስለናል እንጂ ለኦሮሞ አባቶቻችን፣በኢትዮጵያ ፊደላት መፃፍ አዲስና እንግዳ ጉዳይ አይደለም። በቅርቡ በደርግ ዘመን እንኳን “በሪሳ” የሚል ጋዜጣ ነበር። ከዛሬ 120 ዓመታት በፊት ቄስ ኦነሲሞስ ነሲብ፣ ሙሉውን ቅዱስ መፅሐፍ፣ ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ራዕዩ ዮሃንስ ከትበውበት ነበር። ከዛሬ 200 ዓመት በፊትም እንደፃፉበት የሚያሳይ ሰነድ፣ በቀጣፊው “ጆግራፊ ላጠና ነው” ብሎ መጥቶ፣ ብርቅዬውን “መፅሃፈ ሄኖክ”ን ይዞ በኮበለለው በጀምስ ብሩስ እጅ ተገኝቶ ነበር። ቀደም ሲል በግዕዝ ፊደላት በኦሮምኛ ስለተፃፉት ሰነዶች ሁሉ ጠቅለል አድርጎ ለመናገር

1ኛ. ከ16ተኛው ክፍለ ዘመን በፊት የተከተበ ቅዱስ ቁርአን በሀረር ይገኛል።
2ኛ. በ1845 ከአፄ ቴዎድሮስ ዘመን በፊት የመፅሐፍ ቅዱስ ወንጌላት በከፊል የተፃፉበት
3ኛ. ከላይ አንደጠቀስኩት፤ ከ120 ዓመታት በፊት በኦሮሞው ሊቅ በቅዱስ ኦነሲሞስ ነሲብ (አባገመችስ) ሙሉው መፅሐፍ ቅዱስ በአፋን ኦሮሞ የተተረጎመበት
4ኛ. በ1967 ዓ.ም. ከ20 በላይ በሆኑ በተለያዩ ብሄርና ብሄረሰቦች ቋንቋ፣ የመሬት አዋጅን ፈትፍቶና ቁልጭ አድርጎ የተገለፀበት
5ኛ. የኢትዮጵያ የመሠረተ ትምህርት ከ30 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች ቋንቋዎች፣ በብቃትና በጥራት ይሰጥበት የነበረ
6ኛ. የ“በሪሳ” ታላቅ የአፋን ኦሮሞ ጋዜጣ ለዘመናት በበርካታ ቁጥሮች ሲሰራጭበት የነበረ
7ኛ. የቀድሞው የኢትዮጵያ ህዝባዊ ሪፐብሊክ መንግሥት በበርካታ ባብዛኛው፣ ከ45 ብሔር ብሔረሰቦች በላይ ቋንቋዎች የተገለጡበት
8ኛ. በበርካታ የእስልምና ዝክሮች፣ መንዙማዎች የተፃፋበትና የተዘከሩበት
9ኛ. በርካታ የክርስትያን መዝሙራት በኦሮምኛና በሌሎች ቋንቋዎች የተገለጡበት
10ኛ. በአፋን ኦሮሞና በሌሎችም ከረጅም ዘመናት በፊት የመዝገበ ቃላት የተደራጀበት ናቸው።

እንኳን ዛሬ ዳብሮ በኮምፒዩተር ሳይንስ ተደግፎ ድሮም ቢሆን ኢትዮጵያውያኑ ፊደላት ተፈትነው፣ ኦሮምኛን ለማስተናገድ እንደሚችሉ ተረጋግጧል። በዶክተር አበራ ጥረት፣ በዩኒኮድ ዩኒቨርሳል ኮድ በመግባታቸው ጠቀሜታቸው ተገልፆ፣ ዓለምአቀፍ ዕውቅናን አግኝተዋል።

ከኦሮምኛ በተጨማሪ፣ በኣሁኑ ጊዜ ግዕዝ በዩኒኮድ ዕውቅና ያገኙትን የቢለን፣ ቤንች፣ ምኢን፣ ሙርሲ፣ ሱሪ፣ ትግረ፣ ትግርኛ፣ ኣገው፣ ኣውንጂ፣ አማርኛ፣ ዲዚ፣ ዳውሮ፣ ጉሙዝ፣ ጉራጌ፣ ጋሞ ጎፋ እና ግዕዝ ቋንቋዎች የሚጋሯቸውን ቀለሞችና ሌሎችንም ያስከትባል። ለእዚህም ተግባር የዶ/ር ኣበራ ሞላ ግዕዝኤዲት ገበያ ላይ ውሏል።

3. ከአገራዊ ስነልቦና፣ ከአመችነትና ከቅለት አኳያ ግእዝ ከላቲን ይሻላል

ኦሮምኛን የማይናገሩ አያሌ ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ጊዜ ኦሮምኛን መማር ይፈልጋሉ። በአማራው ክልል እንደ አዲስ፣ አፋን ኦሮሞ ትምህርት እንዲሰጥ ሲደረግ፣ በባዕዱ ፊደል በላቲን መሆኑ የተማሪዎችን የመማር ፍላጎት በእጅጉ ያመነምነዋል። ያለ ፍላጎት የሚደረጉ አዋጪነታቸው አጠያያቂ ነው የሚሆነው።

በመሆኑም አፋን ኦሮሞ ሕዝቡ የእኔ ቋንቋ ነው ብሎ ደስ ብሎት እንዲማረው፣ የርሱ ፊደል በሆነው በግእዝ ማቅረቡ፣ ከአገራዊ ስነ-ልቦና አንጻር በጣም አስፈላጊ ነው። ያ ብቻ አይደለም፣ በግእዝ ፊደላት ተማሪዎች እንዲማሩ ቢመቻችላቸው በቀላሉ ሊቀስሙት ይችላሉ። በግድ በላቲኑ ተማሩ ካልናቸው ግን፣ “ጊዜና ገንዘብ ከሚያባክነው ከላቲኑ ፊደል ይልቅ ቆጣቢ፣ ቀልጣፋና ምቹ በሆነውና በምናውቀው ባገራችን ፊደል እንጽፋለን” ቢሉ፣ ይህ አቋማቸው በቀላሉ የሚታይ አይሆንም።

አንድ ተማሪ የግእዝ ፊደላትን ማንበብና መጻፍ ሲችል አማርኛን ብቻ አይደለም ማንበብና መጻፍ የሚማረው። ትግሪኛንም፣ አፋን ኦሮሞ በግእዝ ከተጻፉ ኦሮሞኛንን፣ ጉራጌኛንና ሌሎችንም ነው። በመሆኑም ለመጀምሪያ ጊዜ አፋን ኦሮሞ ተማሪዎች በግዕዝ ፊደል ሲማሩ፣ አፋን ኦሮሞ እንግዳ አይሆንባቸውም። በቀላሉ ይረዱታል።

4. ከሳይንስ አኳያ – ኦሮምኛን በኮምፒተር በተሟላ መልኩ መጻፍ ይቻላል

ኦሮምኛ በኢትዮጵያ ቀለማት ቢፃፍ የተሻለ ነው ሲባል፣ አንዳንድ የድሮ ፖለቲከኞችና የቀድሞ ታጋዮች የሚያቀርቧቸው ሰበቦች፣ “አንዳንድ የኦሮምኛ ቃላት በተለምዶ ግዕዝ በሚባለው ኢትዮጵያዊ ፊደላት ሊፃፉ አይችሉም፣ ለታይፕራይተርም አይመቹም፣” የሚሉ ናቸው። ይህ ግን እውነት አይደለም። ለምሳሌ አይቻሉም ተብለው የነበሩት ፊደላትና ቃላት በኦሮሚያዊትዋ ልጅ፣ በሰንዳፋው ተወላጅ በዶክተር አበራ ሞላ መላ እነሆ ተችለዋል።

ዸዹዺዻዼዽዾዿ
ዹፌ፣ ዻባ፣ ዻራርቱ፣ ባዻዻ፣ ዼራ፣

ልክ እንደ ላይኛዎቹ ፊደላትና ቃላት፣ የኦሮሞ ቀለማት ሁሉ በኢትዮጵያ ፊደላት ተቀርፀው በተግባር ለመዋል እየጠበቁ ነው። እድሜ ለዶክተር አበራ ሞላ እ.ኤ.አ. ከ1987 ጀምሮ በሶፍትዌር ደረጃ ተዘጋጅተው ገበያ ላይ ውለዋል። የአንዱን ቃል ከሌላው መለያ የማጥበቂያ ምልክቶችም ተበጅቶላቸዋል። ዶክተር አበራ ሞላ፤ የግዕዝ ፊደላት ለኦሮምኛና ለሌሎቹም ዋና ዋና ቋንቋዎቻችን መፃፊያ ብቁ እንዲሆኑ ለ35 ዓመታት ያህል ለፍተውባቸዋል። ስለዚህ የኢትዮጵያ ፊደላት የላቲኑን ሊተኩ የማይችሉበት ምንም ምክንያት የለም። አውቆ የተደበቀን ቢጠሩት አይሰማም ካልተባለ በቀር። የኢትዮጵያ ፊደላት ኦሮምኛን ለመክተብ ብቁ ከመሆናቸውም በላይ ብዙ ጥቅም ያላቸው መሆናቸውን የሚመሰክሩ ሰነዶች ተዘጋጅተዋል። ዊኪፔድያ ውስጥ ገብተው የዶክተር አበራ ሞላን የምርምር ውጤት ይመልከቱ። የአዲስ አበባው ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ባዩ ይማም በበኩላቸው፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ቀደም ብለው ሰፊ ጥናት አካሂደዋል።

ግዕዝ በዶክተር ኣበራ ሞላ ኮምፕዩተራይዝድ ሆኖ ለዓማርኛ ተመድበው ከተረፉት ሦስት መርገጫዎች ኣንዱ ለኣፋን ኦሮሞ (Afan Oromo) ሲሆን ሌላው ለትግርኛ ተሰጥቶ የቀረው ለኣገው/ቢለን ሥራ ላይ ውለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በ፲፱፻፹፫ ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ ጊዜ የአንድ ድርጅት ኦሮሞ ምሁራን ተሰብስበው ከግዕዙ ይልቅ ላቲን ይበጀናል በማለት ግዕዙን (Ethiopic Oromo syllabary) ስለተዉት የሚከተሉትን መጋራት ሳይጠቅም ኣይቀርም።

፩. ጥንትም ቢሆን ፊደላት በእጅ ጽሑፍ ሲጻፉ ላቲን ከግዕዙ በፍጥነት የተከተበበት ጊዜ ኣልነበረም። ምክንያቱም ግዕዝ ኣንድን ድምጽ በኣንድ ቀለም ሲያሰፍር ለኣብዛኛው የላቲን ድምጾች ሁለት ቀለሞች ስለሚያስፈልጉት ነው።

፪. የላቲንና ግዕዝ ቀለሞች በማተሚያ መሣሪያዎች ሲከተቡ የሁለቱም ቀሎሞች መረጣዎች ኣጠቃቀሞች እኩል ነበሩ። በእዚህ ዘዴ የኦሮምኛ ዓማርኛ መተርጐሚያ በ1850 ግድም በኣቶ ሓብተ ሥላሴ (Lexicon) [857] እና ለኦሮምኛ ሥነጽሑፍ የመጀመሪያው አዲስ ኪዳን ከጥቂት ዓመታት በኋላም ሚስዮኑ ክራጵፍ (J.L. Krapf) በ፲፰፻፸፩ ዓ.ም. በራሱ ስም ያሳተመው ይህንኑ የነአለቃ ዘነብን ፲፰፻፷፪ ዓ.ም. ሥራ “ቁልቁሎታ መጻፎታ ከኩ ሐረዋ” ነበር። [858] ኣለቃ ዘነብ ወደ ፲፰፻፸ ዓ.ም. ግድም የ“ኦሮምኛና ኣገውኛ መዝገበ ቃላት” ጽፈዋል ይባላል። የኣስቴር ጋኖን የትርጕም መጽሓፍ በመጠቀም በ፲፰፻፹፯ ዓ.ም. የታተመም የኦሮምኛ ሓዲስ ኪዳን፣ [859] መጫፈ ቁልቁሉ በ፲፰፻፺፱ እ.ኤ.ኣ. (፲፰፻፺፪ ዓ.ም.) በቅዱስ ኦነሲሞስ ነሲብ፣ [860] [861] እና ከእዚያም ወዲህ እንደነ በሪሳ የኣሉ ጋዜጣዎች በግዕዝ ፊደል በኦሮምኛ ታትመዋል። ቀደም ብሎም በግዕዝ ፊደል በኦሮምኛ ከቀረቡት መረጃዎች ኣንዱ ጀምስ ብሩስ የወሰደው የ1790 የኦሮምኛ ትግጉም ጽሑፍና ሌላም ኣለ። [862] በእጅ የጽሕፈት መሣሪያ ዘመን ታይፕራይተር ዓማርኛን ስለኣልጻፈ ላቲን ብልጫ ነበረው።

፫. በዶክተሩ ኮምፕዩተራይዝድ የሆነው ግዕዝ እ.ኤ.ኣ. በ1987 ለገበያ ቀርቦ በማተሚያ ቤቶች ፊደላቱ መክተብ ስለተጀመረ ምሁራን ደስ ሊላቸውና ሳይንሱንና ቴክኖሎጅውን ማወቅና ማስተዋወቅ በተገባ ነበር። ይህ በኣለመደርጉ እ.ኤ.ኣ. 1992 [863] በፕሮፈሰር ጥላሁን ጋሜታ ወደ ላቲን ለማዞር ከቀረቡት የኣማርኛ የጽሕፈት መኪናን የሚመለከቱት ጊዜ የኣለፈባቸው ምክንያቶችም መልሶች ነበሩ። [864] [865][866] ስለዚህ በግዕዝ ፊደል በማተሚያ ፊደላት ሲጻፉ የነበሩት በኮምፕዩተር ስለቀረቡ ቴክኖሎጂው ስለተሻሻለና ስለቀለለ ጉዳዩ ይመለከተናል የኣሉት የኦሮሞ ምሁራን ሊደሰቱ የሚገባ እንጂ ወደ ላቲን የሚያስዞር ኣዲስ ምክንያት ኣልነበረም። በጊዜውም በፕሮፌሰር ባዬ ይማም በዓማርኛ መልስ ቀርቦ ፕሮፌሰር ሚንጋ ነጋሽና ፕሮፌሰር ሳሙኤል ክንዴ ወደ እንግሊዝኛ ተርጕመውታል። [867]

፬. ላቲን የእራሱ ችግሮች የኣሉት ፊደል ነው።
[868] [869] [870] [871] በዶክተሩ ፈጠራ እየኣንድኣንዱን የግዕዝ ቀለም በሁለት መርገጫዎች መክተብ ተቻለ። ላቲን ይኸን እየኣንዳንዱን የግዕዝ ቀለም በሁለት መርገጫዎች የመክተብ ችሎታ ስለሌለው ግዕዝን በግዕዝ ፊደል መክተብ ብልጫ ኣገኘ። ስለዚህ ኦሮምኛን በላቲን ፊደል መክተብ (ቁቤ) መሻሻል ኣይደለም።

፭. ይህ በእንዲህ እንዳለ የኦሮምኛው የግዕዝ ፊደል ከሌሎቹ ጋር በዶክተሩ ኮምፕዩተራይዝድ ስለሆነ [872] ለኣለፉት ፴ ዓመታት በኮምፕዩተር ቀርቦ በኋላም በዩኒኮድ ዕውቅና ቢያገኝም [873] ሁሉም ባይሆኑ ኦሮሞዎች ግዕዙን እርግፍ ኣድርገው ጥለው ወደ ላቲኑ ስለዞሩ የተፈጠሩት ችግሮች ቀጥለዋል።

፮. በእጅ የጽሕፈት መሣሪያ ዘመን ታይፕራይተር ኦሮምኛን ስለኣልጻፈ ላቲን ብልጫ ነበረው። የዶክተሩ ፈጠራ ለእውሸቱ (የፈጠራ) የታይፕራይተር የአማርኛ ነገሮችና ለትክክለኛዎቹ የማተሚያ ቤቶች ፊደላት ኣጠቃቀሞች ፈውሶች (Breakthrough) ነበር። ስለ ታይፕራይተሩ ድክመት ዶክተሩ እ.ኤ.ኣ. በ1991 [874] [875] ስለኣቀረቡ መሣሪያው ወደ ላቲን ለመዞር ምክንያት መሆን ኣልነበረበትም። ከእዚያም ወዲህ በኮምፕዩተር የኦሮምኛው የግዕዝ ፊደል በዶክተሩ መከተብ ችሎታና የተጠቃሚዎች መኖር ግንዛቤ ውስጥ ሳይገቡ ብዙ ዓመታት ባክነዋል።

፯. ቁቤ በላቲን ዋየሎች ከሚጠቀምባቸው በተሻለ ኣፋን ኦሮሞ በግዕዙ ሊጠቀም ይችላል። የኦሮምኛን ፊደል ለመክተብ ከላቲኑ ቁቤ የግዕዝ ፊደል ይጠቅማል። [876] [877]
፰. መጽሓፍ ቅዱስ በከፊል እ.ኤ.ኣ. በ1841 በኦሮሞ ቋንቋ በግዕዝ ፊደል ተጽፏል። [878] [879] እንዲሁም እ.ኤ.ኣ. በ1875 የኦሮሞ ሓዲስ ኪዳን በግዕዝ ፊደል ታትሟል። [880] [881] [882]

፱. በልሳነ ግእዝና በኣፋን ኦሮሞ (ግእዚፊ ኣፋን ኦሮሞቲን – Giiiziifi Afaan Oromootiin) የተዘጋጀው መጽሓፈ ቅዳሴ – ክታበ ቅዳሴ – Kitaaba Qiddaasee መጋቢት 10 ቀን 2008 ዓ.ም. በኢሊሌ ሆቴል ተመርቋል። የትርጐማና የኣርትኦት ሥራው 10 ዓመታት የወሰደው ባለ ሦስት ዓምዱ ክታበ ቅዳሴ፦ የመጀመርያው ረድፍ በግእዝ ቋንቋ፣ ሁለተኛው ረድፍ በኦሮምኛ ሆኖ በግእዝ ፊደል፣ ሦስተኛው ረድፍ በኦሮምኛ ሆኖ በቁቤ ፊደል ተጽፏል ይላል ሪፖርተር ጋዜጣ። [883] ይህ የግዕዝ ፊደል ኦሮምኛን ኣይጽፍም ለሚሉት ማፈሪያ ነው።

፲. መጽሓፍ ቅዱስ ሙሉዉን ወይም በከፊል ከ፲፭፻፮ ዓ.ም. ጀምሮ በግዕዝ ቀለሞች በማተሚያ ቤቶች ከታተሙባቸው ቋንቋዎች መካከል የግዕዝ ቋንቋ(ግዕዝኛ)፣ ዓማርኛ፣ ትግርኛ፣ ኦሮምኛ [884] [885] [886] ፣ ሃዲያ፣ ሲዳሞ፣ ከንባታ፣ ወላይታና ጌዴኦ ይገኙበታል። ስለዚህ ለዓመታት በማተሚያ ቤቶች የግዕዝ ፊደላት ሲከተብ የነበረው ኦሮምኛ ኮምፕዩተራይዝ ሆኖ ዛሬ ሥራ ላይ እየዋለ ግዕዝ ኦሮምኛን ኣይጽፍም ማለት ሳይንስ ኣይደለም።

፲፩. በኣነሰ የኆኄያት ግድፈቶች (Spelling / እስፔሊንግ) እና ስፍራዎች (Spaces) ማስከተብ ብልጫዎች የነበረው የግዕዝ ፊደል በዶ/ር ኣበራ ፈጠራ የተነሳ የግዕዝ ፊደል ሓሳብን በኣነሰ ጊዜ (Time)፣ መርገጫዎች (Keystrokes) እና ገበታዎች (Keyboards) በኮምፕዩተሮችና የእጅ ስልኮች በማስከተብ ብልጫዎቹ ወደ ኣምስት ዓይነቶች ከፍ ብለዋል። ለምሳሌ ያህል “ዘ ኲክ ብራውን ፎክስ ጃምፕስ ኦቨር ዘ ሌይዚ ዶግ።” የሚለውን ዓረፍተ ነገር ላቲን በ36 ቀለሞችና በቁቤ በ45 ቀለሞች ከመክተብ ይልቅ በግዕዝ ፊደል በ24 ቀለሞች መክተብ የተሻለ ነው።

፲፪. የቁቤ ሥርዓት እ.ኤ.ኣ. በ1992 ገደማ የተመሠረተው ኣንዱ ቀለም ኣንድን ድምጽ በመወከል ነው ተብሏል። የላቲንም ሆነ የቁቤ ቀለሞች ኣንድን ድምፅ በኣንድ ቀለም ከሚወክለው የግዕዝ ፊደል ጋር የመወዳደር ችሎታ የላቸውም። ላቲን ኣንድኣንድ ድምጾችን የሚከትበው በሁለት ቀለሞች ስለሆነ ሁሉም ቀለሞች ለየብቻቸው ኣንድ ድምጽ እንዲወክሉ እንኳን ተደርጎ መጠቀም ኣይቻልም። ለምሳሌ ያህል “d” እና “h” የ“ዽ” እስፔሊንግ ስለሆኑ “ዲ” እና “ኤች”ን በሁለት ቀለምነት ጎን ለጎን ኣስቀምጦ በ“d” እና “h” ድምጽ ሰጪነት መጠቀም ኣይቻልም። ይህ ምሳሌ የሚያሳየው ቁቤ የተመሠረተው በጥቂት የኦሮሞ ምሁራን ማምታታትም ላይ መመርኰዙን ነው።

፲፫. ማንኛውንም የኦሮሞ ፊደል በሦስት መርገጫዎች መክተብ ነውር ነው። ማንኛውንም የኦሮምኛ ድምጽ በሦስት መርገጫዎች መክተብ ነውር ነው።

፲፬. ጥቂት የኦሮሞ ምሁራን ዓማርኛ የማጥበቂያ ምልክት የለውም የሚሏቸውን ስሕተቶች ቀጥለውበታል። ዓማርኛ መጥበቅ የኣለበትን ቃል ከማይጠብቀው የሚለይበት ሁለት ዘዴዎች ኣሉት። ከእነዚህ ኣንዱ ከሚጠብቀው ቀለም ኣናት በላይ ኣንድ ነጥብ መክተብ ሲሆን ምሳሌውም በ፲፮፻፺ ዓ.ም. ታትሟል። ይኸንንም ኣጠቃቀም ሓዲስ ዓለማየሁ [887] በ“ፍቅር እስከ መቃብር” መጽሓፋቸው ኣስፋፍተውታል። በኣዲስ ቅርጽ ለኮምፕዩተር እንዲስማማ መጥበቅ ከኣለበት ቀለም ኋላ እንዲከተብ ተደርጎ ማጥበቂያ በዶክተሩ ፓተንትም ውስጥ ኣ.ኤ.ኣ. በ2009 ተጠቅሷል። [888]

፲፭. የቁቤ ዋየሎች “ኤ”፣ “ኢ”፣ “ኣይ”፣ “ኦ” እና “ዩ” (“a”፣ “e”፣ “i”፣ “o” አና “u”) ስለሆኑ በቁቤ “ክታበ”ን ከ“ኪታባ” የመለየት ችግሮች ኣሉት። ይህ በኣዲስ ፊደልነት የቀረበውንም [889] ይመለከታል። ግዕዝ ሰባት እንዚራን ሲኖረው ኦሮምኛ 10 ያስፈልጉታል የተባለው ትክክል ከኣለመሆኑም ሌላ ቍጥሩን መጨመርም ስለኣላዋጣም ኣልቀጠለም።

፲፮. ይህ ግዕዝና ኦሮሚፋ ሳይንሳዊ ጽሑፍ ስለ ፊደላቱ እንጂ ቋንቋዎቹን ኣይመለከትም። የኦሮሞ ቋንቋችን መዳከም ስለሌለበት ስለ ፊደል ስንወያይ ሰለኣልፈጠርናቸው ቋንቋና ኦሮሞነት መቀላቀል ሳይንስ ኣይደለም።

፲፯. እነ “ሸ”፣ “ቸ”፣ “ኘ”፣ “ዸ”፣ “ጠ”፣ “ጨ”፣ “ጰ”፣ እንዚራኖቹንና ሌሎች ቀለሞች የኣሉትን ለኦሮምኛ የሚያስፈልጉትን ቀለሞች ትቶ እነዚህን ወደ የሌሉት የላቲን ፊደል መዞር ሳይንስ ኣይደለም። [890]

፲፰. የኦሮምኛ ድምጾችንና እርባታዎችን የሚወክል የፊደል ገበታ (ከኣማርኛ ታይፕራይተር፣ ዓረብኛና ላቲን) ለጊዜው የተሻለው ላቲን ነው በማለት በስሕተት የቁቤ ኣጻጻፍ ሥራ ላይ ዋለ። ይህ ለዓማርኛው በኣለመደረጉ ዶክተሩ በመፍትሔው የደረሱለት ለኣፋን ኦሮሞ ጭምር ነው። ምክንያቱም ዓማርኛና ኣፋን ኦሮሞ በትክክለኛው የግዕዝ ፊደል ለብዙ ምዕት ዓመታት ተጠቅመዋል። [891] የጄምስ ብሩስና ሌሎች መረጃዎችም ኣሉ። ስለዚህ ዓማርኛውንም ሆነ ሌሎችን ቋንቋዎቻችን ለማይጽፈው የዓማርኛ ታይፕራይተር ሲባል ፊደሉን የተዉት ቋንቋዎች በኣንድኣንድ ተናጋሪዎች ስሕተት እንጂ በግዕዝ ፊደል ሲጠቀሙ በነበሩ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ስሕተት ኣልነበረም።

፲፱. በዶክተሩ ፈጠራዎች ከ“አ” እና “ኸ” መርገጫዎች ፲፬ የግዕዝ ቀለሞች እየተከተቡ ናቸው። [892] [893]

፳. ቁቤ በ“a”፣ “e”፣ “i”፣ “o” እና “u” በተጠቀመው ዓይነት በ“ኣ”፣ “ኤ”፣ “ኢ”፣ “ኦ” እና “ኡ” የግዕዝ ቀለሞች መጠቀም ይችል ነበር። ኣንዳንድ ኦሮሞዎች “ቢራ” በላቲን ኦሮሚፋ “biirraa” ተብሎ የሚጻፈው ግዕዝ ስለማይችለውም ነው ይላሉ። በ“biirraa” ምትክ “ብኢኢርርኣኣ” ተብሎ በግዕዝ ፊደል መጻፍ ይቻላል። ስለዚህ ቁቤ የተመሠረተው ሳይንሳዊ ጥቅም ላይ ኣይደለም። “ቢ” እና “ራ” ቀለሞችን ዓማርኛ በኣራት ዓይነቶች ማለትም “ቢራ”፣ “ቢ’ራ”፣ “ቢራ’” አና “ቢ’ራ’” መጠቀም ይችላል።

፳፩. ኣንድኣንድ የኦሮሞ ምሁራን ግዕዝ የኦሮምኛ ቃላትን ኣይጽፍም በማለቱ በኣለማወቅ በስሕተቱ ገፍተውበታል። ጎዸቱ፣ ቶኮፋዸ፣ ዹፌ፣ ዹጉማ፣ ጀዺ፣ ዻባ፣ ዻራርቱ፣ ባዻዻ፣ ዻዻ፣ ጄዼ፣ ዼራ፣ ዽባፍ፣ ዽባ፣ ነንዾከዼስ ምሳሌዎች ናቸው።

፳፪. ጥቂት የኦሮሞ ምሁራን “ዻ” የግዕዝ ኦሮምኛ ቀለም በኣንድ ቀለም በሁለት መርገጫዎች ከመክተብ ይልቅ “dha” በማለት በሦስት ቀለሞችና በሦስት መርገጫዎች በኦሮሚፋ መክተብ የተሻለ ሳይንስ ይመስላቸዋል።

፳፫. በሚገባ ሳይታሰብበት የግዕዝ ቀለሞች በላጭነት ጥቅሞች ሳይገለጹ ታልፈዋል። ምሳሌ፦ ግዕዝ ችግር የለውም ማለት ሳይሆን የላቲን ቃላት እስፔሊንግ እድሜ ልክ ቢማሩትም ማስታወስ ኣይቻልም። በእዚህ ላይ “ኦሮሞ” የሚለው ቃል እስፔሊንግ በላቲን “Oromo” በኦሮሚፋ የኣለ በቂ ምክንያት “Oromoo” ነው።

፳፬. በኣጠቃቀም የላቲን ፊደል ከግዕዝ ሳድሳን ቀለሞች ጋር ኣንድ ዓይነት ነው። ግዕዝ እንዚራኑን በኣንድኣንድ ቀለሞች ሲወክል ላቲን ዋየሎቹን ሳድሳኑ ጎን ማስከተብ ስለኣለበት ከሰባት ጊዜ በላይ እጥፍ ስፍራዎች ያስባክናል።

፳፭. ጥቂት የኦሮሞ ምሁራን በስሕተት ኦሮሚፋ 10 እንዚራን ሲያስፈልገው ግዕዝ ሰባት ብቻ ኣለው ይላሉ። ዋየል መደራረብ ትርፉ ስፍራ ማባከን ነው። [894]

፳፮. ጥቂት የኦሮሞ ምሁራን በስሕተት ላቲን 26 ቀለሞች ሲኖሩት የግዕዙ ብዙ ናቸው ይላሉ። የላቲን “a” ዓይነቶች ከ26 በላይ ናቸው።

ኦሮምኛን ጨምሮ እሱ ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች የፈጸመውን ተግባር ሁሉ በሚከተለው የዊኪፒዲያ ሊንክ ማግኘት ይቻላል።

https://am.wikipedia.org/wiki/%E1%8A%A3%

E1%89%A0%E1%88%AB_%E1%88%9E%E1%

88%8B#%E1%8C%8D%E1%8B%95%E1%

8B%9D%E1%8A%93_%E1%8A%A6%E1%88%

AE%E1%88%9A%E1%8D%8B

በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በኦሮሞው ፓስተር ኦነሲሞስ ነሲብ በግዕዝ ፊደላት መጫፈ ቁልቁሉ ተብሎ ከተተረጎመው የኦሮምኛ ቅዱስ መፅሃፍ ውስጥ የተወሰዱ ሁለት ገፆች

LEAVE A REPLY