ታህሳስ 28 2010
አንዲት የገጠር ኮረዳ እሁድ ሰርግሽ ነው ስትባል ቅዳሜ ለእሁድ ዋዜማ የጫጉላ ቤቱን አሰራር ስትለማመድ፣ እንደተባለችው ሳይሆን ቀርቶ ስትሳቀቅ፣ በሳምንቱ ደግሞ ሰርግሽ ነው ስትባል፣ ለእሁዱ ስራ ቅዳሜን ስትደሰት እንደገና ሲከሽፍ፣ በመጨረሻ የሚባለው ነገር የማይፈፀም ሲሆንባት “ከእንግዲህስ ካልታዘልኩ አላምንም” አለች አሉ፡፡
ልብ በሉ! ተደግሶ፣ ዳስ ተጥሎ እድምተኛ ሞልቶ ሲበላ ሲጠጣና ሲጨፈር ቢዋል እንኳ ታዝዬ ከወላጆቼ ግቢ እስከምለቅ ድረስ አላምንም ነው ያለችው፡፡ የኢህአዴግና የኢትዮጵያ ህዝብ ነገርም እንደዚህ ያለ ሆኗል፡፡ “ከሰማይ በታች የቀረን የለም ….ለሆድ ሳናስቀር ተነጋግረን አንድ ሆነናል … ከዚህ በኋላ መፍትሄ እንደምንሆን እመኑን…” ባይ ቃልኪዳናችሁን ኢህአዴጎች ለራሳችሁ አድርጉት፡፡
በናንተ ላይ ህዝብ ሃሳቡን የማይጥለው “ታደስን” እያላችሁ በተደጋጋሚ ስለከሸፈባችሁ (ሌላው ቀርቶ የህዝቦች ብሶት ባስደንጋጭ አኳኋን ከገነፈለበት ከ2008 አመት እስከ 2009፣ ሁለት አመት ያህል በሆነ ጊዜ ውስጥ በቶሎ ፍርጥርጥ ያለ ተሃድሶ ማድረግ ዳገት ሆኖባችሁ አገሪቱም ድርጅታችሁም የፍንዳታ ጠርዝ ላይ እስከሚደርሱ ስለዘገያችሁ) ብቻ አደለም፡፡ ባንድ ድርጅት ላይ ሃሳብን መጣል መፍትሄ ሳይሆን ችግር ስለሆነ፣ እስከዛሬም ድረስ የአገሪቱና የህዝቦቿ እጣ ከኢህአዴግ ጋር ተያይዞ በመቆየቱ ኢህአዴግ ችግርና አደጋ ውስጥ ሲገባ የአገሪቱና የህዝቦቿም እጣ አደጋ ውስጥ ሲገባ ቆይቷል፤ አሁንም የሆነው ይህ ነው፡፡ እውነት ነው፤ ህዝብ አሁን ከወሬና ከቃል ኪዳን ይልቅ ተከታታይ የተግባር ለውጦችን ይሻል፡፡
እውነት ነው፤ ይህ ሁሉ የሰዎች ደም የፈሰሰበትና ከፍተኛ የኑሮ መፈናቀል የደረሰበት ቀውስ የመጣው፣ በቶሎም ሳይቀጭ የሰነበተው በናንተ አመራር ድክመት ነው፡፡ ይህንንና እንደቡድንም እንደግለሰብም ተጠያቂነት እንዳለባችሁ ማመናችሁ ትልቅ ነገር ነው፡፡ በተግባርም ግጭት ከቆሰቆሰው አንስቶ ትእዛዝ እየሰጠ የገደለና ያስገደለም ሆነ ፈጣን መፍትሄ ከመስጠት የቦዘነ አካልና ግለሰብ ሁሉ ሲጠየቅ ማየት ህዝብ ይፈልጋል፡፡
አደጋ ውስጥ የገባውን የአገሪቱንና የህዝቦቿን ሰላም ካደጋ ማውጣትና ማስተካከል አጣዳፊ ተግባር መሆኑም እውነት ነው፡፡ ይህ አጣዳፊ ተግባር ግን የአገሪቱን እጣ ከኢህአዴግ እጣ ከማላቀቅ (የኢህአዴግ መከፋፈልና መናቆር ወደ አገር በመሸጋገር ፈንታ የራሱ ጣጣ ሆኖ የሚቀርበትን ለውጥ ከማካሄድ) ተግባር ሊነጠል አይችልም፡፡ እያጠፉ፣ ህዝብ እየበደሉና እያፈኑ በስልጣን ላይ መኖር የተቻለው፣ የህግ የበላይነት የተጎሳቆለው፣ የፍትህ ሚዛን ተዛንፎ እስከ ወህኒ ቤት ድረስ በፖለቲካዊ ማጥቂያነት ጭምልቅልቁ የወጣው፣ እንደትግሉ ሁሉ የድሉ ባለቤትና ጠባቂ እኛ ነን ባዮችና ሌላውን በጥርጥሬ ተመልካቾች/ በእብሪት አርበድባጆች ተበራክተው የትግራይ ህዝብ ያለሃጢያቱ ለመጠመድ የበቃው ወዘተ የአገሪቱ መንግስት አውታሮች በኢህአዴግ መርህ ስለተቀረፁ፣ ጠላቴና ወዳጄ በማይል የዴሞክራሲና የፍትህ ገለልተኛነት መርህ ስላልታነፁ ነው፡፡ ካሁን በኋላ ግን ኢህአዴግ መርሄ የሚለው ነገርና “መርህ አልባነት” ምንትስ የሚል መተቻቸቱ የራሱ ድርጅታዊ ጉዳይ እንዲሆን፣ ከዚያ ውጪ ግን፣ በህገመንግስት ወረቀት ላይ ደንዝዞ የቆየው የኢወገንተኛነት