የትግራይ ህዝብ ታግሎ መስዋእት ከፍሎ አምባገነናዊውን የደርግ ስርዓት ከስልጣን በማባረሩ ሊመሰገን ይገባ ነበር። ግን ሲመሰገን አላየንም። ለምን? ምክንያቱም የደርግ አምባገነናዊ ስርዓት ቢባረርም በሌላ የኢህአዴግ አምባገነን ስርዓት ስለተተካ። የኢትዮጵያ ህዝብ ከደርግ ቢላቀቅም ከአምባገነን ስርዓት ግን አልተላቀቀም። ደርግ ቢሄድም ስርዓቱ ግን አሁን ድረስ አለ።
እንዲያውም አዲሱ ትውልድ የደርግን መጥፎነት አያውቅም። ማወቅም አያስፈልገውም። የኢህአዴግን መጥፎነት ማወቅ በቂው ነው፤ በዚሁ ትውልድ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ያለው የኢህአዴግ እንጂ የደርግ መጥፎነት አይደለም። የደርጉ አልፏል። ያለፈን ለመቀየር አትታገልም፤ በቃ ተቀይሯላ! የኢህአዴጉ ግን አሁንም አለ። ስለዚህ ልትቀይረው ይገባል። ለመቀየር ማወቅ አለብህ። እናም የኢህአዴግ ስርዓት ልንቀይረው የሚገባ ያሁኑ ጉዳያችን ነን። ደርግ ግን አጀንዳችን አይደለም፤ አልፈዋልና። ረስተነዋል። ምክንያቱም እጫንቃችን ላይ ሌላ ደርግን የሚያስረሳ አፋኝ ስርዓት አለብን።
የትግራይ ህዝብ ለነፃነትና እኩልነት ታገለ እንጂ አንድን አምባገነን በሌላ አምባገነን ለመተካት አልነበረም። አምባገነንነት ብሄር የለውም። የኢህአዴግ ስርዓት በትግራይ ህዝብ ደም ያገኘውን ስልጣን ለህዝቦች ነፃነትና እኩልነት ማስፈን ቢያውለው ኖሮ የትግራይ ህዝብ እንደተመሰገነ ይኖር ነበር። ምክንያቱም ከደርግ በኋላ ሌላ አምባገነን አናይም ነበር። ሁሉም ህዝቦች በነፃነት መኖር ቢችሉ ኖሮ ዓመፅ ባልኖረ፣ ሰላም ባልደፈረሰ እና ህዝብ ባልተጎዳ ነበር። ህዝብ የፈለገውን ነገር (ስልጣንን ጨምሮ) በሰላማዊ መንገድ ማግኘት የሚችል ከሆነ ዓመፅ አያስፈልገውም። መንግስት ማንኛውም የህዝብ ጥያቄ መመለስ ነበረበት፤ ካልቻለ ስልጣኑን ለህዝብ ማስረከብ።
ኢህአዴግ ያላደረገው/ያደረገው ነገር ምንድነው?
(አንደኛ) ህወሓት ገና ስልጣን እንደያዘ “አሸንፌያለሁ” በማለት የህዝቦችን ፍላጎት ሳያዳምጥ የራሱን አሻንጉሊቶች በየክልሎቹ ሾመ። ለምሳሌ ህወሓት “ኦነግ የኔ መሳርያ ሊሆን አይችልም” በማለት ኦነግን አባሮ ኦህዴድን መረጠ። ኦነግ በጠላትነት ተፈረጀ። ኦህዴድ የተመረጠው የኦሮሞን ህዝብ ለማገልገል ሳይሆን ህወሓትን ለማገልገል ነበር። የኦሮሞ ህዝብ የፈለገውን እንዲመርጥ ሊፈቀድለት ይገባ ነበር።
በሌሎች አከባቢዎችም የደርግ የምናምን ርዝራዦች እየተባሉ ብዙ ሰዎች በተሸናፊ ጠላቶች ተፈረጁ። የህወሓት የስልጣን ዘመን ገና ከጅምሩ በ”አሸናፊዎች” እና በ”ተሸናፊ ጠላቶች” ግንኙነት ላይ የተመሰረተ መሆኑ አመላከተ። ባንድ ሀገር ውስጥ አሸናፊና ተሸናፊ ካለ እኩልነት ሊኖር አይችልም፤ አሸናፊና ተሸናፊ እኩል አይደሉማ። እኩልነት ባልሰፈነበት ዴሞክራሲ አይኖርም። ዴሞክራሲ ከሌለ ዓመፅ ይኖራል፤ እያየነው ነው።
አሸናፊና ተሸናፊ አንድ ላይ ተባብረው ሀገር ሊያለሙ አይችሉም። በዚህ ላይ ህወሐት “ተሸናፊዎቹን” በጠላትነት ፈርጇቸዋል። በጠላትነት የፈረጅከው አካል እንዲተባበርህ አትጠብቅ። አንተን ለማሸነፍ አይተኛም። ጠላት መፍጠር አልነበረበትም። ሁሉም በገዛ ሀገሩ ተከብሮ እንዲኖር ሊፈቀድለት ይገባ ነበር። አሁን “ጠላቶች ስርዓታችንን ለማፍረስ እየሰሩ ነው ገለመሌ” ብትል ሰሚ የለህም። አዎ ጠላት ከሆነ ሊያፈርስህ ይጥራል። አሁንማ ህዝብ ሁሉ ጠላትህ ሆኗል።