ከፎቶው ቃል አለ /አባይነህ ካሴ/

ከፎቶው ቃል አለ /አባይነህ ካሴ/

ከፎቶው ቃል አለ /አባይፎቶውን ዐይቼ፣
ሙግት ውስጥ ገብቼ፣
ደግሜ ሳስበው ቆይቼ ቆይቼ፣
የናፈቀኝን ቃል ከፎቶው ሰማሁት፣
አበው ምን ተባባሉ ማለቴንም ተውሁት።

ከፍሩሃን መኻል አንዱ የበረቱ፣
ዓላማውን ይዘው አብረው የሞቱ፣
እጄ ልቤ ላይ ነው እዩት ይመልከቱ፣
አንቱ ብቻ አይደሉም የኔም ነው ስራቱ፣
ካቴናው አይደለም ለእኛ ሠንሰለቱ፣
የጥንት የጠዋቱ ነባር ነው ቅናቱ፣
ጸጋ እንዲበዛ እንጅ ቆዩ ከተፈቱ፡፡

ጌታን ያሠረ ዓለም ለእኛ እንዴት ይራራ፣
ትቢያ ነህ ስንለው ይኾናል መራራ፣
ገድሎን ይፈጽሙ የአምላክን አደራ፣
ብቻዎን አይደሉም ብዙ ነን የቆምነው ከዓላማዎ ጋራ።

እኔን አባቶቼን እኔን ደጋጎቹን፣
ግፍ ያበዛል እንጅ ማሠር የተፈታን፣
የክርስቶስ አካል ከእንግዲህ ምን ሊኾን?
ወኅኒ ቤቱ ቀርቶ መቃብር ተረትቷል፣
በሰማዩ ችሎት በየማን ይቆማል።

አባም ሲመልሱ
ከንፈር ከትናጋ ሳያንቀሳቅሱ
ሊጠይቁን መጡ፣
አባቴ ቆራጡ።
ዐይኖቼና ዐይኖችዎ፣
እጅ በልብዎ፣
የተነጋገርነው ቁም ነገር ነውና፣
ዕለት ይድረስልን እንደ ወይነ ቃና።
ሥጋዬ እንጂ ነፍሴ ሐሴት ላይ እንዳለች፣
ልብዎ ራሷ ዛሬ ምስክር ነች፣
ከዓላማችን ስንዝር ዝንፍ የለም ፍንክች።

የአበውን ቃል ኪዳን ቀርቦ ላስተዋለ፣
ብዙ በጣም ብዙ ከአበው የተዋለ፣
ቢነገር ማይገባ መክኖ ላልታደለ፣
ላገር ለኢትዮጵያ ተብሎ የተከፈለ፣
ሌላም ሌላም ብዙ ከፎቶው ቃል አለ።

LEAVE A REPLY