/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- ኢትዮጵያ በገጠማት የጸጥታ ችግር የደቡብ ሱዳንን “የሰላም ድርድር” ማካሄድ እንደማትችል የደቡብ ሱዳን የመንግስት ቃል አቀባይ አስታወቀ።
ኢትዮጵያ የእራሷን ችግር ሳትፈታ ደቡብ ሱዳን ከአማጺያን ጋር የምታደርገውን የሰላም ድርድር በሀገሯ ማስተናገድም ሆነ ከመምራት እንደማትችልና ይልቁንም ለራሷ የውስጥ ችግሮች መፍትሔ ማምጣት ይኖርባታል ሲሉ ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስታት(ኢጋድ) የደቡብ ሱዳን መንግስትን ከተቃዋሚው ጥምረት ጋር ሽምግልና በሚቀጥለው ሳምንት በአዲስ አበባ ለማካሄድ ጥሪ ማቅረቡን ተከትሎ የደቡብ ሱዳን የመንግስት ቃል አቀባይ ለራዲዮ ታሙጃ እንደገለጹት፤ የሰላም ድርድር የሚካሄድበት ቦታ ከኢትዮጵያ እንዲቀየር ጠይቀዋል።
ቃል አቀባዩ እንደገለጹት መንግስት ከተቃዋሚዎች ጋር የሚያደርገውን የሰላም ድርድር በታቀደለት ጊዜ እንዲከናወን በጁቡቲ፣ ኬንያ ወይም በዩጋንዳ እንዲካሄድ አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የሰላም መታወክ ስላለ በማንኛውም ጊዜ በሚፈጠር ግጭት ድርድሩ ሊቋረጥ ስለሚችል ከወዲሁ ወደ ሌላ ሀገር እንዲቀየር መንግስታቸው መወሰኑን ጨምረው ገልጸዋል። የኢጋድ የወቅቱ ሊቀመንበር የሆኑት ጠ/ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ጉዳይም ገና እንዳልተፈታ ጠቅሰው በዚህ ሁኔታ ለድርድር አዲስ አበባ ላይ መቀመጥ የሀገራቸው ፍላጎት አለመሆኑንም ቃል አቀባዩ አብራርተዋል።በኢጋድ የሚመራውን የደቡብ ሱዳን “የሰላም ድርድር” ኢትዮጵያ ለአማጺያኑ ታደላለች በማለት ጁባ በተደጋጋሚ ስሞታ ስታሰማ ቆይታለች።
ደቡብ ሱዳን ከእናት ሀገሯ ሱዳን ጋር በርካታ ዓመታትን አስከፊ የሆነ የእርስ በርስ ጦርነት አካሂዳ እ.ኤ.አ በ2011 ነጻ ብትወጣም የተመኘችውን “ነጻነት” ከሁለት ዓመታት በላይ ሳታጣጥም በ2013 ዳግም ወደ ማያባራ የእርስ በርስ ጦርነት ተዘፍቃ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ደቡብ ሱዳናዊያን ህይወታቸውን ሲያጡ፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩት ደግሞ ከቀያቸውና ሀገራቸው መፈናቀላቸው ይታወቃል።