/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- የኢትዮጵያን ጉዳይ የሚመለከተው H.R 128 የተባለው ረቂቅ ህግ በአሜሪካ ም/ቤት ለውሳኔ እንደሚቀርብ ተገለጸ።
በኒውጀርሲ ተወካይ ክሪስ ስሚዝ የተረቀቀውና በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድጋፍ ያለፈው ረቂቅ ህግ የፊታችን የካቲት 9/2018 ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ለውሳኔ እንደሚቀርብ የኮሎራዶ እንደራሴ ማይክ ኮፍ ማን ዛሬ በቲዉተር ገጻቸው አስታውቀዋል። ረቂቅ ህጉ በአሜሪካ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሁለቱም ፓርቲዎች (በሪፓብሊካንና ዴሞክራት) እስካሁን የ88 እንደራሴዎችን ድጋፍ ማግኘቱም ተገልጿል።
House Resolution 128 (H.R 128) የተባለው ረቂቅ ህግ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝ እንዲሻሻል፣ሁሉን አቀፍ ህዝባዊ መንግስት እንዲመሰረት፣ የሚዲያ ነጻነት እንዲከበርና ሌሎች ድንጋጌዎችን ያካተተ ነው።
የምክር ቤቱ ረቂቅ ህጉን ካጸደቀው የኢትዮጵያ ህዝብ እያካሄደው ላለው የነጻነት፣የፍትህና የእኩልነት ትግል አውንታዊ አስተዋፅዖ የሚያደርግ ሲሆን የስርዓቱ ባለስልጣናትን የበለጠ አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚከታቸው ይታመናል።