ሲመቱት ይጠብቃል /ከአንተነህ መርዕድ/

ሲመቱት ይጠብቃል /ከአንተነህ መርዕድ/

ማርች 22 ቀን 2018

የኢትዮጵያ ህዝብ ለበርካታ ዓመታት የሚገባውን እንደዜጋ በነፃነት የመኖር መብት ለመጎናፀፍ ያደረገው ጥረት ሁሉ በአምባገነኖቹ እየተዳጠ አሁን ላለበት ዝቅተኛ ኑሮና ለከት ያጣ ግፍ ተዳርጓል። የግፉ ፅዋ ሞልቶ መፍሰስ በመጀመሩም ከአስከፊው ስርዓት ጨርሶ ለመላቀቅ በተለይ ባለፉት ሶስት ዓመታት እልህ አስጨራሹን ትግል ተያይዞታል። የአሁኑ ትግል ካለፉት በብዙ መልኩ የተለየ ነው። ህዝባዊ አመፁ ሰከን ያለና ህዝቡን ከዳር ዳር ያሳተፈ ለአምባገነኖቹ ጨርሶ ያልተመቸ፣ ግፈኛውን አገዛዝ ቀስ በቀስ እየደማ እንዲሞት የሚያደርግ ነው።

ፈረንጆች ቢስማር ሲመቱት እያደር ይጠብቃል እንዲሉ፤ ባለመዶሻው ወያኔ የህብረተሰቡ አንጓ የሆኑትን ራስ ራሳቸውን መታሁ ሲል የበለጠ ማህበራዊ ትስስሩንና የትግሉን ሂደት ሲያጠብቁት እናያለን።

አማራውን በጠላትነት በፕሮግራሙ ነድፎ ከሌላው ህብረተሰብ ጋር በማቃቃር ግፍ ሲፍፅምና ሲያስፈፅም፣ ይህ ለምን ይሆናል ያሉትን ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስን በግፍ ቢገድልም ዛሬ አማራው ይህንን ግፍ ተቀምጦ የማያይ፣ አስፈታነው ሲሉት ነጥቆ የሚታጠቅ፣ በገደሉት ቁጥር የሚገድል፣ አጠፋነው ባሉ ቁጥር ጉሮሮአቸው ላይ የሚሰነቀር አጥንት ሆንኗል።

ኦሮሞውን ለስልጣን አጃቢነት ለመጠቀም ኦነግን ከተገለገሉበት በኋላ የወረወሩ ወያኔዎች መሬቱንና ሃብቱን በመቀራመት ልጆቹን በመግደልና በማሰር የከመሩበትን እዳ ዛሬ እነሱ እንዲከፍሉት እያስገደዳቸው ነው። ኦሮሞው ሺዎች ሞተውበት፣ ሚሊዮን ተፈናቅሎና ተሰድዶ ቄሮና ልሂቃኑ በሰከነ ሁኔታ የስርዓቱን ስስ ብልት እየመታ እንዳይነሳ ከማደባየቱም በላይ በወያኔ ሲቀነቀን የነበረው “አገር ሊያፈርሱ ነው” የሚል ቅጥፈት ከንቱ ሆኖ የኢትዮጵያ ባለቤትነቱን እያሳያቸው ነው።

ከህዝብ በተዘረፈ ገንዘብና በተባባሪዎች ደባ አንዳርጋቸው ፅጌ ታፍኖ ቢታሰርም ትግሉን ሺ ጊዜ አሳደገው፣ ብዙ ሺ አንዳርጋቸዎችን አፈራ፣ አንዳርጋቸው ነፃነት ለሚሹ የፅናት ተምሳሌት የሆነውን ያህል ለወያኔ መንፈሱ እንቅልፍ የሚነሳ ቅዠት ነው።

ፖለቲከኞች የዴሞክራሲ ስርዓትን ለማስፈን ህዝባቸው መሃል ስለተንቀሳቀሱ ብቻ ተገድለዋል፣ ታስረዋል፣ ተሰድደዋል። ታስረው የወጡት አንዱዓለም አራጌ፣ በቀለ ገርባ፣ መረራ ጉዲና፣ አበበ ቀስቶ፣ ሃብታሙ አያሌው፣ የሺዋስ አሰፋ፣ ማሙሸት አማረ፣ ስማቸውን ዘርዝረን የማንጨርሳቸው ኢትዮጵያውያን አስረን፣ ሞራላቸውን ገድለን ለቀቅናቸው ሲሉ የበለጠ የበሰሉ፣ ለየነገዋ ኢትዮጵያ ተስፋ የሚሆኑ መሪዎች ሆነው ወጡ።

በነፃ ሚድያው ጎራ የህዝቡ ድምፅ የሆኑትን ጋዜጠኞች ማሰርና ማሰደድ ለወያኔ ምንም እንዳልበጀው እስክንድር፣ ተመስገን፣ ውቭሸት፣ወዘተ በህዝባቸውና በዓለም ያገኙትን ክብርና የነሱን ፅናት ለተመለከተ፣ ርዕዮት፣ ሲሳይ፣ መሳይና ሌሎችም በርካታ በዓለም የተሰራጩ ጋዜጠኞች በሙያቸው ህዝባቸውን በማገልገል ለለውጡ የሚያደርጉት አስተዋፆ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ እንዳልሄደ አሳይቷል።
በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ስርዓቱ አመራሮቹ ላይ ወኪሎቹን ቢያስቀምጥም የሙስሊሙ ያላሳለሰ ትግል፣ የመሪዎቹ ፅናት፣ በኦርቶዶክስ ገዳማትና መነኮሳት የሚፈፀመው ግፍ ስርዓቱን ጨርሶ ከምዕመኑ የሚነጥል፣ ህዝባዊ ትግሉንም የሚያጎለብት እየሆነ ነው የሄደው።

ህወሃት በአገልጋይነት ያቋቋማቸው ድርጅቶች እንኳ ከሚሞት ስርዓት ጋር ላለመሞት ብለው ብቻ ሳይሆን ለአገራቸውና ለህዝባቸው የሚበጀው ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን መገንባት መሆኑን በማረጋገጥ ክውስጡ ሰንገው ይዘውታል። በምርኮኞችና የኢትዮጵያን ህዝብ እስከ አጥንቱ ግጠው በበሉ አደግዳጊዎቹ ሊያፍናቸው ቢሞክር ህዝባቸው ከጎናቸው ከመሆኑም በላይ እነሱ የታገሉለትን ዓላማ ዳር ሳያደርስ እንደማያርፍ በተግባር እያሳየ ነው።

ወያኔ እየዛለ በሄደ ክንዱ መታሁ ባለ ቁጥር እየጠበቀ የሄደው ህዝባዊ ትግል በአምባገነኖች የሬሳ ሳጥን ላይ የመጨረሻዋን ቢስማር ለመምታት ተቃርቧል። ከዚህ ጋር መታሰብ ያለበት ቀጣዩ እርምጃ የተገኙ ድሎች እንዳይነጠቁ ህዝቡ በዘላቂነት የሚጠብቅበትን መንገድ መነጋገርና ስርዓቱን ከአሁኑ ማበጀት መጀመር ላይ ማተኮር ያስፈልጋል። ህዝቡ የማይመቸውን ስርዓት ማፍረስ ላይ ያተኮረውን ያህል የሚፈልገውን አዲስ ስርዓት መገንባት የሚጀመረው ከአሁኑ በመሆኑ በሁሉም መስክ ህዝባዊ መሰረቶችን መጣል ላይም ሃሳብ መቀያየርና የተግባር እንቅስቃሴም መጀመር ያለበት ወቅት ላይ ነን።

LEAVE A REPLY