የአባይ ግድብ ተጠናቅቆ አገልግሎት ይሰጣል ከተባለ ከሁለት አመት በኋላ ግድቡ እንዴት እየተሰራ እንደሚገኝ አዲስ ፕሮፖጋንዳ ተጀምሯል። እንደእኔ እምነት ትህነግ/ኢህአዴግ የወቅቱን የፖለቲካ ትኩሳት ለማብረድ ቀዳሚ ሚና ይጫወታል ያለው ሚዲያውን ነው። ለዚህም ሚዲያዎች፣ እና የብሮስካስት ባለስልጣንም ሳይቀር እስር በእርሳቸው ከመገማገም ያለፈ እጅ ሲጠቋቆሙ ተመልክተናል። በስተመጨረሻም ሚዲያዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሕዝብ እንቅስቃሴን ከማስተላለፍ እንዲቆጠቡ፣ በአንፃሩ “ልማት” ቀዳሚ አጀንዳ እንዲመሰል የተወሰነ ይመስላል።
በአሁኑ ወቅት “በቆሎ፣ ድንች……” መሰል የግብርና ዜና ሕዝብን አስልችቷል። አሁንም ሕዝብ የሚጠብቀው የግድቡ ዜና እንደሆነ “ተገምግሟል”። በመሆኑም ባለፉት ጊዜያት ቀዝቀዝ ብሎ የነበረውን የ”ታላቁ ሕዳሴ ግድብ” ፕሮፖጋንዳ እንደገና በተጠናከረ መንገድ ሚዲያው ላይ ማምጣት አስፈልጓል። ለዚህም ሲባል ገንዘብ የሚሰበስቡት እንደገና ሕዝብን እንዲቀሰቅሱ፣ እንደ ቅርስ ግደቡን ማስጎብኘትን ስራቸው ያደረጉት አምባሳሰሮችን ሳይቀር እንዲጎበኙ በማድረግ ይህን ዜና ማድረግ ላይ ተጠምደዋል። በዚህ መሃል የጊዜያዊ አዋጁ “ስኬት” ብቻ እንዳይደበዝዝ “አቅጣጫ ተቀምጧል።” ይህ ትህነግ/ኢህአዴግ ግድቡ ከሚገባው በላይ ተጋንኖ እንዲታይ በሚሰራው ፕሮፖጋንዳ የሕዝብን ቀልብ ለመያዝ እየተጠቀመበት ያለው ዘዴ ነው። እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው፣ እኔም የምህንድስና ባለሙያ በማነጋገር የግድቡን እውነታዎች እንደሚከተለው ለማቅረብ ሞክሬያለሁ።
የግድቡ እውነታዎች!
አባይ ላይ ግድብ ለመገንባት አጤ ኃይለስላሴ ከ1948 እስከ 1956 ዓም በአሜሪካኖቹ ጥናት አስደርገው ነበር። ደርግም ተመሳሳይ ጥናት አድርጎ እንደነበር ይነገራል። ከ1997ቱ የሕዝብ ትግል ቅልበሳ በኋላ በ2001 ዓም አረቦቹ ለዓለም በተለይም ለአፍሪካ የአብዮት ወጋገን ሲያሳዩ፣ ትህነግ/ኢህአዴግ ሕዝብን የሚያባብልባቸው ካርዶች መካከል አንዱን መምዘዝ ነበረበት፣ አባይን! ይህን ሲያደርግ ግን በአጤ ኃይለስላሴም በደርግም ያልተጠና፣ እሱ የጀመረው አዲስ ፕሮጀክት ማስመሰል ነበረበት።
ከ7 አመት በፊት መጋቢት 2003 ዓም ለሕዝብ አዲስ ፕሮጀክት ተደርጎ በአቶ መለስ ዜናዊ በኩል የተገለፀው ፕሮጀክቱ ከስም ጀምሮ ብዙ ለውጦች ተደርገውበታል። ከስሙ ብንነሳ እንኳ መጀመርያ “x”የሚል ስያሜ ነበረው ተባለ። ለሕዝብ ይፋ በተደረገበት ወቅት ደግሞ “የሚሊኒየም ግድብ” ብለው አስተዋወቁት። ሚያዝያ 2003 ዓም በሚኒስትሮች ምክር ቤት “ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ” ግድብ ተብሎ እንዲጠራ ተወሰነ። ይህ “ታላቅ” የሚል ስም በተሰጠው ወቅት ከተጀመረ ከ3 አመት ከ8 ወር በኋላ የመጀመርያ ምዕራፍ ኃይል ያመነጫል ተብሎ ታቅዶ የነበር ቢሆንም ስም የመቀያየሩን ያህል አልተሳካለትም። ከድሃው ገንዘብ የመሰብሰቡን፣ በሚዲያ የማደንቆሩን፣ በስብሰባ ስለግድቡ የመልፈፉን፣ “ታላቅ” ግድብ እያሰራ ነው ስለተባለው የኢህአዴግ ፖሊሲ “ስኬት” የመለፍለፉን ያህል ጠብ ያለ ውሃ፣ ብልጭ ያለ የመብራት ምልክት አልነበረም።
ብዙ የተወራለት የግድብ ግንባታ ለሳሊኒ የተሰጠው ያለ ውድድር ነበር። መጀመርያ ሳሊኒ ለግንባታው ውል የወሰደው 4 ነጥብ 8 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የነበር ቢሆንም ይህ ገንዘብ ከቆይታ በኋላ ወደ 6 ቢሊዮን ዶላር ከፍ እንዳለ ተገልፆአል። ግድቡ ባለፉት ሁለት አመታት ውስጥ ተጠናቅቆ አገልግሎት ይሰጣል ብለው በየሚዲያ ሲያወሩ የነበሩት ባለስልጣናትና ሚዲያዎች፣ ዛሬ ላይ፣ ይጠናቀቃል ከተባለ በኋላም “እየተፋጠነ ነው፣ ተጎበኘ፣ 60 ምናምን ፐርሰንት ተጠናቅቋል……” በማለት ላይ ናቸው።
ከስም፣ ከበጀትም ባሻገር የግድቡ አቅምም ባለስልጣናቱ በሞቃቸው፣ ፕሮፖጋንዳው በደራ ወቅት ተቀያይሯል። መጀመርያ ላይ 14 ተርባይኖች እያንዳንዳቸው 375 ሜጋ ዋት ያመነጫሉ ተብሎ ነበር። ከጊዜ በኋላ እነዚሁ ተርባይኖች እያንዳንዳቸው 400 ሜጋ ዋት እንደሚያመነጩ ተገለፀ። እነዚህ ተርባይኖች መጀመርያ ያመነጫሉ የተባሉት ከ155 ሜትር ርቀት ነበር። በቁጥር ደረጃ የ25 ሜጋ ዋት ማሻሻያ ሲደረግባቸው የሚያመነጩበት ርቀት አልተሻሻለም። ይህም ማለት ተሻሽለዋል ተባሉ እንጅ 400 ሜጋ ዋት ማመንጨት አይችሉም ማለት ነው። 400 ሜጋ ዋት ማመንጨት ከነበረባቸው 375 ሜጋ ዋት ለማመንጨት ከነበረው 155 በተሻለ ርቀት መሻሻል ነበረባቸው። በግልፅ ቋንቋ ኩባያ ይይዘው የነበረውን ውሃ ስኒ ላይ ቢፈስ ስኒው የኩባያውን አቅም ሳይሆን ሌላው ተደፍቶ፣ ስኒ የሚችለውን ብቻ ነው የሚይዘው ማለት ነው። ስኒው የሚይዘው የስኒውን አቅም ብቻ ነው። በመሆኑም ግድቡ ተሻሻሏል ተብሎ ያመነጫል የተባለውን መጠን በሚዲያ ላይ እንጅ በኤሌክትሪክ መስፈሪያ ወይንም በመብራት አናገኘውም ማለት ነው።
ግድቡ በገንዘብም ማሻሻያ ተደርጎበታል ተብሏል። መጀመርያ ከቻይና ብድር 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን፣ እንዲሁም 3 ቢሊዮን ከሕዝብ የሚሰበሰብና ለመንግስት በጀት በአጠቃላይ 4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር በጀት ተይዞለት ነበር። የስም፣ የይዘትና ሌሎችም ለውጦች ተደርገውበታል በተባለበት ወቅት በጀቱ ወደ 6 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር እንዳደገ ተነግሯል። በዚህ በተለወጠ፣ በተቀያየረ፣ ተሻሻለ በተባለ አህዝ ሁሉ ግድቡ አሁንም “60 ምናምን ፐርሰንት ተጠናቅቋል” እንጅ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቋል የሚል ዜና ከተስፋ ያለፈ አይደለም። ያልተሻሻለው ነገር “በ10 በመቶ፣ 15 በመቶ፣ 30 በመቶ……60 በመቶ… …ተጠናቅቋል” እየተባለ ባልተጠናቀቀ ቁጥር እንዳለቀ የሚገለፅበት በተስፋ የማጠናቀቅ የህልም ሪፖርት ብቻ ነው።
የግድቡ እቅድ ይፋ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ፣ ይህ ግድብ የኢትዮጵያ ብዙ ነገር ተደርጎ ሲወራ ቆይቷል። በርከት ያሉ የ”አምስት አመት” እቅዶች በወረቀትና ስልጣን ላይ ባሉት ባለጊዜዎች ኪስ ባክኖ ፕሮጀክቶቹ መና ቀርተዋል። 150 ሚሊዮን ዶላር የተመደበለት ስኳር ፋብሪካ በአምስት አመቱ እቅድ መና ቀርቶ፣ በቀጣዩ “የእቅድ አመት” ተመሳሳይ በጀት ተመድቦለት መና ቀርቷል። አዲሱ አምስት አመት በጀት ሲጀመር፣ ባለፈው መና ከቀረውና ወጣይ ከሚበጀተው በተጨማሪ አዲሱ በጀት ከመመደቡ በፊት ያለፈው አምስት አመት እቅድ ግምገማ እየተባለ በ”ጥናት” ስም በርካታ የሀገር ሀብት በገዥዎቹና በአካባቢያቸው በሚገኙ አካላት ኪስ ገብቷል።
እነዚህ የአምስት አመት እቅዶች ከከሸፉ በኋላ ኢህአዴግ እንደማካካሻ የወሰደው ግድቡን እቅድ፣ ፕሮጀክት፣ ለኢትዮጵያ እንደ አንድ ግድብ ሳይሆን የ”መካከለኛ ገቢ” መሰለፊያ ቁልፍ አድርጎ ነው። ግድቡ በዋነኝነት የአረቡን አብዮት ያስደነገጠው ትህነግ/ኢህአዴግ አጀንዳ ማስቀየሻ እንደነበር ግልፅ ነው። በዚህ የፖለቲካ አላማ፣ ያለፉት እቅዶች ማካካሻ ተደርጎ የተጋነነ ፕሮፖጋንዳ ሲደረግለት የነበረው ይህ ግድብ ስም ከእናቶች መቀነት ሳይቀር በርካታ ገንዘብ ተሰብስቦበታል። የግድቡ ጉዳይ እንደተባለው ገንዘብ የሚወሰን አልነበረምና በተባለው ጊዜ እንዲጠናቀቅ ማድረግ አልቻለም።
ይህ እንደ ግድብ ሳይሆን መና ለቀሩት እቅዶች ሁሉ ማማካሻ ተደርጎ ይወራለት የነበረው ግድብ በ2013 ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ያሰልፋል ተብሎለት ነበር። ሆኖም አሁን ባለው አካሄድ፣ የፖለቲካ ሁኔታ እና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ግድቡን ለማጠናቀቅ ሌላ አምስት አመት ሊፈጅ ይችላል። የተነገረለትን የኤሌክትሪክ ማመንጨት አቅም ያስገኛል ብንል እንኳ አሁን ባለው የሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ታሪፍ ሲሰላ ግድቡ ሙሉ በሙሉ ከተጠናቀቀ በኋላ በአመት አንድ ቢሊዮን ዶላር ዋጋ የሚያወጣ የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል ብለዋል! ግድቡ 6ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ወጭ እንደሚወስድ ተገልፆአል። በተባለለት ጊዜ አለመጠናቀቁ፣ ሙስና እና ሌሎች ተደማምረውበት ወጭውን በይፋ ከተነገረው በእጥፍ ሊጨምሩት እንደሚችሉ ግልፅ ነው። በይፋ ፕሮጀክቱ ይጠናቀቅበታል የተባለውን 6 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ወስደን፣ ከፕሮፖጋንዳው ሳንሸራርፍ ያመነጫል የተባለውን ኃይል ያመነጫል ብንል ከእዳ ነፃ ሆኖ ለኢትዮጵያ አንድ ከእዳ ንፁህ ሳንቲም ለማበርከት በትንሹ 6 አመት መጠበቅ አለብን። ይህም ለኢትዮጵያ አንድ ሳንቲም ለማበርከት አስራ አንድ አመት መጠበቅ ይገባናል እንደማለት ነው። ቢያንስ እስከ 2021 ዓም ማለት ነው!
ሆቴሎች፣ የመንግስት ተቋማት፣ ሆስፒታሎች፣ ፋብሪካዎች እና ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛውን የኃይል ፍጆታ ይጠቀማሉ። ሕዝብ እየተመናመነ ካለው የማገዶ እንጨት ወጥቶ ኤሌክትሪክ ኃይል ለመጠቀም የሚገደድበት አጋጣሚ ሰፊ በመሆኑ ተቋማቱን ትተን ሕዝብ የሚጠቀምበትን ብቻ እንመልከት።
የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን ከሚገመተው 107 ሚሊዮን በአምስት አመት ጊዜ ውስጥ ወደ 120 ሚሊዮን እደሚጠጋ ጥናቶች ያመለክታሉ። በትንሹ፣ አንድ ቤተሰብ በአማካይ 5 አባላት ቢኖሩት ግድቡ ይጠናቀቃል በተባለበት አምስት አመታት ውስጥ ኢትዮጵያ 24 ሚሊዮን መብራት ተጠቃሚ ቤተሰብ ይኖራታል። አሁን ባለው የኃይል አቅርቦት መስፈርት ለአንድ ቤተሰብ 4 ኪሎ ዋት ኃይል የሚሰጥ ሲሆን ይህም ማለት በጠቅላላው 96 ሺህ ሜጋ ዋት ኃይል ያስፈልጋል ማለት ነው። ከዚህ አንፃር የሕዝብን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት ታላቅ የተባለውን ግድብ ያክል ኃይል የሚያመነጭ 16 ተጨማሪ ማመንጫዎች ያስፈልጋሉ ማለት ነው። ከተጠቀሰው ሕዝብ ቁጥር መካከል ለግማሹ ብቻ የኃይል አቅርቦት ይሟላ ከተባለ ታላቅ የተባለውን ግድብ ያህል የሚያመነጩ 8፣ ሩብ ሕዝብ ይጠቀም ብንል እንኳ ቢባል 4 ተጨማሪ ማመንጫዎች ያስፈልጋሉ። ትህነግ/ኢህአዴግ ቁጥሩን ለሚያሳንሰው የከተማ ሕዝብ ብቻ እንኳን በብቃት የኤሌክትሪክ ኃይል ይድረስ ቢባል ከአስር አመት በላይ ፕሮፖጋንዳ የተነዛለትን ግድብ ያክል የሚያመነጩ ተጨማሪ ሁለት ማመንጫዎች ያስፈልጋሉ። ይህ ሁሉ ገዥዎቹ ለውጭ ሀገር እንሸጠዋለን የሚሉትን ኃይል ለሕዝብ በቀጥታ ቢደርስ፣ እንዲሁም በቀዳሚነት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚጠቀሙትን ሁሉንም ተቋማት ወደጎን ትተን ነው።
ከለይ ከተጠቀሰው መረዳት እንደምንችለው ዳስ እየተጣለ በዘማቻ ቅስቀሳ የሚደረግለት፣ ዋንጫው አለፈ፣ ዜጎች ጎበኙት የሚባለው ግድብ መገንባቱ አስፈላጊ ቢሆንም ይሰጣል የሚባለው ጥቅም ከሚገባው በላይ የተጋነነ ነው። ዝርዝር መረጃዎቹ እና ገዥዎቹ በተስፋ የሚነግሩን የግድቡ አራምባና ቆቦዎች ናቸው። ምን አልባትም ስለ ግድቡ የሚደረጉ ዝግጅቶች፣ መስርያ ቤቶች ሰራተኞቻቸውን ወደ ግድቡ በመውሰድ ከሚያጠፉት ወጭ፣ ለሚዲያ ፍጆታ፣ ስብሰባ፣… …ከሚወጡት ወጭዎች እንዲሁም በግድቡ ስም ከሚሰበሰበው ገንዘብ አንፃር ሲታይ ግንባታው በርካታ ወጭዎች የወጡበት ሆኖ እናገኘዋለን። ይጠናቀቃል የተባለበትን ጊዜ፣ ግድቡ የተጀመረበት ምክንያት እንዲሁም ያለ እቅድ ከመጀመሩ የተነሰ በየጊዜው ያለ በቂ ምክንያት የተቀያዩሩት የግድቡ ሁኔታዎችን የሚያመለክቱት የግድቡ ግንባታ ከምህንድስናው ይልቅ የትህነግ/ኢህአዴግ በተስፋ የመግዛት ስልትን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።