የጋሸ መስፍንን ፅሁፍ አንብቤ ስጨርስ ባለፈው ቅዳሜ አዲስአበባ ላይ የወጣችው ውይይት መፅሄት ላይ የወጣውን አንድ መጣጥፍ አስታወሰኝ። መጣጥፉ ዶክተር ቴዎድሮስ የሚባል ምሁር ስለ አማራ ጉዳይ የፃፈው በጣም ተነባቢ ፅሁፍ ነው። አንብቤ ስጨርስ ለደራሲው የተሰማኝን ለመግለፅ የኢሜይል መልእክት ከተብኩ። እንዲህ በማለት፣
“ውይይት መፅሄት ላይ የአማራውን ጉዳይ በተመለከተ የፃፍከውን አንብቤ ይህን መልእክት ልፅፍልህ አነሳሳኝ። የተዋጣለት ፅሁፍ ነው ያቀረብከው፣ ሆኖም ያላነሳሃቸው፣ ምናልባት ወደፊት መዳሰስ የምትፈልጋቸው ጉዳዪች ይሆናሉ። ፅሁፍህን አንብቤ ስጨርስ ከመጡልኝ ጥያቄዎች መሃል፣
1) ከፕሮፌሰር አስራት መአህድ ጀምሮ ዛሬ በዳያስፖራ እስከሚገኙት 10 ያህል የአማራ ድርጅቶች ድረስ፣ በአማራነት መሰባሰብ ለምን ያልሰራ ይመስልሃል? የአማራው ቀዳሚ ማንነቱ ኢትዮጵያዊነቱ ከመሆኑ አኳያ፣ በሁለተኛ ማንነቱ ማደራጀት ከባድ ስለሆነ ይሆን?
2) በኢህአፓና ኢህዴን የትጥቅ ትግል አመታት የአማርኛ ተናጋሪውን የጎንደርና ወሎ ገጠሮች ለ10 ዓመታት የማየት ዕድል ነበረኝ ። መንደሮቹ፣ ተሬዎቹ፣ ወንዞቹ መጠሪያቸው በአብዛኛው አማርኛ አይደለም። ለምሳሌ ጨር፣ አጨር፣ ምጫራ፣ ዞዝ፣ ተከዜ፣ ወዘተ እያለ የብዙ መቶ ቀበሌዎችንና ወንዞችን ስም ልዘረዝርልህ እችላለሁ። ይህ ለምን ሆነ ብዬ በጉዳዩ ላይ ሳስብ የመጣልኝ፣ ምናልባት ይህ ህዝብና መሬት አማራ ተናጋሪ ከመሆኑ በፊት ሌላ ቋንቋ ተናጋሪ ነበርን የሚል ጥያቄ አጭሮብኛል።
ብዙዎቹን ቃሎች ስታያቸው ደግሞ ጨ፣ ዘ ሆሄዎች አሉባቸው። ለምን? ምናልባት ይህ ህዝብ አገው የነበረ ይሆን? ከአማራ ሳይንት ውጪ ያለው አማራ እንዴት አማርኛ ተናጋሪ ሆነ? መቼ ሆነ? ኦሮሞዎች ሲስፋፉ የተጠቀሙበትን ዓይነት ኦሮሙማ ወይም ኦሮሞ የማድረግ ታሪክ አማራው ስለሌለው (ቢያንስ በፅሁፍ ከትቦ ያስቀረልን የአባ ባህረይን መሰል ምሁር ስላልነበርም ሆነ) በአማራው ትውፊት ውስጥ ስላላገኘን፣ የአማራው ህዝብ መስፋፋት ጉዳይ ግልፅ አይደለም ። እንደ ኦሮሞው ለከብቶቹ ግጦሽና ውሃ ፍለጋ የመስፋፋት ታሪክ የለውም። የራሴን መላምት ላስቀምጥ ።
መቼና እንዴት እንደሆን ባላውቅም የአማራው መስፋፋት የኢትዮጵያ መንግስታዊ ሥርአት አማርኛን ከመቀበል ጋር የተዛመደ እንዳይሆን ፍርሃት ይሁን ግምት አለኝ። ከመንግስታዊ ሥርአቱ ጋር የተነካካ ወይም ስርአቱን ወዶ የተቀበለ ሁሉ አማራ የሚሆንበት ሂደት ተፈጥሮ እንደሆንስ ብዬ አስጠነቅራለሁ። ምናልባትም ለዚህ ይሆናል ከወሎ እስከ ጎጃም ያለው ምናልባት ቀድሞ አገው ወይም ሌላ የነበረ ህዝብ አማርኛ ተናጋሪ የሆነው። የመንደሮቹንና ወንዞቹን ስም ለመቀየርም አስፈላጊ ሆኖ ያላገኘው። ለዚህም ይሆናል አማርኛ ተናጋሪው ራሱን ከመንግስታዊ ሥርአቱ ነጥሎ የማያየው። ለዚህም ይሆናል ቀዳሚ ማንነቱ የመንግስታዊ ሥርአቱ ርእዮተዓለም ኢትዮጵያዊነቱ የሆነው ። ለዚህም ይሆናል በአማራነት የመሰባሰብ ጉዳይ ሲነሳለት “ኢትዮጵያን ለማን ትቼ” የሚለው።
ሰፋ አድርገህ ብታየውና ብትመራመረው በሚል ነው እነዚህን ያነሳሁልህ ። ጥናት አድርጌ ሳይሆን ከህዝቡ ጋር አብሮ በገጠር ከመኖር የቀሰምኩት ስለሆነ፣ “የተምታታበት ሽማግሌ” ብለህ ንቀህ አትተወውም ብዬ አሳባለሁ። ቸር ይግጠመን።”
የጋሼ መስፍንን ፅሁፍ ደግሞ እዩት። ባለፈው ሳምንት የአማራ ድርጅቶች ነን የሚሉ ሁሉ በጋራ ተሰባስበው ከመከሩ በሁዋላ፣ ትግሉን መልክ ለማስያዝ ስለተማማሉ እንደ ቀድሞው የማይስማማቸውን ሃሳብና አመንጪውን ሁሉ ከአማርኛ ተናጋሪው ህዝብ ጨዋነትና ባህል በራቀ መንገድ የሚዘልፉበትና የሚያዋርዱበት አስከፊ ተግባር ይቆማል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ሃሳብን በሃሳብ እንጂ በስድብ ወይም እንደ ወያኔ በዱላ መዠለጡን ብናቆም መልካም ነው ። መልካም ንባብ!
https://ethiopianege.com/archives/5376