ያኔ የዛሬ 43 ወይም 44 ዓመት ወጣትነታችሁንና ልጅነታችሁን ለመሰዋት ወደ ትግል የገባችሁበትን ዘመን መለስ ብላችሁ አስቡት እስኪ።
ትግራይን ነፃ ለማውጣት(ከኢትዮጵያ ለመገንጠል)አልነበር? ዛሬም ስማችሁን አልቀየራችሁም አላማችሁን ግን እንጃ፣ ህዝባችን ተበድሏል ብላችሁ ያሰባችሁለትን የትግራይ ህዝብ ፍትህና እኩልነት ለማጎናፀፍ እና በሌሎች በርካታ ብሶቶች እንደሆነ ብዙ ግዜ ነግራችሁን ነበር።
በሂደት መንግስት ለመመስረት የኢትዮጵያ ህዝብን ነው የምንወክለው ብላችሁ 3 ደርጅቶችን ፈጠራችሁ። ብዙውን ታሪክ ልዝለለውና ልነግራችሁ ወዳሰብኩት ነጥብ ላተኩር ።
አዲስ አበባን ስትቆጣጠሩ የተናገራችሁትን በወቅቱ ትንሽ ልጅ ብሆንም ፈፅሞ አልረሳውም
የዘመናት ብሶት የወለደው ጀግናው የኢህአዴግ ሰራዊትደርግ ሲጠቀምበት የኖረውን የአዲስ አበባውን ሬዲዮ ጣቢያ ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ተቊጣጥሮታል። ጉምቦት 20 ሺዘጠኝ ሞቶ 83 ዓ.ም.
ይህን መልዕክት ከጠዋት ጀምሮ እስከማታ ስለሰማሁት የድምፁ ቅላፄ ሳይቀር ዛሬም ድረስ ይሰማኛል።
የዘመናት ብሶት ያላችሁን የ17 ዓመቱን የደርግ አገዛዝ ዘመን ነበር። እናንተ ስልጣን ላይ ከወጣችሁ 27 አመት ሊሆናችሁ ነው።
ደርግ አትናገሩ አትተቹ እርምጃ እወስዳለሁ ስላለ ደፍሮ የሚናገር አልነበረም።
እናንተ ደሞ ዴሞክራሲያዊ መብታችሁ ነው እንደልባችሁ ተናገሩ ብላችሁ ነፃነትን አስለመዳችሁን። ይኸው ዛሬ ዝም በሉ ብትሉንም ዝም ማለት አልቻልንም።
መንግስት የሚቀያየረው በምርጫ ነው ብላችሁ ምርጫ አሳጥታችሁን ብቻችሁን 27 ዓመት መራችሁን ( ገዛችሁን)
እናም ዛሬ ብዙ እጥፍ ብሶት የወለደው ትውልድ አፈራችሁ።
በፈጣሪ አስቡት እስኪ “ብሶት የወለደው “ብሎ ስልጣን ላይ የወጣ ሌላ “ብሶት የወለደው” እስኪጥለው ይጠብቃል???
ዛሬ በዚህ እድሜያችሁ እየተዋጋችሁ ያላችሁት የያኔውን ወጣትነታችሁን ነው።
ዛሬ በዚህ እድሜያችሁ እየተዋጋችሁ ያላችሁት የያኔውን ልጅነታችሁን ነው።
ዛሬ በዚህ እድሜያችሁ እየተዋጋችሁ ያላችሁት የያኔውን ታጋይነታችሁን ነው።
ግፈኛ ካላችሁት በላይ ግፍ፤ ጨቋኝ ካላችሁት በላይ ጨቋኝ የመሆን እቅድ ይዛችሁ አልተነሳችሁም ነበር። አሁን ግን ምን እየሰራችሁ ነው? የያኔውን የትግል አላማችሁንስ አሳክተናል ብላችሁ ታስባላችሁ? አሸናፊስ ናችሁ???
በእርግጥ ባለስልጣን ናችሁ አሸናፊ ናችሁ ለማለት ግን ይከብደኛል።
የትግራይ ህዝብስ በእናንተ አርፏል? ??
ብዙ ጊዜ የተናገራችሁለትስ የዴሞክራሲ ስርዓት ሰፍኗል???
የማይተገበር ተስፋ ለምን ሰጣችሁን?
ለማይለወጥ መንግስትስት በይስሙላ ምርጫ ስንት ብጥብጥና ትርምስ ተፈጠረ? ስንት የሀገር ሀብት ወደመ!!
እያለቀ ያለውንና ያለቀውንስ ዜጋ ቁጥር ታውቁታላችሁ???
ሌላ የሰማዕታት ኃውልት ይቁምስ ቢባል በመላ ኢትዮጵያ ስንት ኃውልት ሊቆም ነው?
ይሄ ጉዳይስ እስከመቼ ነው የሚዘልቀው?
ቆይ ምንድነው የህይወት ግባችሁ?
መቼ ነው የምትረኩት?
ምንድነው ፍርሃታችሁ?
ለምንድን ነው ትዉልዱን ተመልካች ብቻ እንዲሆን የበየናችሁበት???
በትውልዱ የማታምኑትስ እስከመቼ ነው?
ኡፍፍፍ ምን እንደምል ግራ ገባኝ።
አሁንም መፍትሄው ያለው እጃችሁ ላይ ነው።
የሰራችሁልንን መልካም ስራዎችና ልማት አይተን እንዳናመሰግናችሁ ብሶት ጋርዶናል።
ህዝባችን በዘር ተከፋፍሎ እርስ በእርስ እየተወነጃጀለና እየተጫረሰ ነው።
እባካችሁ ሰላምና እርቅ እንዲሰፍን፤
ሀገራችን ከመበታተን እንድትድን የያዛችሁትን ግትር አቋም ቀይሩ።
ኢትዮጵያ እኮ የሁላችንም ናት። የህዝቡን ታጋሽነትና የመገዛት ብቃት አክብሩለት እንጂ እራሩለት።
እግዚአብሔር አምላክ ለሁላችንም ልብ ይስጠን።