ፕሮፍ. መስፍን ለሰዳቢዎቻቸው ምላሽ ሰጡ

ፕሮፍ. መስፍን ለሰዳቢዎቻቸው ምላሽ ሰጡ

ብልግና ከደንቆሮነት ደንቆሮነት ከብልግና ይወለዳል፤ አነዚህ ሰሞኑን የሚንጫጩት ዱሮ አሳዳጊ የበደላቸው ሲባሉ የነበሩ ዛሬ ግን አሳዳጊያቸውን የበደሉ በማያውቁት ነገር ሁሉ ከልክ ያለፈ ኩራት የሚሰማቸው ናቸው፤ እውቀት በየመንገዱ ወድቆ የሚለቃቀም ነገር ይመስላቸዋል፤ እውነት በጫጫታና በማደናበር የሚተከል ይመስላቸዋል፤ እንደዚህ ዓይነቶቹን አንድ ጊዜ አንድ መምህር በቲቪ ሲናገር ፊደላውያን ሲላቸው ሰምቻለሁ፤ ፊደልን በመከራ ተምረው ትምህርት የሚባል ነገር የጨረሱ የሚመስላቸው ናቸው፤ ያሳዝናሉ፤ የወደፊትዋ ኢትዮጵያ ይበልጥ ታሳዝናለች፤ ሆኖም በነዚህ ሰዎች ተስፋ አልቆርጥም! የእነሱው ዓይነት ሰዎች ወይ በገንዘብ፣ ወይ በዱላ ያስተምሯቸዋል፤ ትምህርት የሚገባቸው በነዚያ መንገዶች ብቻ ነው! ወያኔ ሲዘለዝላቸው መቼ ይናገራሉ፤ ምን አፍ አላቸው!

ለእውቀትና ለእውነት ደንታ የሌላቸው ሰዎች መሆናቸውን፣ ሌላው ቀርቶ የተጻፈውን እንኳን በትክክል ሳያነቡና ሳይገባቸው እንደየበር ላይ ውሻ የሚጮሁ መሆናቸውን ለማሳየት ሁለት ማስረጃዎችን አቀርባለሁ፤ አንደኛ አማራ የለም አላልሁም የትም ቦታ አላልሁም፤ ያልሁት አማራ የሚባል ጎሣ የለም ነው፤ በዚህ ትርጉሙ ድርጅቶች ተቋቁመው ሲፈልጉት ሁለት ዓመታቸው ነው፤ ገና አላገኙትም፤ አማራ የሚለውን ቃልም ሆነ ጎሣ የሚለውን ቃል በትክክል የማያውቁት ፊደላውያን ጩኸታቸው የብዙ ሰዎችን ጆሮ ስለጎዳ ለማብራራት ወሰንሁ፤ የኔ የግል አስተያየት እንዳልሆነም ለማሳየት ታላላቅ ሊቃውንትን በአስረጂነት ደርድሬ ነበር፤ ስሕተቴ ሊቃውንቱን ከድንጋይ ራሶች ጋር ለማስተዋወቅ መሞከሬ ነው፤ አይለምደኝም፤ የለመዳችኋቸው እንደለመዳችሁት ያስተምሯችኋል፡፡

ሁለተኛ፣ አማራ ለሚለው ቃል ትክክለኛ ትርጉም ለመስጠት አልሞከርሁም፤ ግን ሊቃውንቱ ከጻፉት ውስጥ ይነበብ ነበር፤ ከድንጋይ ራሶቹ አንድም የተጠቀሱትን አንብቦ የተረዳ የለም፤ ያሳዝናል፤ የአማራን ትክክለኛ ትርጉም ለመቀስቀስ የዞረባቸው የወያኔ ከድሬዎች ሥራ የጀመሩ ይመስላል፤ እስላም ጠቀላይ ሚኒስትር ሊሆን ነው እየተባለ ይወራል፤ ይኸ ወሬ አማራን ሊቀሰቅስ የሚችለው እስላም አማራ ሳይባል፣ አማራ ጎሣ ሳይባል ነበር!

ፕሮፍ. መስፍን ወልደማርያም ስድብና ውዝግብ ያስነሳባቸዉን ፅሁፍ  ለማንበብ ይህንን ይጫኑ ፡ –

የአማራ ጉዳይ /ፕሮፍ. መስፍን ወልደ ማርያም/

LEAVE A REPLY