/ዳንኤል አበራ/
“ኦሮምኛን በግዕዝ በዐማራ ክልል” በተሰኘ ርዕስ በዋናነት ለፕ/ት ገዱ፣ ለኛ በግልባጭ አራት ጦማሮች በተከታታይ አድርሳችሁናል። ከአራቱ ተሽሎ ያየሁት የፕ/ት ግርማን ነው ትህትና የተላበሰ ጦማር ነው። አራተኛው ጦር-አውርዱ፣ ኑና እንያችሁ ፉከራው ሲበዛ አጭር መልስ እና ትክክለኛውን መንገድ ለመጠቆም ተከስቻለሁ።
1. ትዛዛዊ ጥያቄአችሁ “ኦሮምኛን በግዕዝ በዐማራ ክልል” ድርብርብ ችግር የነበረው፤ ያለው፤ የሚያስከትል ስለኾነ ፕ/ት ገዱ እና የዐማራ ክልል ከተናጠላዊ እርምጃ እንዲታቀቡ እጠይቃለሁ።
2. በኢትዮጵያ የቅርብ 25 ዐመት ታሪክ የቋንቋ ጉዳይ ደም አፋሳሽ ንብረት አውዳሚ ነው፤ ለምሳሌ ከደቡብ ወጋጎዳ እንዲሁም የምሁራኑ ደብዳቤ አይግለፀው እንጂ በምሁራኑ የተጠቀሰው የ1990 የዐማራ ክልል ጥናት በጎንደር ደም እንዳፋሰሰ መዘንጋት የለበትም። ስለኾነም ክልሉ ከተናጠላዊ ተግባራዊ እርምጃ እንዲታቀብ እማፀናለኹ።
3. በኢትዮጵያ የቋንቋ አጠቃቀም ጉዳይ ውስብስብ ስለኾነ፤ የቋንቋ አጠቃቀም የክልል የውስጥ ጉዳይ ብቻ ስላልኾነ፤ ጦማር የላኩትን ምሑራኑንም ኾነ ፕ/ት ግርማን አመስግነን፤ ኦሮምኛን በዐማራ ክልል ኾነ ሌላው የቋንቋን ጉዳይ፤ ያለንን ቸግር ለመፍታት ኾነ ወደፊት ለሚፈጠሩት በተጠና ሁኔታ መፍትሔ ለመስጠት የምንችለው በሐገራዊ እንቅስቃሴ ብቻ ነው።
4. ሐገራዊ እንቅስቃሴ ስል የቋንቋ ፖሊሲን የሚያሻሽል፤ የቋንቋ አጠቃቀም ዕቅድን የሚነድፍ፤ የቋንቋ አጠቃቀም ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌን የሚተነተን ነው።
5. አኹን ባለው ኹኔታ ይህንን በዕውቀት፣ በተማከለ መንገድ አስፈፃሚ አካል የለም።
6. ሐገሪቱዋም ክልሎችም ከአላስፈላጊ መጓተት አጓጉል ምክር ከመተግበር፣ ከአጓጉል ጥናት እንዲድኑ አሁን ባለቤት እና አቅም አልባውን የኢትዮጵያ የቋንቋዎች አካዳሚን (የኢትዮጵያ የቋንቋዎች ጥናት ማዕከልን) እንደ አስፈፃሚ አማካሪ አካል በሚኒስተር መስሪያ ቤት ደረጃ በአስቸኳይ አዋቅሮ መንቀሳቀስ ግድ ይላል።