ዛሬን በእስር ቤት —ከእነ እስኬው ጋር…. /ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ/

ዛሬን በእስር ቤት —ከእነ እስኬው ጋር…. /ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ/

ዛሬ ቀትር ላይ እስክንድር ነጋን፣ አንዷለም አራጌን፣ ተመስገን ደሳለኝን፣ በፍቃዱ ሃይሉን፣ ዘላለም ወቅቃገኘሁን፣ ተፈራ ተስፋዬን፣ ይድነቃቸው አዲሱን፣ አዲሱ ጌታነህ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ ማህሌት ፋንታሁንና ወይንሸት ሞላን ጎተራ ፔፕሲ ፋብሪካ አከባቢ በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ጠይቀናቸው ነበር – ከግርማ ሰይፉ ጋር፡፡

ፖሊስ ጣቢያው ሰፊና የበዙ ቢሮዎች ቢኖሩትም፣ እስረኞችን ለመጠየቅ ግን ትንሽ ዙሪያ ጥምጥም ያስኬዳል፡፡

እነእስክንድርን ለመጠየቅ ሶስት ቅያሶችን ዞረን አንድ ተለቅ ያለ ቢሮ ፊት ለፊት ቆምን፡፡ በአከባቢው ፖሊሶች ጥንድ ጥንድ በመሆንና ፈንጠር ፈንጠር በማለት ቆመዋል፡፡ አንዱ ፖሊስ ‹‹በመስኮት በኩል ጠይቋቸው›› አለን፡፡ እነእስክንድርን፣ የመጀመሪያው እሁድ ዕለት፣ ከ90 ሰዎች ጋር ከታሰሩበት ክፍል ለይተው በማውጣት፤ ከትናንት ጀምሮ ለብቻቸው በአንድ ቢሮ ክፍል ውስጥ አዘዋውረዋቸዋል፡፡ በቅድሚያም በጠባብ የመስታወት መስኮት ብቅ ብሎ ያየን ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ነው፡፡ እየሳቀ ሰላም አለን፡፡ አንዷለም ተከተለ፡፡

ወዲያው ሁለቱንም በቁመት የሚበልጠው እስክንድር ከጀርባቸው ብቅ አለ፡፡ ሁሉም ላይ ነጻነት፣ ፈገግታና ትህትና በጉልህ ይታያል፡፡ ዘላለም፣ ተፈራ፣ በፍቃዱም መጡ፡፡ …ሁሉንም በየተራ ሰላም አልናቸው፡፡

ክፍሉ ሰፋ ያለ ቢመስለልም መስኮቷ ጥቂት ሰዎችን ብቻ ነበር ማነጋገር የምታስችለው፡፡ በቻልነው መጠን ከሁሉም ጋር መጠነኛ ንግግር ለማድረግ ችለናል፡፡ ‹‹የመጀመሪያው ቀን አዳር አዳር አይባልም፤ ይዘገንናል፡፡›› ሲል አንዷለም ነገረን፡፡ ‹‹እሁድ ሌሊት ትንሽ ማረፍ የቻልኩት እኔ ብቻ ነበርኩ – ወገቤን ስለሚያመኝ፡፡ አሁን ከዚያ የተሻለ የቢሮ ክፍል ሰጥተውናል፡፡›› ሲል ተመስገን አከለ፡፡ ‹‹አሁን የወገብ ህመምህ እንዴት ነው?›› በማለት ጠየኩት፡፡ ‹‹ማስታገሻ መድሃኒት እየዋሰድኩ እገኛለሁ፡፡ በተረፈ እስኬውና በፍቄ እያሹኝ ነው፡፡›› በማለት በፈገግታ መለሰልኝ፡፡

‹‹ምን አዲስ ነገር አለ? ምንስ የመረጃ ዜና አለ?›› በማለት የጠየቀው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ነበር፡፡ ባለን መረጃ መጠን በጥቂቱ ነገርነው፡፡ በፍቄም ‹‹ተመላላሽ እስረኛ ሆንኩ አይደለ? …›› በማለት እየሳቀ አወራኝ፡፡ ….በመሃል ሌሎች ጠያቂዎች መጥተው ቦታውን ያዙት፡፡ እስኪጨርሱ ጠበቅናቸው፡፡

‹‹በእናንተ በኩል ምን አዲስ ነገር አለ? ምንስ ተባላችሁ?›› በማለት ጥያቄ አቀረብኩላቸው፡፡ ቃል አለመስጠታቸውን፣ ጠበቃ አምሃ መኮንን መጥቶ እንዳነጋገራቸው፣ መርማሪያቸውም የፍቺ ተስፋ መኖሩን እንደነገራቸው …ወዘተ ተመስገንና አንዷለም በየተራ አስረዱን፡፡ ተመስገን ግን ‹‹እዚህ በሌላ ክፍል፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከ80 በላይ እስረኞች ከኦሮሚያ ክልል መጥተው ታስረዋል፡፡ ተስፋ የሚሰጡን ግንእንዲሁ ለማዘናጋት ይመስለኛል፡፡..›› የሚል ሃሳቡን ሰነዘረ፡፡

አንዷለምም፣ ‹‹ገና ከረዥም ዓመት እስር በኋላ ተፈትተን በቅጡ ሳናርፍ፣ በአጋጣሚ በሥጦታ ፕሮግራም ላይ ዳግም እኛን ማሰራቸው ምን እንደሚጠቅማቸው አላውቅም፡፡ …›› አለ፡፡ …እስክንድር፣ ብዙ አልተናገረም፤ ቦታውም አመቺ አልነበረምና፡፡ ነገር ግን ‹‹መጽሐፍ አምጡልን፡፡ …ሰርኬንም አይዞሽ በላት፡፡›› ሲል በእነዚያ ርሩህሩህና ንቁ አይኖቹ ጭምር መልዕክቱን ነገረኝ፡፡

ፖሊሱም ‹‹በቃችሁ›› የሚል ቃል ተነፈሰ፡፡ ከዚህ በላይ መዝለቅ አልቻልምና እንመጣለን በማለት ሁሉንም ተሰናብተናቸው ወጣን፡፡

የሴቶች መጠየቂያ ቦታን ደረስን፡፡ በዚህ ጊዜ ጠበቃ ወንድሙ ኢብሳ ለጥየቃ ሲገቡ አገኘናቸው፡፡ ‹‹ሴት እስረኞች የሚጠየቁት በዚህ በመስኮት ነው፡፡›› ሲሉ ፖሊሶች ጥቁምታ ሰጡን፡፡ በተባለው መስኮት ስንደርስ፣ ማሂና ወይንሸት አንዲት ፍራሽ ላይ በጀርባቸው ጋደም ብለው ጣራ ጣራውን እያዩ ያወጉ ነበር፡፡ በመስኮት ሲያዩን ተነስተው መጡ፡፡ ከእነርሱም ጋር ስለነበረው ነገር፣ ስለቀጣይ ሁኔታ ግምት በመጠኑ ቢሆን ተጨዋወትን፡፡ ከእነርሱ ጋር አምስት ሌሎች ሴቶች አብረዋቸው አሉ፡፡ በሌላ ጉዳይ የተያዙ ናቸው፡፡ ጠበቃ ወንድሙም ከማሂ ጋር እየተቀላለዱ አወጉ፡፡ …ተረኛዋ ፖሊስ ብዙም እንድንቆይ አለፈለገችም፡፡ ‹‹ይበቃችኋል›› አለች፡፡ …‹‹አይዟችሁ›› ብለን ተሰናብታቸው ወጣን፡፡ …ይኼው ነው!

…አይ የኢትዮጵያ አገዛዝ ሁነት! ….በግፍ ማሰር! መፈታት! ማሰር! መፈታት! …ይኼ እኩይ አዙሪት፤ የሚቆምበት ዕለት እና ዘመንን ላይ ከነፍሴ እሻለሁ!
…ግን ፍቷቸው!

LEAVE A REPLY