በኢትዮጵያ የዘር ፖለቲካና አመራር ለሃያ ሰባት ዓመት ከሽፏል። ክሽፈቱ የሃገሪቱን ፖለቲካና ኢኮኖሚ ለቀውስ ዳርጓል። ስርዓቱ በማህበረሰቡ፤ በግለሰቦች እና በተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ላይ በተናጥልም ይሁን በወል ወደር የሌለው በደል፤ ሰቆቃና ግፍ ፈፅሟል። የጎሳ ፖለቲካ በሕዝብ ዘንድ ተጠልቷል። ተቃዋሚውም ሆነ ምሁሩ አውግዞታል። ሕዝብ የዘር ፖለቲካ እንዲቀየር በጨዋነት፤ በፈሪሃ እግዚአብሔርና በትዕግስት ለሰላሳ ዓመት ለመንግሥትን ሲምከር ቆይቷል።
መንግሥት ለወጥ በማሳየት ፋንታ ባለበት መሄድን መርጧል። የሚገርመው የመንግሥት አመራር አካላት ስርዓታቸው መበስበሱን ለሕዝብ ያሳውቁ እንጅ ለውጥን እንደሬት ተፀይፈውታል። ለሁሉም ጊዜ አለው እንዲሉ የሕዝቡ ትእግስት አለቀና እሹሩሩ በቃ አለ። ብሶት አሸንፎት ተቃውሞውን በይፋ አሰማ። ወዶ ካልተቀየር እኛ እንቀይረዋለን ብሎ በንቂስ ተንሳ። ሕዝቡ ላረጀ ላፈጅ ስርዓት አልገዛም አለ። የማይደፈረው ሃይል ተደፈረ። ፌድርሊዝምን እና የጎሳ ፖለቲካን መፀይፍ ብቻ አይደለም ውጉዝ ከማሪዎስ ብሎ ኮነነው። የዓለም ማህበረሰብም ተቃውሞውን ጀመረ። የምእራቡ ዓለም የኢሃዴግ ስርዓት ለሃገሪቱ መፍትሔ ሊአመጣ ይችላል ብሎ እንደማያማን በይፋ ተናገረ።
ሕዝብና መንግሥት ሲጣሉ ሃገር በማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ መግባት ግድ ነው። በኢትዮጵያም ከቀውሱ መውጫ ቀዳዳ በጠፋበት ወቅት ለውጥ ፈላጊ የሆኑ የጎበዝ አለቆች ከስርዓቱ ውስጥ ተወልዱ። ይህ የለውጥ ፈላጊው ሃይል የህዝቡን ጥያቄ ማስተጋባት ጀመረ። እነ ለማ፤ ዓቢይ እና ገዱን የመሰሉ በይፋ ወጠው ሕዝቡን ተቀላቀሉ። ከትቂት ወራት በፊት ኦሮሞውና ዓማራው በባሕር ዳር ተገናኝተው በአንድነት ለመስራት ወስነዋል። የጎሳ ፖለቲካን ተፀይፈው ኢትዮጵያዊነትን መርህ አድርገው ለመስራት ለራሳቸውና ለሕዝባቸው ቃል ገብተዋል። በተለይ ለማ፤ ገዱ እና ዓብይ ይህን ማድረግ በመቻላቻው ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ነቀርሳ የሆነውን የዘር ፖለቲካ ስርዓት አከርካሪውን ሰበሩት። የሕዝቡን ጥያቄም በከፊልም ቢሆን መመለስ ጀመሩ። ሲፈራ የነበረውን ግንብ አፍርሰው የሕዝብን ፍላጎት አውጀዋል። ይህ ከፍተኛ የሆነ የሃስብና የፖለቲካ ልዕልና በመሆኑ በብዛት ተጨብጭቦላቸዋል። በስፊው ሕዝበ ልቦና ውስጥ የነበረው ግን በፍርሃት መነገር ያልተቻለውን በማውጣታቸው የሕዝብና የተቃዋሚን ቀልብ ስበዋል። በተለይ ዓቢይ ያደረጏቸው ሕዝባዊ ንግግሮች፤ ያቀረባቸው ጽሑፎች፤ አዳዲስ ሃሳቦች የሕዝብን ብቻ ሳይሆን የምሁራንን፤ ፖለቲከኞችንና የዓለም ማህበረስበን ቀልብ አስደምመዋል።
ሕውሃት ኢሃዴግ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በከፍተኛ የፖለቲካ፤ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ በመሆኑ እስራት፤ አፈናና ግድያ ተበራከተ። ሕዝባዊ ዓመጽ በሁሉም የሃገሪቱ ክፍለ ሃገራት ተካሄደ። ኢኮኖሚው ደቀቀ። ኑሮ ተወደደ። ስደት ፤ ስራአጥነትና ቦዘኔንት በረከተ። ዶ/ር መረራ ሚበላው ያጣ ሕዝብ መሪውን ይበላል እንዳሉት መሪዎቹን መብላት ጀመረ። ገዢው ቡድን ሃገር ማስተዳደር ተሳነው። የሃሳብ ልዕልና ከማጣቱ የተነሳ የውቅቱን ፖለቲካዊ፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በተሻል ዘዴና ወቅቱን በዋጀ መንፈስ መፍታት አልቻለም።
ሁሉም ባለስልጣን በሙስና ከመዘፍቁ የተነሳ የሕዝብን ብሶትና እሮሮ ማከም አላስቻለውም። የሕዝብ ሃብተ መዝረፍ፤ ሙሰኝነት አስነዋሪ መሆናቸው ቀርቶ የመልካም ስነምግባር መግለጫና ባህል ሆኑ። አመራሩ ችግሮችን መወጣት የሚሞክረው ስህተትን በስህተት በማረም ነው። መፍትሔ ብሎ የያዘው ባለስልጣንን በመቀያየር፤ ተቃዋሚን በማሰርና በምግደል፤ ሕዝብን በማሰቃየት ነው። እንዚህ ዘዴዎች ሁሉ ይተሳሳቱ ናቸው። እነዚህ ሁሉ ስልቶች ችግሩን በሚገባ ለመፍታት ሳይሆን ለይስሙላ የሚደረጉና የጊዜ መግዣ ብሎም የስልጣን ማራዘሚያ ሂደቶች ናቸው። አለባብሰው ቢአርሱ ባረም ይመለሱ ማለት ይህ ነው። ህይለ ማርያም ደሳለኝ በራሱ ፈቃድ ስልጣን እንደለቀቀ አስመስሎ ለማሳየት ተሞከረ። አንድ መንግሥት እዚህ ደረጃ ሲደርስ ሕዝብና ሃገር የመምራት ክህሎቱ አብቅቶለታል ማለት ነው። በሌሎች አገሮች እንደህ ዓይነት መንግሥት ሥልጣኑን ለሕዝብ አስረክቦ እራሱን ያገላል።
በተቃራኒው በኢትዮጵያችን ከብዙ ፍትጊያ በኋላ ዶ/ር ዓቢይ ዓህመድን አዲስ ጠቅላይ ምኒስትር አድርጎ መርጧል። ተቃውሞው የበዛው በኦሮሚያና በዓማራ ክልሎች በመሆኑ ኦረሞውን ጠቅላይ ዓማራውን ምክትል ጠቅላይ አድርጎ ሾመ። ሁልቱ ብሔሮች ከሃገሪቱ ሕዝብ 70% የያዙ በመሆኑ በተራ ዴሞክራሲ ስርዓት ሲታይ አሿሿሙ ትክክል ነው።
ተሿሚው የሃግሪቱን ሁለንተናዊ ችግሮች፤ የቀውሱ መንሲኤዎችን በተለያዩ መድረኮች ባደረጉት ንግግር (messy lectures) አብራርተዋል። ችግሩን ለመፍታት መፍተሄ ያሏቸውን ለምሳሌ እርቀ ሰላም፤ የሽግግር መንግሥት ማቋቋምን፤ የዴሞክራሲ ባህል ማጎልበትን፤ የሕግ የበላይነትን፤ ሰብዓዊ መብት መከበርን፤ ሕገ መንግስቱን እና የዓለም አቀፍ ሕግ ባከበረ መልኩ ኢትዮጵያን ወደ መድበለ ፓርቲ ስርዓት ማሸጋገር እንደሚአስፈልግ በዓፅኖት ሰብከዋል። ይህች ሃገር ሳትበታተን የቆየችው በሕዝቧ አስተዋይነት፤ በሕዝቦች መካከል ባለው የቆየ መቀራረብ፤ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ትስስር እንጅ በኢሃዴግ አፍራሽ አሰራር ከሆነ ሃገሪቱ እስካሁን ፈርሳ ነበር በማለት የሃሳብ ልዕልናቸውን አስመስክረዋል።
ምንጊዜም ችግር የሚፈጠረው ስህተትን በስህተት ለማረም ሲሞከር፤ ባለማዎቅ እና በድንቁርና፤ አውቆ በቸልተኝነትና በማናለብኝነት ለማለፍ ሲሞከር ነው። ችግሩን ማወቅ ወይም መረዳት በራሱ የችግሩን 50% የመቀረፍ ያህል ይቆጠራል። አሁን የአመራሩን መርከብ የተሳፍሩት ዓብይ ችግሩን ከነመፍትሔው ያወቁ፤ የተመራመሩና በጥራት የተናገሩ ናቸው። ከልምድ አንፃርም በቂ ተመክሮ ያላቸው ናቸው።
ከቀደምት የሕውሃት መሪዎች በዕድሜ ወጣት ስለሆኑ በተፈጥሮ ሕግ መሰረት ለውጥ ፈላጊ ናቸው። ስለሆነም ለውጥ ለመስራት ዝግጁ ናቸው ማለት ይቻላል። ባላቸው የተፈጥሮ ፍላጎት እና ባካበቱት ዕውቀትና ልምድ ተመርኩዘው የኢትዮጵያን ሕዝብ አቀራርበው ለሃገሪቱ የሚመጥን መፍትሔ እና አመራር ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በኢሃዴግ ዘመናቸው የፀጥታና ድህንነት መዋቅሩን፤ የመከላከያ ተቋሙን፤ የመረጃና ደህንነት ስርዓቱን በቅርብና በጥለቀት የተረዱ በመሆኑ ሁሉንም ሴራ አሸንፈውና ቀልብሰው ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ይታደጓታል የሚል ተስፍ አለን። ሃገሪቱንም ለሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግር፤ ድርድርና ብሎም ሁሉን አሳታፊ ለሆነ የዴሞክራሲ ስርዓተ ማህበር ሊአብቋት ይችላሉ የሚል ተሳፋ በኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን በዓለም ማህበረሰብ በተልይ በምእራቡ ዓለም መንፈስ ውስጥ ሰርጿል። ቻሉም አልቻሉም ሕውሃት/ኢሃዴግ በምናውቀው መልኩ መቀጠል ከማይችልበት ደረጃ የደረሰ መሆኑ ግን ሊሰመርበት ይገባል።
የሃሳብ ልዕልና ያሳዩት ዓቢይ ያልተሄደበትንና ተፈርቶ የቆየውን ግን ትክክለኛውን ስልት ተከትለው ወንዝ ሊአሻግሩን የሚችሉ ይመስላል። የሚቀጥለው ፌድራላዊ ምርጫ የሚካሄደው ከሁለት ዓመት በሗላ ነው። ዓቢይ ይህን የሁለት ዓመት ዕድሜ ተጠቅመው ወደ ነፃና ፍትሐዊ ብሎም ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሊአሸጋግሩን ይችላሉ።
ቅዱስ መጽሐፍ ኢትዮጵያን አንድ ያልታወቀ ሰው ከስቃይና ከመከራ ያውጣታል ወይም ይታደጋታል ይላል። ዓቢይ የቅዱስ መጽሐፍ አንዱ ሰው የማይሆኑበት አመክኒዮ የለም። ዓቢይ ኢትዮጵያን ወደ ትንሳዔዋ፤ ወደ ቀደሞ አንድነቱዋ፤ አብሮነትዋ፤ ፍቅርዋ ሊመልሷት የሚችሉ መሲሃ ሳይሆኑ አይቀርም።
አሁን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ወንዝ ከፍተኛ ማዕበል የበዛበት ነው። ይህን መዓበል ተቋቁሞ መሻገር ከባድ እንደሚሆን ጥር ጥር የለውም። ይሁን እና ዓቢይ ባላቸው ክህሎት፤ የሃሳብ ልዕልና፤ እውቀትና ተዕግስት ይህን የተረበሸ ወንዝ መሻገር የሚሳናቸው አይሆንም።
ስለዚህ ዓቢይ የወንዝ አሻጋሪው መርከብ ካፕቴን ስለሆኑ ኢትዮጵያን ወደ መድበለ ፓርቲ እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሊአሸጋግር የሚችል የሽግግር ካቢኔ አቋቁመው ሽግግሩን ሊአበስሩ ይገባል። ይህን ለማድረግ እውቀቱ፤ ተመኩረው፤ ልምዱ፤ ወታደራዊ ብቃቱ፤ የደህንነት መረጃ እና የለውጥ ፈላጊ ወጣትነት አላቸውና ታምር የምናይበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም። ይህች ሁለት ዓመት ለዓቢ ካቢኔና ለኢትዮጵያ ሕዝብ የፖለቲካ ሽግግር ወቀት መሆኑን አውቀን እንተባበራቸው። መልካም የሽግግር ዘመን ይሁንልን።
ነን ሶቤ
አቢቹ ነጋ
መጋቢት 29, 2018