/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከሚገኝበት ፖሊስ ጣቢያ ለህክምና ዘውዲቱ ሆስፒታል መግባቱን ቤተሰቦቹ ገለጹ። ጋዜጠኛ ተመስገን ሆስፒታል የገባው ቀድሞ የነበረበት የወገብ ህመም የባሰ ደረጃ ላይ በመድረሱ እንደሆነ ታውቋል። ተመስገን ዛሬ ጠዋት ጤና ጣቢያ ቢሄድም ህመሙ ካቅማቸው በላይ በመሆኑ ወደ ዘውዲቱ ሆስፒታል እንደተወሰደ ታውቋል።
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በቅርቡ እንደተናገረው በዝዋይ እስር ቤት በነበረበት ጊዜ ከፍተኛ በሆነ የጀርባና የጆሮ ህመም ሲሳቃይ መቆየቱን ገልጿል።
ከእስር ቤት ሲወጣም ጆሮውን የተሻለው ቢሆንም የጀርባ ህመሙ ግን እየባሰበት በመሄዱ ውጭ ሀገር ሄዶ ለመታከም ዝግጅት እያደረገ በነበረበት ወቅት ባለፈው እሁድ ጀምሮ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ታዋቂውን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ጨምሮ ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር የሻይ ቡና ፕሮግራም ላይ ሳሉ መታሰራቸው ይታወቃል።
በቦታው የሚገኘው የጋዜጠኛ ተመስገን ዳሳለኝ ወንድም ታሪኩ ደሳለኝ የሚከተለውን መረጃ በፌስ ቡኩ አጋርቷል።
____________
“ ጭንቅ አርግዘን ዘውዲቱ ሆስፒታል ተቀምጠናል
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ለዳግም እስር ከተዳረገ ዛሬ በስድስተኛው ቀን በህመሙ ምክኒያት ሆስፒታል ገብቶል።
ትላንት መጋቢት 20/2010 ዓም
ትላንት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን ስጠይቀው አሁን ያለቡት የእስር ክፍል “ለሰው ሳይሆን ለበግ የሚሆን አይደለም” ብሎኝ ነበር። በሰአቱ ሆኔታው ሳየው የጀርባውና የወገቡ ህመም ክፍኛ እንዳመመው ቢያስታውቅም ምንም እንዳልተፈጠረ አደርጓ አዋርቶኝ ለጀርባ እና ለወገቡ ህመሙ የመጣሁትን ማስታገሻ መዳኒት ሰጥቼ ወደ ቤት ብመለስም ሃሳቤ ግን ተመስገን ጋር ፖሊስ መመሪያ ነበር።
ዛሬ መጋቢት 21/2010 ዓም
ጠዋት እነ ተመስገነን አስጠርቼ ሲመጡ የተመስገን ፊት ልክ እንዳልሆነ አስተዋልኩ። እነ አንዷለምም እጅጉን ታሞ ነው ያደረው አሉኝ። እነሱ አረጋገጡልኝ እንጂ ሁኔታው ያስታውቃል። ህክምና እደሚያስፈለገው ለመምሪያው ሀላፊዎች ለመናገር የመጣነውን ቁርስ ሰጥቻቸው ወጣሁ።
ጠዋት 3:37
በዚህ ስአት በአራት ፖሊሶች ተጅቦ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍል ከተማ የወረዳ 8 እና 9 የሆነው ጤና ጣቢያ ተመስገንን ይዘን ደርስ። ጤና ጣቢያው ህክምናውን ለማድረግ ከሞከረ በኃላ የተመስገን ህመም ከአቅሜ በላይ ነው በማለት እሪፈር ለዘውዲቱ ሆስፒታል ፃፋ ተመስገንን ይዘን ወደ ዘውዲቱ ሆስፒታል ሄድን።
ዘውዲቱ ሆስፒታል ከደረስን ሰአታት ቢያልፈን የተመስገን ህክምና እስካውን አላለቀም እኛም ጭንቅ አርግዘን ዘውዲቱ ሆስፒታል እንገኛለን።
በተመስገን ላይ ለሚደርሰው ነገር ሁሉ መንግስት ሀላፊነቱን ይወስዳል።
ከሰአት 9:03
መጋቢት 21/2010 ዓም”