/ኢትዮጵያ ነገ/፡- ለኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት(ኦህዴድ) የተሰጠው ድርብ ኃላፊነት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ለማ መገርሳ ገለጹ፡፡
ፕሬዚዳንት ለማ ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (ኦ.ቢ.ኤን) ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ የኦህዴድ ሊቀ መንበር ዶክተር አብይ አህመድ በኢህአዴግ ምክር ቤት ለግንባሩ ሊቀመንበርነት መመረጣቸው ለድርጅቱ ድርብ ኃላፊነት እንደተሰጠው ያረጋግጣል ብለዋል።
አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ለመተካትና ሊቀመንበሩን ለመምረጥ የነበረው ትግል ዴሞክራሲያዊና እልህ አስጨራሽ እንደነበር ጠቁመዋል።
አሁን ኦህዴድ የተሰጠው ኃላፊነት የኦሮሞ ህዝብ የረጅም ጊዜ ጥያቄ እንደነበረና ህዝቡ የኦህዴድን አመራር በመተማመን ኃላፊነቱን በመስጠቱም አመስግነዋል።
በአሁኑ ወቅት የኦሮሞ ህዝብ በከፈለው መስዋዕትነት የተሰጠው ድርብ ኃላፊነት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸው፤ ኦህዴድ እና የኦሮሞ ህዝብ የተሰጣቸውን አገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የህዝቡን ጥያቄዎችን ለመመለስ ቃል በገባነው መሰረት የሚያስፈልገውን መሰዋዕትነት ሁሉ በመክፈል እንሰራለንም ብለዋል።
“የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች ብሄሮች ጋር በጋራ በመሆን ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት መስራት እንደሚገባም” ፕሬዚዳንቱ አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።