/ኢትዮጵያ ነገ ዜና /፡- አሜሪካ ወደ ሀገሯ ለመግባት ቪዛ አመልካቾችን የአምስት ዓመታት ማህበራዊ ሚዲያና የእጅ ስልክ መረጃዎችን እንደምትጠይቅ አስታወቀች።
የዶናልድ ትራምፕ አስተዳድር ትናንት እንዳስታወቀው ወደ አሜሪካ ለመግባትና ቋሚ የመኖሪያ ካርድ (greens card) ለማግኘት የሚያመለክቱ ሰዎች እንደ ፌስ ቡክ፣ ኢሜል፣ ስልክ ቁጥርና ሌሎች የሚጠቀሙባቸውን የማህበራዊ ሚዲያ መገናኛዎችን፤ ቪዛ ካመለከቱበት ቀን ወደሗላ አምስት ዓመታት የተለዋወጧቸውን መልዕክቶች ለማሳየት እንደሚገደዱ ተገልጿል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከትናንት አርብ ጀምሮ ለ60 ቀናት በረቂቅ ህጉ ላይ ህዝብ አስተያይት እንዲሰጥበት ክፍት መደረጉም ተገልጿል።
ህጉ ተግባራዊ ከተደረገ ወደ አሜሪካ ለመግባት የሚያመለክቱ ስደተኞችና ጎብኝዎች ላይ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችልና የግለሰቦችን ሚስጥር (privacy) እንደሚጋፋ የተለያዩ አካላት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ህጉ የዲፕሎማት ማህበረሰቡንና ኦፊሴላዊ የመንግስት ባለስልጣናትን እንደማይመለከት ተገልጿል። ለተለያዩ ተግባራት ወደ አሜሪካ ለመግባት የሚያመለክቱ ሰዎች በየዓመቱ ወደ 15 ሚሊዮን እንደሚጠጋም መረጃዎች ጠቁመዋል።
የቪዛ አመልካቾች ከስልክና ከማህበራዊ ሚዲያ በተጨማሪም ቀድሞ ስላደረጉት አለም አቀፍ የጉዞ ሁኔታ እንዲሁም የአመልካች የቤተሰብ አባላት በሽብር ድርጊቶች ውስጥ ተካፋይ መሆን አለመሆናቸውንም ማብራራት እንደሚጠበቅባቸው የተዘጋጀው ረቂቅ ህግ እንደሚደነግግ ተገልጿል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ስደተኞችን በተመለከተ በሚያወጧቸው ህጎች በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ሲተቹ እንዲሁም ከአሜሪካኖች ሳይቀር ከፍተኛ ውግዘት ሲደርስባቸው መቆየቱ ይታወሳል።