የኢህአዴግ ምክር ቤት ዛሬ መግለጫ አውጥቷል

የኢህአዴግ ምክር ቤት ዛሬ መግለጫ አውጥቷል

በመግለጫውም ስልጣን የግል ጥቅም ማሳደጃ መሳሪያ መሆኑን

ሙስና መስፋፋቱን

ጸረ-ዲሚክራሲዊ አስተሳሰብ መስፋፋቱን

በሀገሪቱ ለተፈጠረው ችግር በከፍተኛ አመራሩ ድክመት መከሰቱን

በአንድን ማህበረሰብ ነጥሎ ማጥላላት መኖሩንና ሌሎችንም ችግሮች ጠቅሷል።ሙሉ መግለጫው ቀጥሎ ቀርቧል።

____________________________

ከኢህአዴግ ምክር ቤት የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ

የኢህአዴግ ምክር ቤት ከመጋቢት 11 ቀን እስከ መጋቢት18 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡

በዚህ ስብሰባ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ባቀረባቸው ሁለት ሪፖርቶችና ከድርጅታችን ሊቀ መንበር የስራ መልቀቂያ ጋር በተያያዘ የመተካካት አጀንዳ ላይ ሰፊ ውይይት አካሂዶ ስብሰባውን በመግባባትና በአንድነት መንፈስ አጠናቋል፡፡

ምክር ቤታችን በቅድሚያ የመከረበት አጀንዳ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በታህሳስ ወር ያካሄደውን ግምገማ መነሻ በማድረግና በየብሄራዊ ድርጅቱ የተካሄደውን ራስን ፈትሾ የማስተካከል እንቅስቃሴ ባካተተው ሪፖርት ላይ ነበር፡፡

በዚህ ሪፖርት አገራችን ባለፉት 27 አመታት በተጓዘችበት ሂደት የተመዘገቡ ለውጦች እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ ያጋጠሙን ፈተናዎችና በእጃችን የገቡ መልካም እድሎች በዝርዝር ቀርበው በሰፊው ተመክሮባቸዋል፡፡

ድርጅታችን ኢህአዴግ በየምርጫው የህዝብ ድምፅ አግኝቶ አገር የመምራት ኃላፊነቱን ከተረከበበት ጊዜ ጀምሮ በተካሄዱ ጥረቶች ለማንም ግልፅ እንደሚሆነው በሁሉም የህይወት መስኮች አገራዊ ተስፋችንን ያለመለሙ ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡

ይህ ለውጥ ከምንም ነገር በፊት የጀመረው አገራዊ የዴሞክራሲ ትንሳኤን ያበሰረ ዴሞክራሲያዊ ህገ መንግስት ባለቤቶች በመሆናችንና አቅም በፈቀደ መጠን ይህንኑ ተግባራዊ በማድረግ የዜጎችና የህዝቦች መብትና ተሳትፎ የተከበረበት ሁኔታ በመፈጠሩ ነው፡፡

አገራችን የሁሉንም ህዝቦች ተሳትፎ ባረጋገጠ አኳኋን ባፀደቀችው ህገ መንግስት የዜጎችና የህዝብ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተሟላ እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡

በብዝሃነት በተዋቀረችው አገራችን ውስጥ የዘመናት የህዝቦች ጥያቄ ሆነው የቆዩት የእኩልነት መብቶች ተከብረዋል፡፡

የብሄሮች፣ የኃይማኖቶች፣ የፆታና መሰል የእኩልነት መብቶች ህገ መንግስታዊ እውቅናና ዋስትና ተሰጥቷቸዋል፡፡

አገራችን የብዙ ፍላጎቶችና ጥቅሞች መናሃሪያ መሆኗን በመቀበል የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲገነባ ተደርጓል፡፡

የፖለቲካ ስልጣንም ህዝቡ በምርጫ ከሚሰጠው ድምፅ ብቻ የሚፈልቅ የህዝብ ሉአላዊነት ማረጋገጫ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ የአገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሉአላዊ የስልጣን ባለቤቶች ሆነው ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበት ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ተገንብቷል፡፡

መንግስት በህግ አውጭ፣ ህግ አስፈፃሚና የዳኝነት አካላት ተዋቅሮ ሁሉም ተወስኖ በተሰጣቸው ስልጣን ክልል የሚንቀሳቀሱበት ህገ መንግስታዊ ማዕቀፍ ተበጅቷል፡፡

ይህም በመሆኑ ያለፉት 27 አመታት የአገራችን ጉዞ አገራዊ የዴሞክራሲ ትንሳኤያችን የተወለደበት ሊሆን ችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትንሳኤ የተረጋገጠውም በእነዚህ አመታት ነበር፡፡ ለማንም ግልፅ እንደሚሆነው አገራችን መጀመሪያ የእዝ ኢኮኖሚ በመናድ መንግስት ቁልፍ ሚና በሚጫወትበት የገበያ ኢኮኖሚ ለመተካት የቻለችው በእነዚህ አመታት ነው፡፡

በብዙ አገሮች ከእዝ ወደ ገበያ ኢኮኖሚ የተሸጋገሩበት ሂደት ያጋጠመውን ከባድ ምስቅልቅልና የህዝብ ስቃይ በማስወገድ የገበያ ኢኮኖሚውን መገንባት ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ እነሆ ለ27 አመታት በለውጥ ምህዋር ውስጥ መግባት ችለናል፡፡

በተለይ ደግሞ ድርጅታችን ኢህአዴግ በ1993 ዓ.ም አጋጥሞት የነበረውን ቀውስ የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ሞዴልን በመከተል ከፈታን በኋላ በኢኮኖሚና ማህበራዊ መስክ የተመዘገበው ፈጣን እድገትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በዜጎቻችን ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ ማህበረሰብ ሳይቀር የተመሰከረለት ሆኗል፡፡

ኢኮኖሚያችን ለተከታታይ 16 አመታት ከፍተኛ የእድገት ምጣኔ እያስመዘገበ ተጉዟል፡፡ መነሻው ገጠርና ግብርና የሆነው ይህ እድገት ሁሉንም የአገራችን አካባቢዎች ደረጃ በደረጃ እያዳረሰ የተጓዘ ነው፡፡

የአገራችን አርሶ አደሮችንና አርብቶ አደሮችን ምርታማነት ለማሳደግ በተካሄደው ከፍተኛ ጥረት በምርታማነታችን እድገት ላይ የነበረው ገደብ ተነስቶ ተስፋ ሰጭ የግብርና ምርት እድገት ተመዝግቧል፡፡ በዚህም አብዛኛው የገጠር ነዋሪ ተጠቃሚ መሆን ጀምሯል፡፡

በከተሞችም ከአነስተኛና ጥቃቅን እስከ ቀላልና ከባድ ኢንዱስትሪ በልዩ ልዩ የአገልግሎት መስኮች ልማት ተስፋፍቶ ዜጎች ከአገሪቱ እድገት ጋር ደረጃ በደረጃ ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል፡፡

ትምህርትና ጤና ተስፋፍቶ በአገራችን ለልማት መፋጠን ተፈላጊው ቅድመ ሁኔታ እየተፈጠረ የህዝቡ ተጠቃሚነትም እየጨመረ ሲሄድ ቆይቷል፡፡

የህዝብን የልማት አቅም ለመደገፍ የሚያስችሉ መንግስትና ግዙፍ የመሰረተ ልማት አውታሮች ግንባታ ተስፋፍቶ አገራችን ደረጃ በደረጃ የተወዳዳሪነት አቅሟን እያጠናከረች ስትጓዝ ቆይታለች፡፡

መላው የአገራችን ህዝቦች እንደሚገነዘቡት አገራችን የተጓዘችበት የ27 አመታት ጉዞ ከአንድ እድገት ወደሌላ በፍጥነት የተረማመድንበት ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ልዩ ልዩ ችግሮች እያጋጠሙትና እነዚህንም በፍጥነት ሳንፈታቸው በመቆየታችን የተነሳ ለሌሎች ተዛማጅ ችግሮች ስንጋለጥ ቆይተናል፡፡

በመላ የአገራችን ህዝቦች ዙሪያ መለስ ርብርብ የተመዘገቡትን ድሎች ከማስጠበቅ አኳያ የመጀመሪያው ዋነኛ ችግር ሆኖ የተከሰተው መልካም አስተዳደር የማስፈን ጉዳይ ነው፡፡

ምንም እንኳ በዚህም ረገድ የተጓዝንበት ሂደት የህዝብን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረገና ለፈጣን እድገት ያበቃን መሆኑ ባይካድም በተለይ ከቅርብ አመታት ወዲህ የመልካም አስተዳደር ችግር እየተባባሰ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያስመረረና በስርዓቱ ላይ ያላቸው አመኔታ እንዲሸረሸር ምክንያት ሆኗል፡፡

ሙስና እየተበራከተና የህዝብን ልማታዊ ጥረትና ተጠቃሚነት በእጅጉ እየጎዳም ሲሄድ ቆይቷል፡፡

ሙስና ህዝብ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዳያገኝ፣ የህግ የበላይነት እንዳይረጋገጥና ግልፅነት፣ ተጠያቂነትና ዴሞክራሲ እንዲዳከም ከፍተኛ እንቅፋት እስከመሆን ደርሷል፡፡

ይህ ችግር በጊዜና በአግባቡ ባለመቀረፉ የተነሳ በመልካም ሁኔታ የተጀመረውን አገራዊ የለውጥ ጉዞ ለከፍተኛ አደጋ ከማጋለጥ አልፎ ለልዩ ልዩ ቅሬታዎች መበራከትና አገራዊ ህልውናችንን የመፈታተን ጠንቅ እስከ መሆን ደርሷል፡፡

በተለይ ደግሞ ቁጥሩ እየሰፋ የመጣውንና አስተማማኝ የስራና የገቢ እድል ሊፈጠርለት የሚገባውን ወጣት ክፉኛ ተፅዕኖ የፈጠረበት ሆኗል፡፡

በአገር ግንባታ ሂደት ብቁና ገንቢ ሚና መጫወት ያለባቸው ወጣት ወንዶችና ሴቶች ያጋጠሟቸው ችግሮች አስተማማኝ መፍትሄ እንዳያገኙም ጠንቅ ሆኗል፡፡

አገራችን በፈጣን የእድገት ሂደት ውስጥ መግባቷን ተከትሎ የተከሰቱ አዳዲስ ፍላጎቶችና ተግዳሮቶችን በጊዜ ለይቶ መፍታት እንዳይቻልና ፈጣኑን እድገት ህዝብ በሚጠቀምበት አቅጣጫ የማስቀጠል ግባችንን እስከመጉዳትም ደርሷል፡፡

የኢህአዴግ ምክር ቤት ድርጅታችን ይህን የመሰለውን ችግር በጊዜ እንዳያስተካከል ያደረጉት በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ የገመገመ ሲሆን በዋነኛነት ምክንያት ሆኖ ያገኘው ደግሞ በድርጅታችን ውስጥ የህዝብ አገልጋይነት መንፈስ እየተዳከመ ስልጣንን የግል ጥቅም ማሳደጃ መሳሪያ አድርጎ የመመልከትና የመጠቀም ዝንባሌ ሲስፋፋ መቆየቱ ነው፡፡

ለ27 አመታት ያስመዘገብናቸው ሁሉን አቀፍ ለውጦች በድርጅታችን ጠንካራ የህዝብ አገልጋይነት መንፈስና ቅኝት ምክንያት የመጡ መሆናቸው ተዘንግቶ ስልጣን የግል ክብርና ጥቅም ማሟያ ተደርጎ መወሰድ በመጀመሩ መልካሙን ጅምር ሂደት የሚጎዳ በርካታ ስህተቶች ተፈፅመዋል፡፡

ፀረ ዴሞክራሲያዊ ዝንባሌ እየተስፋፋ ህገ መንግስታዊ ዴሞከራሲያችን ሳይቀር ለአደጋ ሲያጋልጠው ቆይቷል፡፡

በስልጣን ፍላጎት የተነሳ ለጥቅም ቡድኖች መፈጠርና መሻኮት የተመቸ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በአመራሩ ውስጥ የሚንፀባረቁ የትምክህትና ጠባብነት አመለካከቶች መግነን የድርጅቱንና የሀገራችን ህልውና እስከመፈታተን ደርሷል፡፡

ድርጅታችን በአስተሳሰብ ጥራት የሚመራበትን የቆየ ብቃት ቀስ በቀስ እያጣ ግብታዊነት የበዛበት ሂደት ሲስፋፋ ቆይቷል፡፡

በዚህ የተነሳ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዳችን አፈፃፀም በታሰበውና በሚፈለገው የውጤታማነት ደረጃ ላይ ሳይደርስ ቆይቷል፡፡

እነዚህ ችግሮች ከምንም ነገር በላይ የከፍተኛ አመራሩ ድክመቶች መሆናቸው በምክር ቤቱ ግምገማ የተረጋገጡ ሲሆን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ለተከሰተው ችግርም ሆነ ለታየው ውድቀት ኃላፊነቱን እንደሚወስድ አረጋግጧል፡፡

በየደረጃው የተወሰዱ ተጠያቂነትን የማረጋገጥ እርምጃዎችም ተገቢና ትክክል በመሆናቸው በተመሳሳይ እርምጃዎች እንዲጎለብቱ መደረግ እንዳለበት ምክር ቤቱ ወስኗል፡፡

ምክር ቤቱ በአገራችን የተጀመረውን ለውጥ ህዝብ በሚጠቅም አቅጣጫ ለማስቀጠል የሚቻለው ድርጅታችንን ከተጣቡት ስህተቶች አላቆ በማጠናከርና በህዝብ አገልጋይነት መንፈስ እንዲንቀሳቀስ በማድረግ እንደሆነ በአፅንኦት ወስኗል፡፡

በተጨማሪም መንግስት የራሱንና የገበያውን የተስተካከለ ሚና አጣጥሞ አገራዊ ትንሳኤያችንን በሚያረጋግጡ የዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ተግባራት ላይ ሲሳተፍና ለመላው አገራችን ልማታዊ ኃይሎች አመቺ ሁኔታ ሲፈጥር እንደሆነ በመገንዘብ የስርዓቱ ዋነኛ ፈተና የሆነውን በመንግስት ስልጣን ያለአግባብ የመገልገል ዝንባሌ እየታገለና ራሱን በቀጣይነት እያፀዳ የህዝብ አገልጋይነቱን አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል፡፡

የአገራችንን የዴሞክራሲያዊና የኢኮኖሚና ማህበራዊ ትንሳኤ ለማረጋገጥ የተጀመረውን እንቅስቃሴ ከተደቀኑበት ፈተናዎች እያላቀቁ ማስፋትና ማጠናከርም ተገቢ ይሆናል፡፡

እነዚህ የለውጥ ተግባራት ህዝብን በሚጠቅም መንገድ ሊፈፀሙ የሚችሉት ልዩነቶችን በዴሞክራሲያዊና ህጋዊ መንገድ በማጣጣምና በህዝብ ድምፅ በመፍታት መጓዝ ሲቻል በመሆኑ የአገራችንን ሰላምና ዴሞክራሲ ማጎልበት ከመቼውም ጊዜ የላቀ ትኩረት እንዲሰጠው ምክር ቤቱ ወስኗል፡፡

ምክር ቤቱ በስብሰባው ላይ ከመከረባቸው ጉዳዮች ሌላው በአገራችን ህዝቦች መካከል ያለው ግንኙነት ነው፡፡ በአገራችን ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ በድርጅታችን መሪነት ከታሪክ የተወረሱ የተዛቡ ግንኙነቶችን ለማስተካከል ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡

በዚህም በመላ አገራችን ህዝቦች መካከል እጅግ መልካም ግንኙነት ተፈጥሮ ህዝባዊ አንድታችን እየተጠናከረ ሲሄድ ቆይቷል፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተወሰነ ደረጃ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን የሚያሻክሩ ዝንባሌዎችና ግጭቶች እየተስፋፉ ሲመጡ ቆይተዋል፡፡

አልፎ አልፎ የተከሰቱት እነዚህ ግጭቶቸ በህዝብ ላይ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት አስከትለዋል፡፡ በግጭቶቹ የተነሳ ከየብሄረሰቡ ዜጎች ለሞትና አካል ጉዳት እንዲሁም ለተለያዩ ማህበራዊ ምስቅልቅሎች እንድንጋለጥ አድርጎናል፡፡

የኢህአዴግ ምክር ቤት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስፋፉ የመጡ የእርስ በርስ መጠራጠሮችና አንድን ማህበረሰብ ነጥሎ በማጥላላት ላይ የተመሰረተ አካሄድ ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ይህን በፅናት የማስተካከል እንቅስቃሴ እንዲካሄድ ወስኗል፡፡

በአገራችን የብሄሮች እኩልነት ተረጋግጧል፤ የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል መሰረት ተጥሏል፡፡ በተግባርም ትልቅ ትርጉም ያለው አዎንታዊ ውጤት ተመዝግቧል፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ከእድገት ደረጃችን ጋር ያልተጣጣሙ የአሰራር ክፍተቶች መኖራቸውንም ምክር ቤቱ በግምገማው ተግባብቶበታል፡፡

እነዚህ ክፍተቶች በአግባቡና በጊዜ አለመደፈናቸው የቅሬታ ምንጭ በመሆን ግጭቶችንም አስከትሏል፤ ተቀባይነት የሌላቸው መጠቃቃቶችም ተፈጥረዋል፡፡

በአገራችን የጭቆና ስርአት የለም፡፡ የአሰራር ክፍተት አለ፡፡ ይህም ሆኖ የተካሄደው መጠቃቃት ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ በአፋጣኝ እንዲስተካከል ይደረጋል፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ሰርቶ የመኖር መብቱ እንዲከበርና ይህም በፅናት እንዲተገበር ይደረጋል፡፡

የኢህአዴግ ም/ቤት ምንም እንኳ በአገራችን በመገንባት ላይ ያለው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ፅኑ መሰረት ያለው ቢሆንም ያጋጠመንን ጊዜያዊ ችግሮች በመንተራስ አገራችንን ማተራመስ የሚፈልጉ ሁሉ ልዩ የስርዓት ማፍረስ ስልቶችን ቀይሰው እድላቸውን እየሞከሩ እንደሆነ አንስቷል፡፡

የህግ የበላይነትን ደግሞ ደጋግሞ በመጣስ፣ በሶሻል ሚዲያ መሳሪያነት አመፅን የለት ተዕለት የትግል ስልት አድርጎ በማቀጣጠል፣ በመንግስትና በድርጅት ላይ አመኔታ እንዲታጣ በማድረግ፣ ህዝብን ከህዝብ የማጋጨት ተግባር እንደነበረ በመገምገም መላው የሀገራችን ህዝቦች ማጣጣም የጀመሩት ሰላም እንዳይደፈርስ በፅናት ሊቆሙለት እንደሚገባ በማስመር ድርጅታችን የመሪነት ሚናውን በብቃት መወጣት እንደሚገባው አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

የተከበራችሁ የኢህአዴግ አመራሮችና አባላት፤

ባለፉት ሩብ ክፍለ ዘመናት በድርጅታችን መስመር የሃገራችን ትንሳኤ ለማረጋገጥ የሚያስችል ርብርብ በማድረግ በሁለንተናዊ መስክ ለተረጋገጠው ስኬት የበኩላችሁን የማይተካ ሚና ተጫውታችኋል፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ህዝባችን ከእኛ ማግኘት የሚገባውን አገልግሎት በተገቢው ደረጃ በመስጠት፣ እድገታችንና አዳዲስ ነባራዊ እውነታዎች እየፈጠሩት ያለውን ሁኔታ የሚመጥን አመራር ባለማረጋገጥና በተግባር አርአያ በመሆን ረገድ እያሳየን ያለነውን መዘናጋት ፈጥነን በማረም ህዝብን የማገልገል ከሚሊዮኖች መካከል የሚገኝ ዕድል መሆኑን በመገንዘብ፣ በድርጅታችን እምነት ስልጣን የህዝብ ማገልገያ መሳሪያ መሆኑን በጥብቅ በማመን መሰረታዊ የድርጅታችን እሴት የሆነውን የህዝባዊነት አመለካከት የዕለት ተዕለት መመሪያችን መሆኑን በተግባር በማሳየት ህዝባችንን ለመካስ የሚያስችል እንቅስቃሴ ውስጥ እንድንገባ ድርጅታችሁ ጥሪውን ያስተላልፍላችኋል፡፡

የተከበራችሁ የሃገራችን ህዝቦች፤

ድርጅታችን ኢህአዴግ በተራዘመ ህዝባዊ ትግል አገራዊ ትንሳኤያችንን በማረጋገጥ ስኬታማ አቅጣጫ የተጓዘና ከመላ የአገራችን ህዝቦች ጋር በመሆን ለዚህ መሰረታዊ ለውጥ ተገቢውን አመራር የሰጠ ድርጅት ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የገጠሙት ፈተናዎች ከባድና የተወሳሰቡ ቢሆኑም እነዚህን እንደተለመደው በህዝባችን ኃይልና ቀና አስተሳሰብ በመተማመን ለመፍታት ተዘጋጅቷል፡፡

አንዳንድ ያጋጠሙን ፈተናዎች በደረስንበት የእድገት ደረጃ የማይቀሩ ብቻ ሳይሆን ወደፊትም ሊያጋጥሙ የሚችሉ እንደሆኑ እንገነዘባለን፡፡

በመሆኑም ከዚህ ቀደም ያሳየነው መዘናጋትና ስህተት በማይደገምበት ሁኔታ ለመጓዝ ተዘጋጅቷል፡፡ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመመካከርና ግብአታቸውን በመጠቀም ወደፊት ለመራመድና በልዩ ትኩረት ለመስራት ተዘጋጅተናል፡፡

በመሆኑም መላው የሃገራችን ህዝቦች እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የጀመርነው የህዳሴ ጉዞ ከግብ እንዲደርስ ድጋፋችሁን እንድትቀጥሉ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የተከበራችሁ የሃገራችን አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች፤

ባለፉት አመታት ባካሄድችሁት የፀረ ድህነት ትግል ከራሳችሁ ተጠቃሚነት ባሻገር የሃገራችንን ገፅታ ለመቀየር ያስቻለ ስኬት አስመዝግባችኋል፡፡ በሃገር ደረጃ ለተረጋገጠው የምግብ ዋስትና የማይተካ ሚናችሁን ተጫውታችኋል፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ያስቀመጥነውን ሃገራዊ ህዳሴ ለማረጋገጥ አሁንም ረዥም ርቀት መሄድ ይጠበቅብናል፡፡

በዚህ ረገድ የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ በላይ የሆኑ በዘመናዊ የግብርና ልማት ላይ የተመሰረተ የሰብል፣ የእንስሳት፣ የአትክልትና የፍራፍሬ ልማት ስራዎቻችን የማስፋፋትና ወደ አንድ የላቀ ምዕራፍ የማሸጋገር እንዲሁም በግብርና ላይ የተመሰረተ የኢንዱስትሪ ልማት አቅጣጫችንን ከዳር የማድረስ ጉዳይ ከእናንተ ጠንካራ የተደራጀ እንቅስቃሴ ውጭ የሚታሰብ አይደለም፡፡

የመኸር እርሻ ስራዎች ላይ ከወትሮ የተለዩ ርብርብ በማድረግ የጀመርነው ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ዕድገት እንዳይቆራረጥ ከእስከአሁኑ በላይ በቴክኖሎጂ በታገዘ ዘመናዊ አሰራር ላይ የተመሰረተ ጥረታችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ጥሪውን ያስተላልፍላችኋል፡፡

በዚህ ረገድ በእውቀት፣ በቴክኖሎጂ ፣ በግብአት አቅርቦት ረገድ የሚታዩ ጉድለቶችን ለማረም ከወትሮ በላቀ ደረጃ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ቁርጠኝት የፈጠረ መሆኑን ለማረጋገጥ ይወዳል፡፡

የተከበራችሁ የሃገራችን ወጣቶች፤

ሃገራችን ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ለዜጐች በተለይ ለወጣቶች የተመቸች ሃገር እንድትሆን አፋኝና ፀረ- ዴሞክራሲያዊውን ስርዓት ገርስሶ በመጣል የትናንት ወጣቶች የከፈሉት ታላቅ መስዋዕትነት በፀረ- ድህነት ትግሉም እያበረከታችሁ የመጣችሁትን ሚና ድርጅታችን በአግባቡ ይገነዘባል፡፡

ወጣቶችን ጨምሮ ለዜጐቿ የተመቸች ሃገር የመገንባት ጉዳይ የነገ ሳይሆን የዛሬ ነው፡፡

ስለሆነም በሃገር ግንባታ ሂደት የሃገራችን ወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ጉዳይ ዋነኛ ስትራቴጅያዊ ሃይል ወጣቶች ራሳችሁ በመሆናችሁ በተደራጀ መንገድ በመንቀሳቀስ የበኩላችሁን የማይተካ ሚና እንድትጫወቱ፣ መሪ ድርጅታችንና ልማታዊ ዴሞከራሲያዊ መንግስታችን ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር የጋራ አቅማችንን አስተሳስረን እንድንረባረብ፣ በመንግስት በኩል መፈጠር ያለባቸውን ምቹ ሁኔታዎች ያላችሁን እምቅ አቅምና ችሎታ ጥቅም ላይ ለማዋል በሚያስችል መንገድ እንዲመራ እንደምናደርግ ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን፡፡

የተከበራችሁ የሃገራችን ሴቶች፤

ድርጅታችን ኢህአዴግ ባለፉት አመታት በሃገራችን ባካሄዳቸው መሰረተ ሰፊ እንቅስቃሴዎች የሃገራችን ሴቶች ተጠቃሚነታችሁን በማረጋገጥ ሂደት የድርጅታችን የጀርባ አጥንት ሆናችሁ ትግሉን በመደገፍና የተገኙ ድሎችን በማረጋገጥ ረገድ የማይተካ ሚናችሁን ተጫውታችኋል።

በሰላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ትግሉ ያበረከታችሁትን አስተዋፅኦ ወደ ላቀ ምዕራፍ በማሸጋገር የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ በልማታዊ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ የበላይነት እስኪደመደም ድረስ ድሉን በመጠበቅና አጠናክሮ በመቀጠል የሚታዩ የሰላም መደፍረስ፣ የህገ ወጥነትና የስርዓት አልበኝነት አዝማሚያዎችን ጨምሮ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በፅናትና በቀጣይነት በመመከት ለላቀ ተጠቃሚነታችሁ በፅናት እንድትቆሙ ድርጅታችን ጥሪውን በድጋሚ ያቀርባል፡፡

የተከበራችሁ የሃገራችን ባለሃብቶችና የንግዱ ማህበረሰብ አካላት፤

የጀመርነውን የህዳሴ ጉዞ ከዳር በማድረስ ረገድ የልማታዊ ባለሃብቱ ሚና የማይተካ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር በጥራትና በተወዳዳሪነት ላይ የተመሰረተ የባለሃብቱ ተሳትፎ የባለሃብቱን ዘላቂ ተጠቃሚነትና የሃገራችንን ህዳሴ በማረጋገጥ ረገድ ላቅ ያለ ትርጉም ያለው ነው፡፡

ስለሆነም የባለሃብቱ ዘላቂ ተጠቃሚነት የሚረጋገጠው በልማታዊነት እንጂ በኪራይ ሰብሳቢነት መንገድ ባለመሆኑ በልማታዊነት መንገድ ብቻ በመንቀሳቀስ መዋቅራዊ ለውጡን ከዳር እንዲያደርስ ድርጅታችን ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን እና እርሱን የሚመራው ድርጅት የሃገር ውስጥ ባለሃብት የማጠናከር ተግባሩን አጠናክሮ ለመቀጠል የሚያስችል ርብርብ የሚያደርግ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡

የተከበራችሁ የሃገራችን ምሁራን፤

በእስከአሁኑ ጉዟችን የመወዳደሪያ አቅም የሆነውን የሰለጠነ ሰው በማምረት የሃገራችንን የመወዳደሪያ አቅም ወደ አንድ ምዕራፍ ያሸጋገረ ተልዕኮ እየተወጣችሁ ትገኛላችሁ፡፡

ይሁን እንጂ የተወዳዳሪነት አቅማችንን እየገነባንበት ያለው መንገድ ለውጡ በደረሰበት እና እየገባንበት ያለውን አዲስ ሁኔታ በሚመጥን ደረጃ ለማድረግ በጥናትና በምርምር አዳዲስ ሃሳቦችን ለሃገራችን ልማትና ዕድገት በሚመጥንና ይህንኑ በሚያስቀጥል አግባብ ደረጃ በማቅረብ አቅማችሁን ሳትሰስቱ እንድትሳተፉ፣ በሲቪል ሰርቪሱ የተሰማራችሁ፣ በአምራች፣ አገልግሎት ለዜጐች በማቅረብም ሆነ በጥራት በተወዳዳሪነት ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ በማድረግ ተሳትፏችሁን እንድታረጋግጡ፣ የኪነ ጥበብ ሙያተኞችም ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠር ሙያችሁን ለሃገራችን ህዳሴ በማዋል ከእስከ አሁኑ ጥረት የላቀ ርብርብ በሚጠይቀን ምዕራፍ ላይ የምንገኝ መሆናችንን ከግምት ያስገባ እንቅስቃሴ እንድታደርጉ ጥሪውን ያቀርብላችኃል፡፡ ይህን አለኝታ ለህዳሴያችን ጥቅም ለማዋል ድርጅታችንና በሱ የሚመራው መንግስት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር
ከእስካሁኑ ያደገ ስራ የምንሰራ መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡

የተከበራችሁ አጋር ድርጅቶች፤

ባለፉት አመታት በሀገራችን የተመዘገቡ ድሎች በምትመሯቸው ክልሎች የተመዘገቡ ድምር ውጤትም ጭምር ናቸው፡፡ በሰጣችሁት አመራር የክልሉን ህዝቦች ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ አዎንታዊ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በልማቱ፣ በመልካም አስተዳደርና በዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ረገድ የተመዘገቡ ውጤቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል፣ የታዩ ጉድለቶችን በቀጣይ ለማረምና የህዝቦችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በምታደርጉት ርብርብ ኢህአዴግ ከጐናችሁ መሆኑን እያረጋገጠ የጀመርነውን የሃገራችን ህዳሴ ጉዞ ከዳር እንድናደርስ ጥሪውን ያስተላልፍላችኋል፡፡

የተከበራችሁ የሃገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች፤

የፖለቲካ ልዩነቶቻችን እንደተጠበቀ ሆኖ ባለፉት አመታት በሃገራችን እየተገነባ ለመጣው የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ የበኩላችሁን አስተዋፅኦ አበርክታችኋል፡፡

አሁን በደረስንበት ደረጃ ሰላማችንን ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በማክበርና በማስከበር እንዲሁም የጀመርነውን የመድብለ ፓርቲ ዴሞከራሲ ስርዓት ግንባታ ትግል በማስቀጠል ሂደት የበኩላችሁን ሚና እንድትወጡ ኢህአዴግ ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡ ይህን በማጐልበት ሂደትም ሚናችንን በተገቢው አጠናክረን የምንወጣ መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡

የተከበራችሁ የጀግናው መከላከያ ሰራዊታችንና የፀጥታ አካላት፤

የሃገራችንን ሉአላዊነት በማስከበር ባለፉት አመታት በከፈላችሁት መስዋዕትነት ሉአላዊነቷ የተረጋገጠ በመስዋዕትነት የተከበረች ሃገር እንድትኖረን በማድረግ ለህዳሴ ጉዟችን እንቅፋት መሆን የሚመኙ፣ የሚያስቡ፣ የሚሞክሩ የእጃቸውን እንዲያገኙ በማድረግ ከህዝባችሁ ጋር ሆናችሁ አኩሪ ገድል ፈፅማችኋል፡፡

እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ህዝባዊ ባህሪያችሁን አጠናክራችሁ በመቀጠል የህዳሴ ሂደታችንን ለማወክ የሚሰነዘሩ (የሚቃጡ ጥቃቶችን) ሙከራዎችን በብቃት በመመከት የሃገራችንን ሰላምና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በማስጠበቅ የምታደርጉትን ርብርብ አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

በሀገራችን የህግ የበላይነት እንዲከበር እስካሁን ስላበረከታችሁት አስተዋፅኦ አክብሮታችንን እየገለፅን፣ ወደፊትም የህግ የበላይነት ያለምንም ማቅማማት እንዲከበር የበኩላችሁን አገራዊ ግዴታ እንደወትሮ ሁሉ ሃላፊነት በተሞላበት አግባብ እንድትወጡ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

ከህዝባችን ጋር ሆነን የማናልፈው ችግር የለም !!

ህዳሴያችን በትግላችን ተጠናክሮ ይቀጥላል!!

መጋቢት 2010 ዓ.ም

የኢህአዴግ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት

አዲስ አበባ

LEAVE A REPLY