ጉዳዩ — ኦሮምኛን የእራሱ በሆነው በግዕዝ ፊደል ተጓዳኝ የፌዴራል ቋንቋ ስለማድረግ ተገቢነት
ክቡር ፕሬዚደንት ሆይ
ክቡርነትዎ ጠንቅቆ እንደሚያውቀው፣ ከአማርኛ ቀጥሎ ኦሮምኛ በሚሊዎኖች ኢትዮጵያውያኖች የሚነገር ትልቅ ቋንቋ ነው። ሆኖም እስክ አሁን ድረስ የኢትዮጵያ ማእከላዊ መንግሥት የሥራ ቋንቋ ሆኖ አያውቅም። ካናዳ የተባለውን ሃገር እንደ ምሳሌ ብንወስድ፣ ሁለት ብሄራዊ ቋንቋዎች አሉት፣— እንግሊዝኛ እና ፈረንሳይኛ። የካናዳ ህዝብ፣ በተለይም የመንግሥት ሠራተኞች ሁለቱን ቋንቋዎች ይችላሉ። ቋንቋዎቻቸው እኩል ተከብረው የፌዴራል መሥሪያ በመሆናቸው የካናዳ ህዝቦች በእዚህ ረገድ የእኩልነት ስሜት የሚሰማቸው እና የረኩ ናቸው። በኢትዮጵያም ደረጃ ኦሮምኛም ከአማርኛ ጋር በተጓዳኝነት የፌደራል ቋንቋ ቢሆን ብዙ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና ስነልቦናዊ ጥቅም ይኖረዋል። ይህን ግንዛቤዎ ውስጥ አኑረው ኦሮምኛ ሁለተኛ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቋንቋ ይሆን ዘንድ እርስዎ እና የሃገር አስተዳደር ባልደረቦችዎ የሚቻላችሁን ታደርጉ ዘንድ አሳስባችኋለሁ።
ካለፉት 30 ዓመት ወዲህ የተወለዱና የማስተማሪያ ቋንቋቸውን ኦሮምኛ ብቻ ባደረጉ የትምህርት ተቋማት የተማሩ የኦሮሞ ወጣቶች ሥራ ማግኝትን አስመልክቶ ተጎጂዎች ሆነዋል። እነዚህ ወጣቶች በክልላቸው መንግሥት የተነገራቸውን ተቀብለው በኦሮሚፋ ብቻ በመማር የትምህርት ጊዜያቸውን አባከኑ። በርካታዎቹ በትምህርታቸው በጥሩ ውጤት ከተመረቁ በኋላ ግን በፌዴራሉ የሥራ ቋንቋ ስለማያነቡና ስለማይጽፉ በመላ ኢትዮጵያ በሚገኙት የሥራ ዕድሎች ተወዳዳሪና ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም። ሌሎች ዜጎች የሚያገኙትን ዕድል ያለጥፋታቸው የኦሮሞ ልጆች አጡ። በወቅቱ የነበሩት የኦሮምያ ክልል አስተዳዳሪዎች ብልሆች ቢሆኑ ኖሮ የሚፈጠረውን ችግር አስቀድመው ገምተው የደቡብ ህዝቦች፣ ተጋሩዎች እና ሌሎቹም ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እንዳደረጉት ልጆቻቸው አማርኛን እንደ ሁለተኛ ቋንቋቸው እንዲማሩ አድርገው የሥራ አድላቸውን ባሰፉላቸው ነበር። ያለፈው ቢያልፍም፣ ለዘለቄታው ግን ለእዚህ ሁሉ የተሻለ መፍትሄ የሚሆነው ኦሮምኛ ሁለተኛ የማእከላዊ መንግሥት ቋንቋ ቢደረግ ነው።
ከእዚህ ጋር በተያያዘ፣ ይህስ ደግ ነው፣ ዳሩ ግን ኦሮምኛ በምን ፊደላት ይከተብ፣ የሚል ጥያቄ ሊከተል ይችላል፣— በባእዱ በላቲን ወይስ በሃገር-በቀሉ ኢትዮጵያዊ ፊደል? በእኔ እና በሌሎችም ምሁራን ምርምር ውጤት መሰረት፣ ከላቲን ይልቅ፣ በተለምዶ ግእዝ በሚባለው፣ እንደ እውነቱ ግን ኢትዮጵያዊ ፊደል መሰኘት በሚገባው ፊደል ኦሮምኛ ቢፃፍ እጅግ በርካታ ፋይዳዎች አሉት። ይህን አባባሌን ዝቅ ብዬ በማስረጃ አንተርሳለሁ።
የሚከተለውን የቁቤ ጽሁፍ ወስደን ከግእዝ እና ከላቲን ፊደል የትኛው ይበልጥ ውጤታማና ብቁ እንደ ሆነ እንመለከታለን፡-
Uummanni Oromoo ilmaan namaa biyya lafaa
ኡመኒ ኦሮሞ ኢልማን ነማ ብያ ለፋ
Kanarratti Uumaman kessaa tokkodha Biyyi
ከነረቲ ኡመመን ኬሳ ቶኮዳ ብዪ
Uumamaa fii jireenya issa Aafrikaa Bahaa
ኡመማ ፊ ጅሬኘ ኢሳ አፍሪካ በሃ
Gara kaabaatti Yemmuu ta’u Uummmata
ገረ ካባቲ የሙ ተኡ ኡመተ
Akata Sabaatti baay’ina gudda qabu kan
አከ ሳባቲ የሙ ተኡ ኡመተ
Baha gaanfa Aafrikaatti argamu keessaa
ባሃ ጋንፋ አፍሪካቲ አርገሙ ኬሳ
Isa tokko Seenaan uummata kanaa akkuma
ኢሳ ቶኮ ሴናን ኡመተ ከና አኩማ
Sabaaf sab-lammaota Aafrikaa heddu namnii
ሳባፍ ሳብ ላሞታ አፍሪካ ሔዱ
Seeraaf sirnaan qulqulleessee barreesse
ሴራፍ ሰርናን ቁልቁሌሲ በሬሴ
Jiraachun baatullee uummata seenaa
ጂራቹ ባቱሌ ኡመተ ሲና
Gudddaa fii gaarii qabu akka ta’e huba
ጉዳ ፊ ጋሪ ቀቡ አከ ተኤ ሁበ።
Chuun nama hin dhiba
ቹን ነመ ሕን ድቡ።
ከላይ ከቀረበው ናሙና ውስጥ የተወሰኑ ቃላትን እየጠቀስን የኢትዮጵው ፊደል ኦሮምኛን ለመጻፍ ከላቲኑ እና ከኢትዮጵያው ፊደል የትኛው ብቁ፣ ቀልጣፋ እና ጊዜ እና ገንዘብ ቆጣቢ እንደሆነ እንይ፤
Uummanni Oromoo ilmaan namaabiyya lafaa “Uumamaa” የሚለው ቃል በላቲን ሲጻፍ 7 ሆህያት ፈጅቷል። በኢትዮጵያው ግን “ኡመማ” ተብሎ በ3 ፊደላት ይጻፋል። “oromoo” የሚለው ቃል በላቲን 6 ሆህያት አሉት፤ በግዕዝ ግን “ኦሮሞ” ተብሎ በ 3 ሆህያት ይጻፋል። “ilmaan” የሚለው በላቲን 6 ሆሄያት አሉት፤ በግዕዝ ግን አራት በቂው ነው። “namaa፣ biyya፣ lafaa፣” የሚሉትም ቃላት በላቲኑ እያንዳንዳቸው 5 ሆሄያት ፈጅተዋል። በግዕዙ ቢሆን ግን “ነማ፣ ቢያ፣ ለፋ” ተብለው እያንዳንዳቸወቅ በ 2 ፊደላት ይጻፋሉ። ኡመኒ ኦሮሞ ኢልማን ነማ ብያ ለፋ Kanarratt Uumama kessaa tokkodha Biyyi የሚሉትን ደግሞ ስናይ “Kanarratti” በላቲን ሲጻፍ 10 ሆሄያት ያስፈልጉታል። በኢትዮጵያው ፊደል በግዕዙ ግን በ 4 ሆሄያት ይጻፋል። “Uumaman” በላቲን 7 ሆሄያት ያስፈልጉታል። በግዕዝ ግን 4 ሆህያት ይበቁታል። “kessaa” የሚለው በላቲን 6 ሆሄዎች ያስፈልጉታል። በራሳችን ፊደል ግን “ኬሳ” ተብሎ በ2 ፊደላት ይጻፋል። “Tokkodha” እና “Biyyi” የሚሉትም በላቲን እንደ ቅደም ተከተላቸው 7 እና 5 ሆህያት ሲኖሯቸው በግዕዝ ግን 3 እና 2 ሆሄዎች ብቻ ነው የሚኖራቸው።
ነገሩ በገጽ ሲታሰብ በላቲን 100 ገጽ የሚፈጅ ጹሁፍ በግዕዝ ግን በ40 ገጽ ሊጻፍ ይችላል። ብዙ ሺ ኮፒ ሲታተም በላቲን ሲሆን አላግባብ የሚባክነውንና በግዕዙ ሲሆን ግን የሚቆጠበውን ስንትና ስንት ቶን ወረቀት አስቡት። ጊዜንና ገንዘብን በተመለከተም እንዲሁ ነው። ለምሳሌ ባለ 100 ው ገፅ በላቲን የተፃፈው መፅሃፍ በ 100 ሳንቲም ቢታተም በግዕዙ የተከተበው ግን 40 ሳንቲም ብቻ ይሆናል። ሂሳቡ በሺ ብሮች ቢሰላ በላቲን ቢፃፍ 6000 ብሮች ማዳን ይቻላል ማለት ነው። የእዚህን ሁሉ ትርፍና ኪሳራ ዐይተው እርስዎ ይፍርዱ።
ኦሮምኛ በኢትዮጵያ ቀለማት ቢፃፉ የተሻለ ነው ሲባል አንዳንድ የድሮ ፖለቲከኞችና የቅድሞ ታጋዮች የሚያቀርቡት ሰበቦች አንዳንድ የኦሮምኛ ቃላት በተለምዶ ግዕዝ በሚባለው ኢትዮጵያዊ ፊደላት ሊፃፉ አይችሉም፣ ለ ታይፕራይትርም አይመቹም፣ የሚሉ ናቸው። ይህ ግን እውነት አይደለም። ለምሳሌ አይቻሉም ተብለው የነበሩት ፊደላትና ቃላት በኦሮሚያዊትዋ ልጅ፣ በሰንዳፋው ተወላጅ በዶክተር አበራ ሞላ መላ እነሆ ተችለዋል።
ዸዹዺዻዼዽዾዿ
ዹፌ፣ ዻባ፣ ዻራርቱ፣ ባዻዻ፣ ዼራ፣
ልክ እንደ ላይኛቹ ፊደላት እና ቃላት የኦሮሞ ቀለማት ሁሉ በኢትዮጵያ ፊደላት ተቀርፀው በተግባር ለመዋል እየጠበቁ ነው። እድሜ ለ ዶክተር አበራ ሞላ ከ እኤአ 1987 ጀምሮ በሶፍትዌር ደረጃ ተዘጋጅተው ገበያ ላይ ውለዋል። የ አንዱን ቃል ከሌላው መለያ የማጥበቂያ ምልክቶችም ተበጅቶላቸዋል። ዶክተር አበራ ሞላ የግዕዝ ፊደላት ለኦሮምኛ እና ለሌሎቹም ዋና ዋና ቋንቋዎቻችን መፃፊያ ብቁ እንዲሆኑ ለ 35 ዐመታት ያህል ለፍቶባቸዋል። ስለእዚህ የኢትዮጵያ ፊደላት የላቲኑን ሊተኩ የማይችሉበት ምንም ምክንያት የለም። አውቆ የተደበቀን ቢጠሩት አይሰማም ካልተባለ በቀር። የኢትዮጵያ ፊደላት ኦሮምኛን ለመክተብ ብቁ ከመሆናቸውም በላይ ብዙ ጥቅም ያላቸው መሆናቸውን የሚመሰክሩ ሰነዶች ተዘጋጅተዋል። ለጊዜው ዊኪፔድያ ውስጥ ገብተው የዶክተር አበራ ሞላን የምርምር ውጤት ይመልከቱ። አስፈላጊ ከሆነ እኔ እና ዶክተር አበራ ከአዲስ አበባው ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ባዩ ይማም እና ከ ከሌሎች ቋንቋ ተመራማሪዎች ጋራ ሆነን ሰሚናር ተዘጋጅቶልን ልንነጋገርባቸው እና ተጨማሪ ማብራሪያ ልንሰጥባቸው እንችላለን። ፕሮፌሰር ባዩ ይማምም በበኩላቸው በእዚህ ጉዳይ ላይ ቀደም ብለው ሰፊ ጥናት አካሂደዋል።
ለእኛ ለአሁኑ ዘመን ሰዎች አዲስ ነገር ይመስለናል እንጂ ለኦሮሞ አባቶቻችን በኢትዮጵያ ፊደላት መፃፍ አዲስ እንግዳ ጉዳይ አይደለም። በቅርቡ በደርግ ዘመን እንኳን በሪሳ የሚል ጋዜጣ ነበር። ከ ዛሬ 120 ዐመታት በፊት ቄስ ኦናሲሞስ ነሲብ ሙሉውን ቅዱስ መፅሃፍ ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ራዕየ ዮሃንስ ከትበውበት ነበር። ከዛሬ 200 ዐመት በፊትም እንደፃፉበት የሚያሳይ ሰነድ በ ቀጣፊው ጆግራፊ ላጠና ነው ብሎ መጥቶ ብርቅዬውን መፅሃፈ ሄኖክን ይዞ በኮበለለው በጀምስ በሩስ እጅ ተገኝቷል። በመጀመሪያ በኦሮሞው ተወላጅ በታላቁ ፓስተር በ ኦኔሲሞስ ነሲብ በግዝ ፊደላት ከተተረጎመው መፅሀፍ ቅዱስ ለናሙና ያህል ሁለት ገፆች ከእዚህ ፅሁፍ ግርጌ አስፍሬሎታለሁ።
ቀደም ሲል በግዕዝ ፊደላት በኦሮምኛ ስለተፃፉት ሰነዶች ሁሉ ጠቅለል አድርጎ ለመናገር፣1ኛ. ከ16ተኛው ክፍለ ዘመን በፊት የተከተበ ቅዱስ ቁርአን በሀረር ይገኛል። 2ኛ. በ1845 ከአፄ ቴዎድሮስ ዘመን በፊት የመፅሀፍ ቅዱስ ወንጌላት በከፊል የተፃፋበት 3ኛ. እላይ አንደጠቀስኩት ከ120 አመታት በፊት በኦሮሞው ሊቅ በቅዱስ ኦኔሲሞስ ነሲብ (አባገመችስ) ሙሉው መፅሃፍ ቅዱስ በአፋን ኦሮሞ የተተረጎመበት 4ኛ. በ1967 አ.ም. ከ20 በላይ በሆኑ በተለያዩ ብሄርና ብሄረሰቦች ቋንቋ የመሬት አዋጅን ፈትፍቶና ቁልጭ አድርጎ የተገለፀበት 5ኛ. የኢትዮጵያ የመስረተ ትምህርት ከ30 በላይ ብሄር ብሄረሰቦች ቋንቋዎች በብቃትና በጥራት ይሰጥበት የነበረ 6ኛ. የበሪሳ ታላቅ የአፋን ኦሮሞ ጋዜጣ ለዘመናት በበርካታ ቁጥሮች ሲሰራጭበት የነበረ 7ኛ. የቀድሞው የኢትዮጵያ ህዝባዊ ሪፐብሊክ መንግሥት በበርካታ ባብዛኛው ከ 45 ብሄር ብሄረሰቦች በላይ ቋንቋዎች የተገለጡበት 8ኛ. በበርካታ የእስልምና ዝክሮች፣ መንዙማዎች የተፃፋበት እና የተዘከሩበት 9ኛ. በርካታ የክርስትያን መዝሙራት በኦሮምኛና በሌሎች ቌንቌዎች የተገለጡበት 10ኛ. በአፋን ኦሮሞና በሌሎችም ከረጅም ዘመናት በፊት የመዝገበ ቃላት የተደራጀበት ናቸው። እንኳን ዛሬ ዳብሮ በኮምፒተር ሳይንስ ተደግፎ አይደለም ኢትዮጵያውያኑ ፊደላት ገና ድሮ ተፈትነው ኦሮምኛን ለማስተናገድ እንደሚችሉ ተረጋግጧል። በ ዶክተር አበራ ጥረት በ ዩኒኮድ ዩኒቨርሳል ኮድ በመግባታቸው ጠቀሜታቸው ተገልፆ ዐለምአቀፍ እውቅናን አግኝተዋል።
ከኦሮምኛ በተጨማሪ፣ በኣሁኑ ጊዜ ግዕዝ በዩኒኮድ ዕውቅና ያገኙትን የቢለን፣ ቤንች፣ ምኢን፣ ሙርሲ፣ ሱሪ፣ ትግረ፣ ትግርኛ፣ ኣገው፣ ኣውንጂ፣ አማርኛ፣ ዲዚ፣ ዳውሮ፣ ጉሙዝ፣ ጉራጌ፣ ጋሞ ጎፋ እና ግዕዝ ቋንቋዎች የሚጋሯቸውን ቀለሞችና ሌሎችንም ያስከትባል። ለእዚህም ተግባር የዶ/ር ኣበራ ሞላ ግዕዝኤዲት ገበያ ላይ ውሏል። ኦሮምኛን ጨምሮ እሱ ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች የፈፅመው ተግባር ሁሉ በሚከተለው የዊኪፒዲያ ሊንክ ማግኘት ይቻላል።
https://am.wikipedia.org/wiki/%E1%8A%A3%E1%89%A0%E1%88%AB_%E1%88%9E%E1%88%8B#%E1%8C%8D%E1%8B%95%E1%8B%9D%E1%8A%93_%E1%8A%A6%E1%88%AE%E1%88%9A%E1%8D%8B
የእንግሊዝኛ ወይም የላቲን ፊደላት ተናጋሪው እንደሚናገረው ስለማይፃፉ ስፔሊንጉን ለማወቅ የእድሜ ልክ ትግል ይገጥማል። በኢትዮጵያ ቀለማት ግን ሰው እንደሚናገረው ስለሚፅፍ የእስፔሊንግ ስህተት ሊሠራ አይችልም። ስለእዚህም ከላቲን ወይም እንግሊዝኛ ፊደላት ይልቅ እሱን መምረጥ ይገባናል። እኛም እንደተጋሩ ወገኖቻችን ብልጥ መሆን ይገባናል። እነሱ በኢትዮጵያ ፊደላት እንጂ መቼ በላቲን ይፅፋሉ? ኤርትራውያንስ መቼ የግእዝን ቀለማት አሽቀንጥረው ጣሉአቸው? ከኢትዮጵያ ተገነጠሉ እንጂ መቼ ከፊደላችን ተገነጠሉ? እንዳውም እነሱ ቀደም ሲል በጣልያን ቅኝ ግዛት ተገዝተው ስለነበር በላቲን እንቸክችከው ቢሉ ጥሩ ሰበብ በሆናቸው ነበር። ከላቲን ይልቅ ኢትዮጵያውያኑ ፊደላት ብዙ ጥቅሞች እንዳላቸው በመገንዘባቸው ግን ፊደሎቻችን ላይ ሙጭጭ ብለው ይዘዋቸው ሄዱ። የኢትዮጵያ ፊደላት የሰሜን ሰዎች እና የአማራ ብቻ አይምሰለን። ባለፉት 4000 ዐመታት ከሁላችንም አባት ከኢትዮጵ ጀምሮ በነገሥታት ልጅ ልጆቹ እየተቀረፀና እየተሻሻለ ሲወርድ ሲዋረድ እዚህ የደረሰ ነው። ከቀዳማዊ ምኒልክ ጋር ወደ ኢትዮጵያ የመጡት አጋዝያን መደበኛ ፊደላቱን ኢትዮጵያ ውስጥ አግኝተው ለራሳቸው እንዲመቻቸው አድርገው ሞርደዋቸዋል። አማሮች ዘመዶቻችንም ለእነሱ አፍ የሚስማሙ የተወሰኑ ፊደላትን ቀርፀው እውስጣቸው አካተዋል። ስለዚህ ፊደላቱ የኦሮሞም ናቸው። በእርግጥም ናቸው
እንጂ ባይሆኑም እንኳ ከማናውቃቸው ከባእዳኑ ከአውሮፓውያኖቹ ፊደላት ይልቅ የተፈጠርንበት እና የኖርባት የኢትዮጵያ ፊደላት ለኛ ይቀርቡናል።
ከቡር ፕሬዚደንት ለማ መገርሳ ሆይ! በኢትዮጵያዊነት ስሜት እና ፍቅር መንደዶን እባህርዳር በነበሩ ጊዜ አሳይተውን ነበር። ኢትዮጥያዊነት የኢትዮጵያን ፊደላትንም ይጨምራል። ስለእዚህ ይህን ጉዳይ አተኩረው ያስቡበት። ከዛሬ 26 ዐመታት በፊት መጫፈ ቁልቁሉን ጨምሮ ኦሮምኛ በኢትዮጵያ ፊደላት እጅግ ብዙ ፅፎበታል። በእዚህ አጋጣሚ አንድ ጥያቄ እንዳቀርብ ይፈቀዱልኝና ባለፉት 26 ዐመታት በቁቤ ወይም በላቲን ፊደላት ምን ያህል የረባ መፃህፍት ተከትበዋል? ከኦሮሞ ሰፊው ህዝብ ውስጥስ ምን ያህሉ ነው በቁቤ የሚፅፍና የሚያነብ? ነው ወይንስ እንዳው ለወጉ ነው ቁቤ ቁቤ የምንለው? እዚህ ላይ ብርሃን የ ሚረጭ ጥናት ቢኖር እንዴት ሸጋ ነበር። ለማንኛውም ቁጥራቸው በዛም እነሰም ቁቤ የሚችሉ ሰዎች በግለሰብ ደረጃ አሁንም በቁቤ እንዳይገለገሉ የሚያግዳቸው የለም። ርስበርሳቸውም ሆነ ለየብቻቸው በቁቤ መጠቀማቸውን ሊቀጥሉ ይችላሉ። በሃገር ደረጃ ግን ከላቲን ይልቅ ግዕዝ በጣም በርካታ ጥቅም ስለአለው ነው ኦሮምኛ ሁለተኛ የፌዴራል ቋንቋ ሆኖ በግእዝ ፊደላት ይፃፍ ብዬ የምመክረው። ኢትዮጵያዊው ፊደል በሀገር ደረጃ ፀድቆ ከተገበረ ከመዋዕለ ህፃናት እና ከ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ሊደርስ ይችላል። በእድሜው የገፋውን አዛውንት ሳያስጨንቁ በህፃናቱ ቢጀመር ከ 20 ዐመታት በኋላ ለመጪው ትውልድ ይዳረሳል። ይህን ጉዳይ ለመተግበር ደሞ ለእርስዎና ለሃገር አስተዳደር ባልደረቦቾ ለወደፊቱ የኢትዮጵያ ህዝብ እሺታ እና ትብብር ያሻችኋል። ይህ በቶሎ የሚፈፀም ነገር ስላልሆነ ለጊዜው ቅዱሱ ሃሳቡ ይንሸራሽር።
ደብዳቤዬን ለመደምደም፣ የኦሮምኛ ተናጋሪ ሕዝብ ቁጥር በጣም በርካታ ስለሆነ ካናዳ ውስጥ እንግሊዝኛንና ፈረንሳይኛን የሥራ ቋንቋዎች አድርገው እንደሚሠሩባቸው ሁሉ በኢትዮጵያ ውስጥም ከአማርኛ ጎን ለጎን ኦሮምኛ በኢትዮጵያውያኑ ፊደላት እየተከተበ የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ሊተጋበት ይገባል። ከእዚህም በተጨማሪ፣ ጥቅሙ በተጨባጭ እየተመዘነ፣ አዋጭነቱ በሳይንሳዊ መንገድ እየተረጋገጠ፤ አማርኛን እንደ ሁለተኛ ቋንቋቸው በተቀበሉ እንደ ደቡብ ክልል ባሉ ሕዝቦች ላይ ጭነት አለመሆኑም እየተጣራ በጥንቃቄ ሊመከርበት ግድ ይላል፡፡ ኦሮሞ ያልሆኑ የ ኦሮሞ ቋንቋ ተናጋሪዎች እና ሌሎችም አያሌ ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ሰዐት ኦሮምኛን መማር ይፈልጋሉ። ዳሩ ግን በባእዱ ፊደል በላቲን ተማሩ ከምንላቸው ይልቅ ሁሉም በሚያውቁት በኢትዮጵያ ፊደላት እንዲማሩ ብናመቻችላቸው በቀላሉ ሊቀስሙት ይችላሉ። በግድ በላቲኑ ተማሩ ካልናቸው ግን፣ “ጊዜና ገንዘብ ከሚያባክነው ከላቲኑ ፊደል ይልቅ ቆጣቢ፣ ቀልጣፋና ምቹ በሆነውና በምናውቀው ባገራችን ፊደል እንጽፋለን” ቢሉ ይህ አቋማቸው በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ክቡር ፕሬዚደንት ለማ መገርሳ ሆይ! እርስዎ አንደሚገነዘቡት፣ በባዕዳን ፊደል የሚጽፉ አፍሪካውያን በአዎሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች ሲገዙ የነበሩና ራሳቸው የፈለሰፏቸው የፊደላት አማራጭ ያልነበራቸው ሕዝቦች ናቸው፡፡ እኛ በጀግኖች አባቶቻችንና እና እናቶቻችን ደም እና አጥንት ነፃነታችን ተከብሮልን የኖርንና አኩሪ ቅርስ የሆነ የራሳችን ፊደል ያለን ሕዝቦች ቅኝ እንደተገዙትና እንድተዋረዱት ያልታደሉ ሰዎች እድንሆን አይገባም። በእዚህ እና እላይ በተዘረዘሩት የአመክንዮ ምክንያቶች፣ እንዲሁም ስለክብራችን እና ማንነታችን ሲባል እርስዎና የአስተዳደር ባልደረቦችዎ ይህን የተቀደሰ ጉዳይ ትጉበት። ከዚያም ውጤቱ ለህዝባችን ልብ የሚያኮራ እና ለኑሮም የሚበጅ ይሆናል።
በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በኦሮሞው ፓስተር ኦነሲሞስ ነሲብ በግዕዝ ፊደላት መጫፈ ቁልቁሉ ተብሎ ከተተረጎመው የኦሮምኛ ቅዱስ መፅሃፍ ውስጥ የወሰድኳቸውን ሁለት ገፆች ከዚህ በታች አስፍሬለዎታለሁ። የዛሬ 120 እንኳን ቅዱስ መፅሃፍን የሚያህል በራሳችን ፊደላት መፃፍ ከቻልን ቀና ልቦና፣ በራስ ፊደል ኩራት እና ፍላጎት ከአለን አሁንማ በ ዘመነ-ኮምፒተር በቀላሉ ኦሮምኛን ግዕዝ በሚባለው ኢትዮጵያዊ ፊደል ያለችግር መክተብ እንችላለን።