ዶክተር አብይ አህመድ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ

ዶክተር አብይ አህመድ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና /፡- ባለፈው ማክሰኞ ኢህአዴግ ሊቀ-መንበር በመሆን የተመረጡት ዶክተር አብይ አህመድ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ተሹመዋል።

ዶክተር አብይ አህመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ቃለ-መሀላ በመፈጸምና ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ በይፋ የስልጣን ርክክብ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በቴሌዥን የቀጥታ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸውም የኢትዮጵያ የቀድሞ ታሪክ ጎልቶ የታየበት፣ ኢትዮጵያ አንድነት የተቀነቀነበት፣ የለውጥ ተስፋ የተሰነቀበትና በርካታ መልካም የሚባሉ ዓረፍተ ነገሮች የተሞሉበት ነበር።

ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር ከግማሽ ሰዓት በላይ በወሰደው ንግግራቸው ኢትዮጵያዊነት፣ አንድነትና ህብረት የሚሉ ቃላቶችን ደጋግመው ተናግረዋል። ዶክተር አህመድ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን ጠክረው እንደሚሰሩ፣ ከኤርትራ ጋር ያለውን ቁርሾ እንደሚፈቱ በንግግራቸው ቃል-ገብተዋል።

ከዚህ ቀደም በስርዓቱ ወታደሮች ለተገደሉት ወገኖችን አስመልክተውም “በተለያየ ጊዜ መስዋዕትነት ለከፈሉ የመብት ተከራካሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ በቅጡ ሳይቧርቁ ህይወታቸው ለተቀጠፈ ለውጥ ፈላጊ ወጣቶች ለስነ-ልቦናዊና አካላዊ ቀውስ ለተዳረጉ ቤተሰቦችና ግለሰቦች ከልብ የመነጨ ይቅርታ እጠይቃለሁ።” ብለዋል።

ዶክተር አብይ አህመድ ባልተለመደ ሁኔታ በህይወት ለሌሉት እናታቸውና ለባለቤታቸው ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል። እናቴ ከሌሎች ቅን፣ የዋህና ጎበዝ ኢትዮጵያዊያን እንደ አንዶቹ የምትቆጠር ናት። ቁሳዊ ሐብትም አለማዊ እውቀትም የላትም። በእናቴ ውስጥ ሁሉንም የኢትዮጵያ እናቶች ዋጋና ምሥጋና እንደመስጠት በመቁጠር ዛሬ በህይወት ከአጠገቤ ባትኖርም ውዷ እናቴ ምሥጋናዬ በአጸደ ነፍስ ይደርሳት ዘንድ በብዙ ክብር ላመሰግናት እወዳለሁ።” ብለዋል።

ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር ንግግራቸውን እንደጨረሱ አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አቀባበል አድርገውላቸዋል። በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የስልጣን ሽግግሩን አስመልክተው ዶክተር አብይ አህመድ በሰጡት አስተያየትም “ኢትዮጵያ የየእራሳቸውን አሻራ ያሳረፉ ታላላቅ መሪዎች ነበሯት፤ አፄ ሚኒሊክ ሀገራችን የዛሬዋን ቅርፅ እንድትይዝና በቅኝ ገዥ ወራሪ ሀይል እንዳትያዝ ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገዋል።

ንጉሱም በትምህርትና በዲፕሎማሲው ዘርፍ እስከ ዛሬ የዘለቀ መሰረት ጥለው ሄደዋል።” በማለት አስተያት ሰጥተዋል። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በወታደራዊ የደርግ አገዛዝ ወቅትም ለሀገር የሚጠቅም መልካም ስራ እንደተሰራ አረጋግጠዋል።

ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስት ከህዝብ ድጋፍ የተሰጠ ቢመስልም ድጋፉ ግን የገቡትን ቃል ወደ ተግባር መለወጥ እስከቻሉ ድረስ መሆኑን የፖለቲካ ሊህቃኑ ይናገራሉ።

ዶክተር አብይ አህመድ ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት ናቸው።

LEAVE A REPLY