/ኢትዮጵያ ነገ ዜና /፡- ዶክተር አብይ አህመድ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ትናንት መሾማቸውን ተከትሎ ደስታቸውን በተለያየ መንገድ የገለጹ ወጣቶች እየታሰሩ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ጠቁሟል።
ዛሬ በድሬድዋ ከተማ ተሰባስበው ደስታቸውን ሲገልፁ የነበሩ ወጣቶች ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈጸመባቸውና በአካባቢው በሚገኝ ወታደራዊ ካምፕ መታሰራቸው ታውቋል። በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች የአጋዚ ወታደሮች ሰብሰብ ብለው ደስታቸውን ለመግለጽ በሚሞክሩ ወጣቶች ላይ ከማስፈራት ጀምሮ ድብደባና እስራት እየተፈጸመባቸው መሆኑን ታውቋል።
በተመሳሳይ መልኩ በጋምቤላ ክልል አበቦ ወረዳ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር መመረጡን ምክንያት በማድረግ እናቶች ተሰባስበው ቡና በማፍላት ደስታቸውን በመግለጽ ላይ ከነበሩት አራቱ በአጋዚ ወታደሮች መታሰራቸው ተገልጿል። ከታሰሩት እናቶች መካከልም አንዷ ጡት የሚጠባ የአንድ ዓመት ህፃን ልጅ እናት መሆኗ ታውቋል።
ዶክተር አብይ ትናንት የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸውን ተከትሎ በቅርቡ አዲስ አበባ (እነ እስክንድር ነጋን)ና ባህር ዳር (ህጋዊ የአማራ ፓርቲ ለመመስረት ሲቀሳቀሱ የታሰሩትን) ላይ የታሰሩትን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ በግፍ የታሰሩት የህሊና እስረኞችን እንዲፈቱ በየአቅጣጫው እየተወተወቱ ባለበት በአሁኑ ወቅት ዛሬም ዜጎች ወደ እስር ቤት መጋዛቸው አሳዛኝ ያደርገዋል ተብሏል።
ወታደሩ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰበብ የህወሓትን የፖለቲካ ስልጣን ለማስጠበቅ ዜጎችን በግደል፣ ማሰርና በማሰደድ ቁልፍ ሚና እየተወጣ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን ትናንት የተሾሙት አዲሱ ጠ/ሚ የመጀመሪያው የቤት ስራቸው “አዋጁን” ማንሳት እንደሆነም የተለያየ ግፊት እየተደረገባቸው ነው። አዲስ አበባ የሚገኘው አሜሪካ ኤምባሲ ትናንት ባወጣው መግለጫ የዶክተር አብይ አህመድን ሹመት እንደተቀበሉና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ይነሳል ብለው እንደሚጠብቁ መግለፃቸው ይታወሳል።