/ኢትዮጵያ ነገ ዜና /፡- አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ዶክተር አብይ አህመድ ትናንት ለፓርላማ ባደረጉት ንግግር ከኤርትራ ጋር ለዓመታት ሰፍኖ የቆየውን የሰላም እጦት በውይይት እንዲፈታ ለኤርትራ መንግስት ጥሪ ባቅረባቸውን ተከትሎ ኤርትራ እንደማትቀበለው ገልጻለች።
የኤርትራ መንግስት ቃል አቀባይ የማነ ገብረመስቀል ለሲ.ጂ.ቲቪ እንደገለጹት የዶክተር አብይ ጥሪም አቶ ሀይለማርያም ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲመጡ እንደተናገሩት ተመሳሳይ ፍሬ የሌለው ንግግር ነው ብለውታል።
ቃል አቀባዩ አያይዘውም ሰላም ለሁለቱ ህዝቦች እንደሚጠቅም ጠቅሰው፤ በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ከ16 ዓመታት በፊት ለኤርትራ የተወሰነውን ውሳኔ ኢትዮጵያ ማክበር አለባት ብለዋል። ኢትዮጵያ ባድመን ጨምሮ በሀይል የያዘቻቸውን ግዛቶች ለቃ ካልወጣች የሚደረግ የሰላም ድርድር ወይም ውይይት አይኖርም ብለዋል።
ዶክተር አብይ ከኤርትራ መንግስት ጋር ለዓመታት ሰፍኖ የቆየዉን አለመግባባት እንዲያበቃና እሳቸውም ችግሩን ለመፍታት የበኩላቸውን እንደሚወጡ በትናንትናው ንግግራቸው አስታውቀዋል። የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደምም እንደተሳሰሩ ገልጸው፤ ለጋራ ጥቅም ሲባል ልዩነቶቻችንን በዉይይት ለመፍታት እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ የኤርትራ መንግስትም ተመሳሳይ አቋም እንዲወስድ በማለት ጥሪ ማቅረባቸው አይዘነጋም።
ለሁለት ተከታታይ ዓመታት በተካሄደው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ከ70,000 በላይ ወገኖች እንዳለቁበት ይነገራል።