ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር… ወድቆ ስለተነሳው ባንዲራ! ጓደኞቻችንን ፍቱልን! /ዳዊት ከበደ ወየሳ/

ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር… ወድቆ ስለተነሳው ባንዲራ! ጓደኞቻችንን ፍቱልን! /ዳዊት ከበደ ወየሳ/

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ለመጨረሻ ግዜ ሳወራው፤ በቅርቡ ባለቤት እና ልጁን ለማየት ወደ አሜሪካ እንደሚመጣ፤ በዚያውም ከ18 አመታት በኋላ እንደምንገናኝ ተስፋ አድርገን ነበር የተሰነባበትነው። ከዚያ በኋላ መታሰሩን ከባለቤቱ ሰርካለም ፋሲል ተረዳሁ። በቅርቡ እንደሚፈታ በማሰብ፤ ነገሩን ቀለል አድርገን ብንይዘውም ቀን አልፎ ቀን ሲተካ ግን፤ የነእስክንድር ነጋ ስቃይ እና መከራም እየበዛ በመምጣቱ፤ እርስዎም “ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር” በሚል ብዙ ደብዳቤ ማስተናገድ ከመጀመርዎ በፊት… ይህንን ደብዳቤ ለመጻፍ ተገደድን።

ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር… ወድቆ ስለተነሳው ባንዲራ! ጓደኞቻችንን ፍቱልን!

ይህ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ…

አጼ ቴዎድሮስ በካባቸው ላይ ያስጠለፉት፤ አጼ ዮሃንስ በመተማ የወደቁለት፤ ፊታውራሪ ገበየሁ ከሌሎች ጀግኖች ጋር በአድዋ ምድር ከፍ አድርገው የሰቀሉት፤ እንኳንስ ኢትዮጵያውያን የኩባ ወታደሮች ጭምር ከኢትዮጵያውያን ጋር በአንድ ምሽግ አብረው ተዋድቀው፤ በመጨረሻም በካራማራ ተራራ ላይ በአይበገሬነት ያውለበለቡት… ከሞታችን በፊት የነበረ እና ከሞታችን በኋላም እኛን ወክሎ የሚውለበለብ የክብራችን ምልክት ነው – ሰንደቃችን!!

ይህ ሰንደቅ አላማ…

ጣልያን ለአምስት አመታት ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት፤ ከተሰቀለበት ማማ ወርዶ… በግራዚያኒ የፋሺስት ወታደሮች ተዋርዶ ለጥቂት አመታት ያህል መቅኖ አጥቶ ነበር። በዚያን የፋሽስት ወረራ ወቅት ባንዲራ ይዞ የተገኘ ኢትዮጵያዊ የሚታሰርበትና የሚገደልበትን ዘመን አልፈን – ዛሬ ላይ ደርሰናል። ዛሬ ግን የጣልያን ፋሺስት ሳይሆን፤ የኢህአዴግ አንጋች እና አንጋሽ ሰዎች ይህንን ሰንደቅ አላማ በተለየ የጥላቻ መንፈስ በማየት፤ ይዞ የተገኘን ሰው በግፍ ገድለዋል፤ በህግ ሽፋን አስረዋል።

ይህም ሆኖ ታሪክ እናውጋቹህ። በአምስቱ የጣልያን ፋሽስት ወረራ ወቅት… አርበኞች በዱር በገደል የሚያውለበልቡት ይህንን ሰንደቅ አላማ ነበር። በላይ ዘለቀ በጎጃም፣ እነአቢቹ በሸዋ፣ እነ ደጃች ገረሱ ዱኪ፣ እነጃጋማ ኬሎ፣ እነራስ አበበ አረጋይ፣ ጣልያን ያወረዳትን ሰንደቅ አላማ ከወደቀችበት አንስተው፤ ከፍ አድርገው እያውለበለቡ ስለኢትዮጵያ ክብር ተፋልመዋል። ብዙዎች በህይወት እያሉ ኢትዮጵያዊ፤ ሲሞቱ ኢትዮጵያ ይሁኑ እንጂ፤ ከመቃብራቸው በላይ ግን ይህ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ሰንደቅ አላማ ነው የሚውለበለበው።

ከአምስት አመታት የአርበኝነት ትግል በኋላ… በኢትዮጵያውያን ከፍ ያለ ተጋድሎ የድል ቀን ሲቃረብ፤ ገና በዋዜማው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በሱዳን ድንበር በኩል ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ፤ ኦሜድላ ላይ የሰቀሉት ይህን ሰንደቅ አላማ ነው። መጋቢት 28፣ 1933 ዓ.ም. ጣልያን ከአዲስ አበባ ተፈጽሞ ወጥቶ፤ በምትኩ አርበኞች ወደ ዋናው ከተማ ሲገቡ፤ ገብተውም ሲያበቁ የጣልያንን ባንዲራ አውርደው የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ሲሰቅሉ፤ እንኳንስ የምድር ፍጡራን ቀርቶ፤ እንኳንስ ነፍስ ያላቸው እንሰሳትና አእዋፍት ቀርተው የሰማይ መላዕክት ጭምር በይባቤ የዘመሩ ይመስል፤ አገር ምድሩ በደስታ ተፍነክንኮ ነበር። ሚያዝያ 27 ቀን ቀዳማዊ ኃይለስላሴ አዲስ አበባ በክብር በገቡበትም ወቅት ይኸው ሰንደቅ አላማ፤ ስለኢትዮጵያ ነጻነት ከወደቀበት መሬት ተነስቶ በብዙ ክብር ዳግም በኢትዮጵያ ምድር ላይ ተሰቅሎ በአየሯ ካይ ተውለብልቧል።

በአፋር “እንኳንስ እኛ ግመላችን ያውቃታል” የተባለላት፤ ከሞ ያሌ ድንበር እስከ ጋምቤላ ጫፍ… ከዱራሜ እስከ ባህር አጽናፍ ሲውለበለብ የኖረ፤ ዛሬም ድረስ ከሸዋ እስከትግራይ ድረስ – ህዝብ በሰርግ እና በሃዘን ግዜ በክብር የሚሰቅለውና የሚያውለበልበው ሰንደቅ አላማ ነው ያለን። ይህ ወድቆ በክብር የተነሳ ሰንደቅ አላማ… ሮም ላይ በአበበ ቢቂላ፤ በቶኪዮ እና ሜክሲኮ፤ አትትላንታና ሞስኮ ላይ… በኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ጀግኖች ምክንያት ከፍ ብሎ ተውለብልቧል – ሰንደቅ አላማችን።

እኛ ኢህአዴግ በሰንደቅ አላማችን ላይ የለጠፈውን ኮከብ እና ክብ መስመር የማንቀበልበት አንደኛው ምክንያት፤ በአለማችን ላይ የሚገኙ የሰይጣን እምነት ተከታዮች የሚጠቀሙበት የአምልኮ ምልክት ስለሆነ ጭምር ነው። እነእስክንድር ነጋ የአምልኮ ኮከብ የሌለበት ሰንደቅ አላማ ከጀርባቸው ስለነበር፤ ዛሬ እንደወንጀለኛ ተቆጥረው… በተፈቱ ማግስት ዳግም ለእስር ተዳርገዋል። እንደው ግን ለጠቅላላ እውቀት ያህል… የፍትህ መክሊታችሁን ሰብራቹህ ስታበቁ፤ በምን የህግ ሚዛን ላይ ሆናቹህ፤ በማን ላይ ትፈርዳላቹህ? ዜጎችን በዚህ አይነት መንገድ ማሰር እና ማሰቃየትስ በምን መመዘኛ ትክክል ሊሆን ይችላል? አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለም ባለበት አካባቢ መገኘት የሚያሳስር ከሆነ፤ ቀስተ ደመናን ከጀርባው አድርጎ ፎቶ መነሳት የሚፈራ ትውልድ እየፈጠርን መሆኑን ልብ ብለነዋል?

እናም ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ሆይ…

ይህ ሰንደቅ አላማ አረንጓዴው ልምላሜ፣ ቢጫው ነጻነት እና ተስፋ፤ ቀዩ ደግሞ በጀግኖች ደም መስዋዕትነት የቆየችው ኢትዮጵያ አገራችን ምሳሌ ነው። ሌላ ትርጉም የለውም። የህዝብን አንድነት ለማሳየት እኮ፤ ቀዩ ቀለም የደም መስዋዕትነታችን ምሳሌ ስለሆነ፤ እሱ ብቻውን በበቃን ነበር። ቢጫውም ተስፋችን፣ አረንጓዴውም ልማታችንን የሚወክል በመሆኑ ከዚህ አልፈን፤ ኮከብ ቆጣሪ ይመስል፤ የኮከብ ስዕል በሰንደቅ አላማ ላይ ማንቆጥ አልነበረብንም።

ይህን አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ሰንደቅ አላማ እንኳንስ በምድር የሚገኙ ጠላቶቻችን ቀርተው፤ ሰይጣንም እንደማይተኛለት ያወቅነው ግን፤ በአርማው ላይ ሌላ አርማ በግድ በተጨመረበት ወቅት ነው። እንደእውነቱ ከሆነ የህዝብ እኩልነት የሚለካው፤ በሰንደቅ አላማ ላይ በሚቀመጥ ስዕል ሳይሆን በተግባር በሚገለጥ ስራ ሊሆን ይገባዋል። ዛሬ ኮከብ ያለበትን ባንዲራ ባየን ቁጥር፤ ኢህአዴግ በለጋ እድሜያቸው በግፍ የገደላቸው ህጻናት እና ወጣቶች፤ የተሰቃዩ፣ የተገፉና የታሰሩ ዜጎች ናቸው የሚታወሱን። ከግፍ ሁሉ የባሰው ግፍ ደግሞ፤ ኮከብ የሌለበት ሰንደቅ አላማ ስንይዝ መታሰራችን፤ ኮከብ ያለበትን ባንዲራ ደግሞ እንድናመልክ መጠየቃችን ነው – ከግፍ ሁሉ የባሰው ግፍ።

ለማጠቃለል ያህል… ኮከብ ያለበት የአምልኮ ባንዲራ በመንግስት መስሪያ ቤቶች ወይም እነሱ ከሚወክሏቸው ሰዎች በስተቀር፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ትላንትም ሆነ ዛሬ፤ ነገም ሆነ ከዚያ ወዲያ ንጹህ የሆነውን ሰንደቅ አላማ ነው የሚያውቀው። መራር የሆነው እውነት ያለው ግን ወዲህ ነው። እኛ ኮከብ ያለበትን ባንዲራ ስንመለከት፤ በግፍ የተገደሉ ንጹሃን ወገኖቻችንን በአይነ ህሊናችን ይመላለሳሉ። ምንም አርማ የሌለበትን ሰንደቅ አላማ ስንመለከት ደግሞ፤ ይህችን አገር በጀግንነት ያቆዩ አባቶቻችን ይታወሱናል። በአጭሩ የሰንደቅ አላማችን ትርጉም… ለአረንጓዴ ልማቷ ሲባል፤ በነጻነት የቆመችን አገር በደም መስዋዕትነት ማቆየት ማለት ነው።

ይህን ሰንደቅ አላማ ነው… አያት ቅድማያቶቻችን ያወረሱን። በመተማ ሆነ በአድዋ፤ በካራማራ ሆነ በባድሜ… ይህ ሰንደቅ አላማ ነው ከፍ ብሎ በኢትዮጵያ አየር ላይ የተውለበለበው። ዛሬም ተስፋ አንቆርጥም። ይህ ሰንደቅ አላማ በህይወት ሳለን ለኢትዮጵያ፤ ስንሞት ደግሞ በኢትዮጵያ የሚነግስ ታላቅ ክብራችን ነው። ስለሆነም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በክብር ስለተወሳው፤ ትላንት ወድቆ ዛሬ ስለተነሳው፤ ተነስቶም በክብር ስለተሰቀለው ሰንደቅ አላማ ብላቹህ… እባካችሁ ጓደኞቻችንን ፍቱልን!

LEAVE A REPLY