ማዕከላዊ የወንጀል ምርመራ ማዕከል መዘጋቱ ተገለጸ

ማዕከላዊ የወንጀል ምርመራ ማዕከል መዘጋቱ ተገለጸ

ታዬ ደንደአና መምህር ስዩም ተሾመ ወደ ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ መዘዋወራቸው ተገልጿል!

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ለዘመናት በቁም ይሰቀሉበት የነበረው ማዕከላዊ የወንጀል ምርመራ ማዕከል ከዛሬ ጀምሮ መዘጋቱ ተገለጸ።

በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ወቅት በጣሊያን ዲዛይነሮችና ኮንትራክተሮች እንደተገነባ የሚነገርለት ማዕከላዊ፤ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን “የፖሊስ ሠራዊት ልዩ ምርመራ” ተብሎ ይጠራ እንደነበር መዛግብት ይገልፃሉ። ማዕከላዊ በውስጡ በርካታ የምርመራና የማጎሪያ ክፍሎችን ያጨቀ ሲሆን የቦታ ስፋቱም በ8 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ላይ ያረፈ እንደሆነ ይነገራል።

ማዕከላዊ የተገነባው ድንጋይ በድንጋይ በመሆኑ በዚያ የሚታሩ ሰዎች ለከፍተኛ ቅዝቃዜ ይጋለጣሉ። በማዕከላዊ ማሰቃያ ቦታ ከደርግ ዘመን ጀምሮ ላለፉት 40 ዓመታት በርካታ ዜጎች በሚደርስባቸው ከባድ ድብደባ ህይወታቸው ጠፍቷል፤ አካላቸው ጎድሏል፤ ለከፍ ስነ-ልቦናዊ ጫና እንደሚጋለጡም ይታወቃል።

የስርዓቱ የሚዲያ ተቋማት ዛሬ እንደዘገቡት የማሰቃያ ማዕከሉ ከዛሬ ጀምሮ የተዘጋ ሲሆን እየተመረመሩ የነበሩ እስረኞችም ሙሉ በሙሉ ወደ ሌላ እስር ቤት መዘዋወራቸውን ገልጸዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ የታሰሩት የአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህሩና ጦማሪ ስዩም ተሾመ እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል ፍትህ ቢሮ የህ/ግንኙነት ሀላፊ የነበረው ታዬ ደንደአን ጨምሮ 31 ማዕከላዊ የነበሩ እስረኞች ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን (3ኛ ፖሊስ ጣቢያ) መዘዋወራቸውን ከቅርብ ምንጮች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

LEAVE A REPLY