ማዕከላዊ ሳይቨርያ “ጨለማ ቤት” ወለሉን በእግራችሁ ስትመቱት ጩኸት ይሰማል። እንደከበሮ ይጮሃል። ልክ ውስጡ ባዶ እንደሆነ ድምፅ ያሰማል። ማዕከላዊ የሚባል የሰቆቃ ቤት ውስጥ፣ ያውም ከጨለማ ቤቱ ስር መዝናኛ ይኖረዋል ተብሎ አይታሰብም። “ግራውንድ” የሚባል ማሰቃያ ነው ብለን እናምን ነበር! እኔ አሁንም ድረስ አምናለሁ።
ነገሮች ሲከብዱ፣ ብርሃንና አየር ሲያጥር፣ መዘጋቱ ሲበዛ ወለሉን በእግራችን እንመታዋለን። በድምፁ ልንዝናና አይደለም። እንዲያው ሰው ካለበት፣ (ደግሞም ይኖርበታል ብለን እናምናለን) ሰው የሚባል ከላያቸው ላይ እንዳለ ይፅናኑ ዘንድ ነው። እንዲያው ከእኛ የባሰ ግራውንድ የታሰረ እንዳለ አስበን ሳይቬርያ የቅንጦት ቤት ነው ብለን ራሳችን ለማፅናናት ነው!
የግራውንድ እስር ቤት ነገር!
ሁለት ወር ከ18 ቀን ሳይቨርያ ቆይታ በኋላ፣ በቆርቆሮና ቆርቆሮ ማህል ሰማይ ወደሚታይበት “ሸራተን” የሚባል እስር ቤት ተዛውሬያለሁ። (ሳይቬርያ ይህ ዝርጉ ሰማይም ይናፍቃል፣ ሸራተን የተባለው ሰማይን በጠባቡ ማየት ስለሚያስችል ነው) ከቀናት በኋላ ማዕከላዊ ቁጥር 27 ምርመራ ቢሮ ተጠራሁ። ስገባ 6 መርማሪዎች ተቀምጠዋል።
ብዙ ብዙ ካወራን በኋላ:_
አንዱ መርማሪ:_ “ጌታቸው እንፈታሃለን፣ ስትወጣ ግን የሆነ ያልሆነ እንዳትፅፍ”
እኔ:_ “ያልሆነውን አልፅፍም፣ የሆነውን ግን እፅፋለሁ”
መርማሪው:_ “የሆነው ምንድን ነው?”
እኔ:_ “ሰው ሲደበደብ አይቻለሁ”
መርማሪው:_ “ማን ተደበደበ? ምን አየህ?”
እኔ :_ “ተስፋዬ ሊበን …… ተደብድቧል፣ ጌቱ ግርማ… …” ሌላም፣ ሌላም
መርማሪው:_” ይህማ በስታስቲክስ ነውኮ የያዘው፣ እሽ እሱን ተወው ጌታቸው! ከሚታዩት እስር ቤቶች ውጭ የምታውቀው እስር ቤት አለ?”
እኔ:_ ግራ ገብቶኛል። ስለዛ ሚስጥር እንዲህ ይገልፅልኛል ብየ አላሰብኩም። ጆሮዬን ማመን አቅቶኛል። “አልገባኝም?” አልኩት!
መርማሪው:_ ” ግቢ ውስጥ ሳይቬርያ፣ ጣውላ ቤት፣ 8 ቁጥር፣ ሸራተን ከምትሏቸው ውጭ ሌላ እስር ቤት ታውቃለህ?” የፈጣሪ ያለህ!
እኔ:_” እርግጠኛ አይደለሁም”።
መርማሪው ከዚህ ውጭ ጥያቄ አልቀጠለም። ጥያቄውን ይቀጥላል ብየ አስቤ ነበር። ለምን እርግጠኛ እንዳልሆንኩ ቢጠይቀኝ ሳይቬርያ ሆነን ከስር ግራውንድ ውስጥ ታጉረዋል ብለን ስለምናስባቸው በእግራችን የምንልከውን መልዕክት እነግረው ነበር። እሱም ተጨማሪ ፍንጭ ይሰጠኝ ነበር። በእርግጥ በቂ ነው። መርማሪው ከሚታወቁት ውጭ ሌላ እስር ቤት መኖሩን ስለማወቅ አለማወቄን የመጠየቁ ሚስጥር ግልፅ ነው። የጠየቀኝ ስለ ግራውንዱ ነው።
ያን ቀን “የሆነ ያልሆነ ነገር እንዳትፅፍ” ሲሉኝ ” የማውቀውም እፅፋለሁ” በማለቴ ደሰ አልተሰኙምና እንደሚከሱኝ አውቅ ነበር። ከሰሱኝ!እሱ ግን አላሳሰበኝም ነበር። ከሳይቨርያ ከወጣ በኋላ ግን ያን እንረግጠው የነበረውን እስር ቤት አስታወሰኝ። በእግሬ ደብድቤ አላስታውሳቸው ነገር ወደ ሸራተን ተቀይሬያለሁ። ማዕከላዊ ይዘጋል በተባለ ቁጥር እነዛን “አሉ የሉም” የምንላቸው ፍጡራን አስታውሳለሁ!
ሌላም! ማዕከላዊ ይዘጋል በተባለ ቁጥር ማዕከላዊ ጥፍራቸው ተነቅሎ፣ ብልታቸውን አኮላሽተዋቸው፣ አካላቸውን አጉድለዋቸው በሌላ እስር ቤት እየተሰቃዩ ያሉትን አስታውሳለሁ! 20 ጥፍሩን ተነቅሎ፣ ብልቱ ተኮላሽቶ ቃሊቲ ያለውን አበበ ካሴን አስታውሳለሁ። ብልቱ ተኮላሽቶ “አኮላሹኝ” ብሎ ሱሪውን አውልቆ በፍርድ ቤት መከራውን በማሳየቱ ቂሊንጦ ጨለማ ቤት የገባውን አስቻለው ደሴን አስታውሳለሁ። እግሩን ያሰለሉትን ዮናስ ጋሻውን አስታውሳለሁ።
በኤሌክትሪክ ጠብሰው የነርቭ በሽተኛ እንዳደረጉት የነገረኝንና ቂሊንጦ የሚገኘውም ዘርዓያቆም አዝመራውን አስታውሳለሁ። የተነቀሉ ጥፍሮች፣ የተኮላሹ ወጣቶች፣ “አንተ አማራ፣ አንተ ኦሮሞ፣ አንተ ጉራጌ……” የተባሉ ግፉአንን አስታውሳለሁ፣ እንደፋሲካ በግ ተሰቅለው የተገረፉ ንፁሃንን አስታውሳለሁ። ደርግን ጥሎ ከደርግ የባሰ በደል የፈፀመውን ግፈኛ አገዛዝ አስታውሳለሁ!
……እናማ……
ማዕከላዊ የተሰቃዩት እስካልተፈቱ ማዕከላዊ አልተዘጋም፣ የቤት ለውጥ ነው!
ማዕከላዊ የቆሰሉት በአካልም፣ በመንፈስም እስካልታከሙ ድረስ ማዕከላዊ አልተዘጋም፣ የቢሮ ለውጥ ነው!
ኢህአዴግ “ሰርቄያለሁ” እንደሚለው፣ ” የመልካም አስተዳደር ችግር አለብኝ” እንደሚለው “ማዕከላዊን እኔም ገርፌበታለሁ፣ አኮላሽቼበታለሁ፣……ግራውንድ ውስጥ አስሬበታለሁ……” ብሎ እስካላመነ ድረስ፣ ማዕከላዊ አልተዘጋም! የቢሮ ለውጥ ነው! ተግባሩ አልፈረሰም!
ማዕከላዊ አልተዘጋም! ማእከላዊ ይዘጋ!
ተግባሩም ይቁም!
የተጎዱት ይፈቱ! ይካሱ!
ትህነግ/ኢህአዴግ የፈፀመውን ይመን!