/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ከስርዓቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በመሆን ዛሬ ወደ ጅጅጋ ከተማ አምርተው ከአካባቢው ህብረተሰብና ከክልሉ ባለስልጣናት ጋር ተወያዩ።
ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ወደ ጅጅጋ ካመሩት ከፍተኛ ባለስልጣናት መካከል አቶ ደመቀ መኮንን፣አቶ ለማ መገርሳ፣ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ አቶ አባዱላ ገመዳ፣አቶ ከበደ ጫኔና ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ይገኙበታል።
እየተባባሰ የመጣውን የሁለቱን ክልሎች ግጭት ከጀርባ በመሆን እንደሚመሩት በተደጋጋሚ የሚነገርላቸው የህወሓት ባለስልጣናት አንድም ሰው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር አለማምራቱም ታውቋል።
በኢትዮጵያ ሶማሌና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ የተፈጠውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታትና የተፈናቀሉ ዜጎችንም በአጭር ጊዜ ለማቋቋም እንደሚሰሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንዖት ሰጥተው መናገራቸውን የመንግስት ሚዲያዎች ዘግበዋል። በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተደጋጋሚ በሚቀሰቀሱ ግጭቶች በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ህይወታቸውን ሲያጡ፤ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ኦሮሞች ተፈናቅለው በመጠለያ ካምፕ ውስጥ እንደሚገኙ ይታወቃል።