ጠ/ሚር አብይ በኢትዮ-ሱማሌ ክልል ጉብኝታቸውን አጠናቀው አምቦ ገብተዋል

ጠ/ሚር አብይ በኢትዮ-ሱማሌ ክልል ጉብኝታቸውን አጠናቀው አምቦ ገብተዋል

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ከስርዓቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በመሆን ወደ ጅጅጋ ከተማ አምርተው ከአካባቢው ህብረተሰብና ከክልሉ ባለስልጣናት ጋር ከተወያዩ በኋላ አምቦ ገብተዋል።

እየተባባሰ የመጣውን የሁለቱን ክልሎች ግጭት ከጀርባ በመሆን እንደሚመሩት በተደጋጋሚ የሚነገርላቸው የህወሓት ባለስልጣናት አንድም ሰው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር አለማምራቱም ታውቋል።

በኢትዮጵያ ሶማሌና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ የተፈጠውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታትና የተፈናቀሉ ዜጎችንም በአጭር ጊዜ ለማቋቋም እንደሚሰሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንዖት ሰጥተው መናገራቸውን የመንግስት ሚዲያዎች ዘግበዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ወደ ጅጅጋ ካመሩት ከፍተኛ ባለስልጣናት መካከል አቶ ደመቀ መኮንን፣ አቶ ለማ መገርሳ፣ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ አቶ ከበደ ጫኔና ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ይገኙበታል። ሁሉም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አመራር በቦታው ሲገኙ የህወሀት ባለስልጣናት በዚህ የእርቅና ውይይት ጉዞ ላይ ያልተካተቱት በምን ምክንያት እንደሆነ አለመገለፁ ያሳሰባቸው አስተያየት ሰጪዎች በእንደዚህ አይነቱ ተመሳሳይ ጉዞ ላይ በተለይ ዶ/ር አብይ እና አቶ ለማ መገርሳ በአንድ አውሮፕላን ጉዞ ማድረግ እንደሌለባቸው ጠቁመዋል።

በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተደጋጋሚ በሚቀሰቀሱ ግጭቶች በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ህይወታቸውን ሲያጡ፤ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ኦሮሞች ተፈናቅለው በመጠለያ ካምፕ ውስጥ እንደሚገኙ ይታወቃል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ላለፉት 3 ዓመታት የጦር አውድማ ሆና በከረመችው አምቦ ከተማ ገብተዋል። የጠ/ሚኒስትሩ የጉዞ አላማም ከአምቦ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ጋር ለመወያየት መሆኑን ተገልጿል። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የስርዓቱ ከፍተኛ ባለስልጣናትም አብረዋቸው እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን በወቅታዊ የሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ንግግር እንደሚያደርጉም ታውቋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ያወጣው መርሃ-ግብር እንደሚጠቁመው ዶክተር አብይ ነገ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በአዲስ አበባ ይወያያሉ፤ከነገ ወዲያ አርብ ደግሞ ወደ ትግራይ እንደሚያመሩ እንዲሁም እሁድ በአዲስ አበባ ሚሌኒየም አዳራሽ ከመላ ሀገሪቱ ከተወጣጡ ወጣቶች ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባሳለፍነው ሳምንት በሶማሌ ክልል የመጀመሪያውን የስራ ጉብኝታቸውን ቢያደርጉም ትችት እየቀረበባቸው ነው።

LEAVE A REPLY