/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝ እንዲሻሻል፣ ሁሉን አቀፍ ህዝባዊ መንግስት እንዲመሰረት፣ የመገናኛ ብሁሃን ነጻነት እንዲከበር፣ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ፣ አፋኝ አዋጆች እንዲሰረዙና ሌሎች ድንጋጌዎችን ያካተተው H.R. 128 የተባለው ረቂቅ ህግ ትናንት በአሜሪካ ም/ቤት ከፍተኛ ድምፅ በማግኘት አለፈ።
የህጉ መጽደቅ የኢትዮጵያ ህዝብ እያካሄደ ያለውን የነጻነት፣ የፍትህና የእኩልነት ትግል ላይ አውንታዊ አስተዋፅዖ ያደርጋል ተብሎም ይጠበቃል።
በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች የተገደሉ፣ በቂሊንጦ እስር ቤት የእሳት ቃጠሎ ምክንያት የተገደሉና እ.ኤ..አ ጥቅምት 2/2016 በእሬቻ በዓል በሚከበርበት ወቅት የተገደሉ ንጹሃን ዜጎች በተባበሩት መንግስታት አጣሪ ኮሚቴ እንዲመረመር H.R.128 ግፊት እንደሚያደርግ ተገልጿል።
በኒውጀርሲ የህዝብ ተወካይ ክሪስ ስሚዝ ከዲያስፖራ ኢትዮጵያዊያን ጋር በመተባበረር የተረቀቀው H.R.128 በሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በግድያና ተያያዥ ወንጀሎት የተሳተፉ የወያኔ ባልስልጣናት ወደ ሀገረ አሜሪካ እንዳይገቡ ገደብ የሚጥልና በዚያው የሚገኝ ሀብት ንብረታቸውም እንዲታገድ እድል የሚሰጥ መሆኑ ታውቋል።
በአሜሪካ ምክር ቤት (Congress) በከፍተኛ ድምጽ የጸደቀው H.R.128 ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለመሆን በሁለቱም ምክር ቤቶች መጽደቅ ስለሚኖርበት በቅርቡ ወደ አሜሪካ ሴኔት ተመርቶ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል። በመሆኑም በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እስካሁን ያደረጉትን ጥረት አሁንም አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ ቀርቧል።