/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- በየአምስት ዓመቱ የሚካሄዱ የምክር ቤትና የአካባቢ ምርጫዎች ተራዘሙ። በመላ ሀገሪቱ በየዓምስት ዓመቱ የሚካሄዱ የአካባቢ ምርጫዎች እንዲሁም የአዲስ አበባና የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር የምክር ቤት ምርጫዎች ወደ 2011ዓ.ም እንዲራዘሙ ተወስኗል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ዘንድሮ (2010 ዓ.ም) መካሄድ የነበረባቸው ምርጫዎችን እንዲያራዝም የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ በመቀበል በአብላጫ ድምጽ ማጽደቁን አስታውቋል። ምርጫውን ለማራዘም እንደ ምክንያት የቀረበውም በመላ ሀገሪቱ የተከሰተው የጸጥታ መደፍረስ በመሆኑም ተገልጿል።
በዚህም የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማትና በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚሰሩ ተቋማት የምርጫውን መራዘም ተቃውመዋል። ከተቃወሙትም መካከል የሂዩማን ራይትስ ዎች (Human Rights Watch) የምስራቅ አፍሪካ ተመራማሪ የሆኑት ፈሊክስ ሆርን ይገኙበታል። የምርጫው መራዘም አስመልክተው በቲውተር ገጻቸው ላይ “መፍትሄው ምርጫን ማራዘም ሳይሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማንሳት ነው” ብለዋል።