አምቦ ትናንትና ዛሬ! /ከአንተነህ መርዕድ/

አምቦ ትናንትና ዛሬ! /ከአንተነህ መርዕድ/

(ሚያዝያ 2018)

አምቦ ስሟ ሲጠራ የብዙዎቻችን ልብ በሃሴት እንደሚሞላ ሁሉ ወያኔዎችና አሽቃባጮቻቸው አጥንታቸው ድረስ የሚዘልቅ ብርድ እንደሚሰማቸው ግልፅ ነው። ያች ምድር የብዙ ጀግኖች መፈጠርያ ናት። ጣልያንን ብርክ ያስያዙ ጀግኖቿን ታሪክ ሲያስታውሳቸው ቢኖርም ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው የአባቶቻቸውን ጋሻ አንስተው የሃገር ጠላት የሆነን ስርዓት በመፋለም ለሌላውም አንቂና አበረታች ሆነው እነሆ እነሱም ታሪክ ሠሩ። አምቦዎች ወያኔን መፋለም የጀመሩት ገና ከመጀመርያው ነው። ከሁሉም በላይ ባለፈው ሶስት ዓመት የአምቦና የአካባቢ ጀግኖች ፣ ቄሮዎች የለኮሱት አመፅ መላ አገሪቷን ከዳር ዳር አዳርሶ እነሆ ዲያስፖራንም አነቃንቆ HR 128 በማስወሰን በወያኔ አንገት ገመድ አጥልቆለታል።

አምቦና ወያኔ ዐይንና ናጫ ናቸው። ወያኔ በጎንደር፣በጎጃምና በወለጋ አቆራርጦ ሲገሰግስ ሊሞት አንድ ሃሙስ የቀረው ደርግ ምንም ሊያደርግ ባልቻለበት ቀውጢ ወቅት የአምቦና የአካባቢው ህዝብ ተቋቁሞታል። ሰራዊቱ በፍርሃት ወደ አዲስ አበባ ሲያፈገፍግ ሴት ወንዱ ወጥቶ የወያኔን ሃይል ብቻውን በመቋቋም ብዙዎችን ገድሎ ከፊሉን ማርኮ ከተማውን ነፃ ከማድረጉ ቀድመው ከገቡ የጋዜጠኞች ቡድን አንዱ ሆኜ ጀግንነታቸውንና አገር ወዳድነታቸውን በተግባር ሲያሳዩ ለመታዘብ እድሉን አግኝቻለሁ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አምቦ ልቤ ውስጥ ናት።በዚያ ቂም ይመስላል ወያኔዎች የአምቦን ህዝብ በተለየ መልክ ፍዳውን ሲያሳዩት የቆዩት። የበርካቶቹን ህይወት በከንቱ ቀጥፈዋል።የኦነግና ሌላም ስም እየተሰጣቸው፣ የሚታሰሩ፣ የሚታፈኑ፣ የሚገረፉ፣ ሃብታቸው የሚነጠቅ ቁጥር ቀላል አይደለም(የነአቶ ደራራ ሞት) ሁሉ አምቦ እንድትከፍል የተጣለባት እዳ ውጤት ነበር። አምቦን ደግሜ ያየኋት ደግሞ ማዕከላዊ ውስጥ ነው። በአቶ ደንደናና ጓደኞቻቸው።

አቶ ደንደና ጉርሙ የአምቦ ሰው ናቸው። መካከኛ ቁመትና ሙሉ ሰውነት አላቸው። ፊታቸው ያሳለፉትን ሰባዎቹ ዓመታት አሻራ ለመተው በያቅጣጫው መስመር አበጅተው ፈገግ ሲሉ ሆነ ኮስተር ሲሉ ልዩ ውበት ያላብሷቸዋል። ፈገግታ የማይለያቸው ብቻም ሳይሆን ካፋቸው ለዛ ያለው ጨዋታ ስለማይታጣ ኦሮምኛ የሚችል ሁሉ ቀርቦ ሲኮመኩም ሌሎቻችንም ኦሮምኛ ባንችልም እሳቸው በፈጠሩት ገራገር ድባብ ደስታ ይሰማን ነበር። ኦሮምኛና ትግርኛ ለመማር ምን ጊዜም ፍላጎት ነበረኝ። የአባ ደንደናን ጨዋታ ያለአስተርጓሚ መስማት ባለመቻሌ ግን የቆየ ቁጭቴን አባሰው።

የቋንቋ ጉዳይ ከተነሳ አዲስ አበባ ዩኒበርስቲ ዶርሚቶሪ (ምኝታ ቦታ) ከሚጋሩኝ ሶስት ጓደኞቼ አንዱ ከነቀምት ሁለተኛው ከጉራጌ ሌላው ከመቀሌ ነበሩና እንደዛሬ የጎሳ ፖለቲካ ሳይሸነሽነንና ሳይለያየን እንደልብ እንቀላለድ ነበር። እነዚህን ወንድሞቼን ከልብ ስለምወዳቸውና ቋንቋቸውንም ማወቅ ስለምፈልግ “እኔ የምመኘው አንድ ዓመት ኦሮምኛ በሚነገርበት ሌላ አንድ ዓመት ደግሞ ትግርኛ በሚነገርበት ቦታ ሄጄ ለመስራትና ቋንቋዎቹን መማር ነው” ስል ኦሮሞው ጓደኛችን “ትግርኛ ለመማር ለምን መቀሌ መሄድ ያስፈልግሃል? ይልቅስ ኦሮምኛ በሚነገርበት አካባቢ ሄደህ ቋንቋውን ብትማር ነው የሚሻለው”፤ ሲለኝ ተሎ ደሙ የሚፈላው የመቀሌዋ ልጅ “ለምን ትግርኛ መማር አያስፈልገውም?” ብሎ ከልቡ ተቆጣ። ቀዝቃዛው የነቀምቴ ሸበላ “ትግርኛ ጉሮሮን በእጅ ይዞ አማርኛ መናገር ስለሆን እዚያ ድረስ ምን አለፋው?” ሲል ሁላችንም እንባችን ጠብ እስኪል ሳቅን። በዚህ አላበቃም “አንተነህ ኦሮምኛንም ቢሆን በቀላሉ ነቀምት ሄደህ በርካሽ እንድትሸምተው አልፈልግም። አማርኛን የተማርሁት በቄስ ትምህርት ቤት ደረቁ ጆሮዬ እንዲህ እንደጨርቅ እስኪሳሳ በመምህሩ እየታሸ ስለነበረ አንተም ያንን መንገድ እንድታልፈው እፈልጋለሁ” አለኝ። በዚያም መንገድ ቢሆን ተምሬ የአባ ደንደናን ጨዋታ ከነመረቁ ባገኝው ምንኛ ደስ ባለኝ!

አቶ ደንደና ጉርሙም ሌላ ወንጀል አልሠሩም። የአምቦ ህዝብ በተለያየ መንገድ እንዲቀጣ ስለተፈለገ ሰለባ ሆኑ። የአምቦ አድባር ሆነው መገኘታቸው ብቻ በወያኔ ወንጀለኛ አደረጋቸው። በ1988፣ 1989 እንዲሁም 1990 ዓ ም ማዕከላዊ፣ፖሊስ ጣብያዎችና ከርቸሌ በታሰርሁ ቁጥር እስር ቤቶቹ በእነዚህ ደጋግና ግፍ በሚፈጸምባቸው ሰዎች የተሞሉ ናቸው። አቶ ደንደናንም ማዕከላዊ ያገኘሁኣቸው በ1989 ዓ ም ነው። እኒህ ደግ አዛውንት ለበርካታ ጊዜ አምቦና ማዕከላዊ ታስረው ቆይተዋል። ከደረሰባቸው ሁሉ ግፍ ባስተርጉኣሚ የስማሁትን አንዷን ቅንጫቢ ታሪክ ባካፍላችሁ የአምቦን ህዝብ ሰቆቃ ትገነዘባላችሁ። አቶ ደንደና አምቦ ታስረው ብዙ ስቃይ ደርሶባቸዋል፣ ያልሰሩትን እንደሰሩ አድርገው ራሳቸውን እንዲወንጅሉ ደጋግሞ ጥያቄ ቀርቦላቸው ባለማመናቸው ዕድሜ ያደከመው ገላቸው ሃያዎቹ ቤት በማያልፍ ዕድሜ ባሉ ወጠምሻ የህወሃትና የኦህዴድ አባላት ተገርፈዋል። ከቁስላቸው ሲኣገግሙ ለዛ በተሞላ ጨዋታቸው ብዙዎችን እንደሳቸው የግፍ ሰለባ የሆኑ እስረኞች ሲኣሳስቁ ሲመክሩ ይውላሉ።

አንድ ቀን ለሊት የታሰሩበት ክፍል በድንገት ይከፈትና አቶ ደንደናና አምስት የሚሆኑ እስረኞች ስም ተጠርቶ ውጡ ይባላል። በለሊት መጠራት እንግዳ ባይሆንም ሰዓት እላፊ በቡድን መጠራት ግን አዲስ ነው። በነጠላ ለሊት እየተጠሩ ተዘቅዝቆ ሩህ እስኪሳት መገረፍ በደርግ ካድሬዎችም ሆነ በወያኔ የተለመደ ነው። በቡድን ስለጠሯቸው ሊገደሉዋቸው እንደሚወሰዱ ገምተዋል። ቀሪውም እስረኛ በኣርምሞ አንገቱን ደፍቶ ባይኑ ሸኛቸው። እያንዳንዳቸው እጃቸውን ወደሁዋላ ታስረው መኪና ውስጥ ገቡ። እነሱ ያሉባት መኪና መሳርያ በታጠቁ ሰዎች በተሞሉ ሁለት መኪኖች ታጅባ አምቦን ለቃ ወደምዕራብ ስትምዘገዘግ ወደ አዲስ አበባ ሳይሆን ወደመገደያቸው እንደሚወሰዱ ተገነዘቡ። የጉደርን አቅጣጫ ይዘው ብዙ ከሄዱ በሁዋላ ዋና መንገዱን ለቀው ወደ በረሃው ወደ ጫካው ገቡና ቆሙ። እስረኞቹን ገደል ጫፍ ላይ አሰልፈው በያንዳንዳቸው ላይ አንዳንድ መሳርያ ተድግኖ “እናንተ ቀንደኛ የኦነግ አባላትና ደጋፊ ናችሁ። ህዝቡንም በመንግስት ላይ ታነሳሳላችሁ። አሁን ልንገድላችሁ ነው። ለቤተሰቦቻችሁ የምታስተላልፉት መልዕክት ካለ ንገሩን” አሏቸው። መልስ የለም። “የሰራችሁትን ወንጀል አጋልጡና እንለቃችሁአለን ያለዚያ እዚሁ ነው የምንጨርሳችሁ”። አሁንም መልስ የለም። መሳርያቸውን እያቀባበሉ ለማስፈራራት ሞከሩ። አልሰራም። ዝምታ ብቻ ነገሠ። በሁኔታው ተስፋ ከቆረጡና ከተበሳጩ ታጣቂዎች አንዱ “ተኙ በጥይት ልንመታችሁ ነው።” ሲል ነበር የአቶ ደንደና ድምጽ ጸጥታውን የሰበረው። “አትቸገሩ ስትመቱን እንወድቃለን፣ ቆዳችን እንዳይበላሽ ሳሳችሁ እንዴ?” ሲሉ በልበሙሉነት ተሳለቁባቸው። ህሊናቸውን ለትንሽ ጥቅም የሸጡና በህዝባቸው ላይ ከስርዓቱ ጋር በማበር ያመጹ የወያኔ ተላላኪዎች የአቶ ደንደናን ሆነ የጓደኞቻቸውን ወኔና ስብዕና ሊሰብሩት አልቻሉም። ወደ እስር ቤት መለሷቸው። ያለፍርድም ብዙ ጊዜ ታሰሩ። መጨረሻውን አላወቅሁም።

የአምቦዎች ወኔ በቀላሉ የሚሰበር አይደለም። የአቶ ደራራ ከፈኔ፣ የአቶ ድንደና ጉርሙ ለጠላት የማይሰበር ልቦናና ወኔ በአምቦ ሳተናዎች አድሯል። ብሎገሩ ስዩምን በእስር እንዲማቅቅ የሚያደርገው ያ የማይሰበር ልቦና ነው። ዶክተር መረራና ባልደረቦቹ ከእስር ሲፈቱ የጀግና አቀባበል ያደረገው የአምቦ ህዝብ ለወያኔ ግልፅ መልዕክት ነበር የላከው። ለአምባገነን ስርዓት የማይንበረከክ ጀግና ህዝብ መሆኑን። ያ መልዕክት በሚገባ ደርሷል።

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የመጀመርያው የኦሮምያ ጉብኝት አምቦ የተመረጠችው ያለምክንያት አይደለም። የማይዳፈነው የአመፅ ችቦ የተለኮሰበትን ቦታና ህዝብ ማመስገን እውቅናም መስጠት ያስፈልጋልና። በወያኔ ጠላት ተደርጎ ስናይፐርና ፕሮፓጋንዳ የተደቀነበት ቄሮ የለውጥ ኃይል መሆኑን እነደመቀ ሳይቀሩ እንዲመሰክሩ ተገድደዋል። በደም የተገኘ ድል ነው። በህይወት ካሉ አቶ ደንደና ጉርሙ ቢያዩት ምን ይሰማቸው ይሆን? ዛሬ በህይወት ለመኖር መቶ ዓመት ያልፋቸዋል። በልጆቻቸውና በሁላችንም ልቦና ሲታወሱ ይኖራሉ።

አምቦ ታሪካዊነቷ ጎልቶ ይኖራል!

ኢትዮጵያ በጀግና ልጆቿ ነፃ ትሆናለች!

LEAVE A REPLY