ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ መስዕዋት ከሆኑ 150 ዓመት

ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ መስዕዋት ከሆኑ 150 ዓመት

ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ በመቅደላ ምሽጋቸው በገዛ ሽጉጣቸው እራሳቸውን መስዕዋት ከሆኑ ዛሬ 150 ዓመት ሆናቸው። የሚከተለው ጹሁፍ ስለ አሟሟታቸው ሁኔታ መጠነኛ ስዕል ይሰጣል ፡ –

የመጨረሻው የመቅደላ ግብግብ ሰኞ ሚያዚያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም. ወደማቆሙ ተቃረበ:: የእንግሊዝ ጦር ሰራዊት ቴዎድሮስን አድኖ ለመያዝ በያቅጣጫው መሯሯጥ ጀመረ::

የቴዎድሮስን ሁኔታ አስመልክቶ የኒውዮርክ ታይምስ ሪፖርተር እስታንሊ ሲናገር ሰኞ ከቀኑ አስር ሰዓት አካባቢ እንግሊዝ በመቅደላ ላይ ካሰማራቻቸው ወታደሮች መካከል ሁለት የአይሪሽ ወታደሮች የተኩስ ድምፅ ወደሰሙበት አቅጣጫ እየተክለፈለፉ እንደደረሱ፤ አንድ ያልታወቀ ኢትዮጵያው ከመሬት ላይ ተዘርሮ ለመሞት በማጣጣር ላይ እንዳለ ያገኙታል:: የግለሰቡ ጣር ስሜት ሳይሰጣቸው ቀድሞውንም ከኛ የተሰረቀ ነው በማለት በቀኝ እጁ አቅጣጫ የወደቀውን ሽጉጥ አንስተው ይወስዱበታል::

ይህ አልበቃ ብሏቸው የጣቱን የወርቅ ቀለበት እና የአንገቱን የወርቅ መስቀል ይዘርፉታል:: ከዚያም የወሰዱትን ሽጉጥ እያገላበጡ በማድነቅ ሲመለከቱ ከጎን በኩል ከብር ተቀርፆ የተለበደ ፅሁፍ ያገኙበታል:: ፅሁፉም “እንደ ኤ.አ. 1854 ለአሽከሬ ለፕላውዲን የአቢሲንያው ንጉስ ቴዎድሮስ ላደረጉለት ቅንነት የተመላበት ደግነት ያለኝን አድናቆት ለመግለፅ ከታላቁዓ ብሪታንያና የአየርላንድ ንግስት ቪክቶሪያ የተላከ ስጦታ” የሚል ነበር::

ወታደሮቹ ፅሁፉን ካነበቡ በህዋላ ከነከናቸው:: አንደኛው ወታደር “ቴዎድሮስ ይሆን እንዴ?” በማለት ነፍሱ ልትወጣ የተቃረበውን ግለሰብ ማስተዋል ጀመረ::ምናልባትም ወታደሮቹ ሊለዩዋቸው ያልቻሉበት ሌላው ምክንያት አፄ ቴዎድሮስ በጠላት መወረራቸውን እንደተረዱ ከቤተሰቦቻቸው እና ከቅርብ ተከታዮቻቸው ጋር ተሰናብተው በሽጉጥ እራሳቸውን መተው እንደወደቁ ጠላቶቻቸው እሳቸው መሆናቸውን እንዳይለዩዋቸው በማሰብ ወልደ ጋብር የሚባለው የቤት አሽከራቸው የሚደርቧትን ባለቀጭን ጥለት ነጠላቸውንና ታጥቀውት የነበረውን ባለከፋይ ቀበቷቸውን አውልቆ በመውሰድ ቁጥራቸው አስራ አምስት ያህል ከሚሆን ከቴዎድሮስ ጭፍሮች ጋር በማምለጥ ተሸሽጎ እንደነበር ለእንግሊዝ ኦፊሰሮች በሰጠው ቃለ መጠይቅ ላይ ተጠቅሷል::

ሌላው ቴዎድሮስ መሆናቸው ያልታወቀበት ምክንያት አለባበሳቸው ተራ ኢትዮጵያዊ ከሚለብሰው ልብስ የተለየ ባለመሆኑ ነበር:: በተለይም ባዶ እግራቸውን ያለጫማ መታየታቸው ብቻ ሳይሆን; ከደረታቸው ስፋትና ከትከሻቸው ትልቅነት በስተቀር ቁመታቸው መካከለኛ እንጂ ረዥምና ግዙፍ ባለመሆኑ, እኒያ በሀገራቸው ላይ ተነስተውባቸው የነበሩትን ሽፍቶች ከመደምሰስ አልፈው ተርፈው በጄኔራል ናፒር የሚመራውን ዘመናዊ የእንግሊዝ ጦር እጄን አልሰጥም በማለት በድንገት የወደቁ ታላቅ አንበሳ መሆናቸውን ከቶውንም ለማመን አልቻሉም ነበር::

ይህ በእንዲህ እንዳለ መቅደላ በእንግሊዝ ጦር ሰራዊት ቁጥጥር ስር ሆነች:: ቀደም ሲል የቴዎድሮስ እስረኞች የነበሩትም ኢትዮጵያውያን በግርግር የታሰሩበትን ቤት በመስበር የእግር ብረታቸውን መሬት እየጎተቱ በአደባባይ መታየት ጀመሩ:: ከፊሉም እንግሊዞች ወደሰፈሩበት ካምፕ በመሄድ ተቀላቀሉ::

ወዲያውኑ አንድ ግለሰብ እየሮጠ ሄዶ የጄኔራል ናፒር የቅርብ ረዳት ለነበረው ለሰር ቻርልስ እስቴቨሊ “እዚያ አንድ ግለሰብ ተዘርሯል፤ ሰዎች ቴዎድሮስ ነው ይላሉ::” በማለት ሪፖርት ያቀርባል:: እስቴቨሊ ግን በነገሩ ሙሉ በሙሉ አላመነበትም ነበር:: በዚህም ምክንያት ይህ ማንነቱ ያልታወቀውን ሬሳ በቃሬዛ ላይ በማድረግ አምጥቶ ለማሳየት በማሰብ ግለሰቡ ሬሳው ወደ ነበረበት ስፍራ ተመልሶ ሄደ:: ጭካኔ በተመላበት አኩዓሁዋን ሁለት እግሮቻቸውን በመጎተት ለቃሬዛ መሸከሚያ ተብሎ ከተሰራ የእንጨት ርብራብ ላይ እንደጣሏቸው ሶስት ጊዜ ካቃሰቱ በህዋላ ሕይወታቸው ልታልፍ ችላለች::

ይህንን ድርጊት አስመልክቶ ማርክሃም ሲያብራራ ወታደሮቹ የአፄ ቴዎድሮስን ቃሬዛ ተሸክመው ለሰር ቻርልስ ለማሳየት እንደደረሱ ታስረው የተፈቱት እስረኞች በሽቀዳደም መጀመሪያ መልካቸውን አተኩረው ካዩ በህዋላ አንድ ነገር ትዝ አላቸውና የግራ እጃቸውን ከፍ አድርገው ጣታቸውን ማየት እንደጀመሩ አንደኛው ጣታቸው ሰባራ ሆኖ አገኙት:: አፄ ቴዎድሮስ ገና በወጣትነታቸው ዘመን ጎጃም ላይ በጥይት ጣታቸው ላይ ተመተው ስለነበር የተቆረጠውን ጣት ስላዩ፤ቴዎድሮስ መሆናቸውን አረጋገጡ::

ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ሬሳው የአፄ ቴዎድሮስ ስለመሆኑ የቀረበው ማስረጃ በእንግሊዝ የጦር መኮንኖች ዘንድ አጠራጣሪ ስለመሰለ አፄ ቴዎድሮስ በሕይወት ሳሉ የሚያውቃቸው የነበረው ራሳም መጥቶ እንዲያያቸው ተደረገ:: ብዙ ሳይቆይ ራሳም ወዲያው እየሮጠ መቶ ሲያያቸው አፄ ቴዎድሮስ ሆነው አገኛቸው:: ምንም እንክዋን በሱና በአፄ ቴዎድሮስ መካከል አልፎ አልፎ አለመግባባት ቢፈጠርም ቆራጥ መሪ መሆናቸውን ጠንቅቆ ያውቅ ስለነበር ሁኔታውን እንደተመለከተ መንፈሱ ተረበሸ:: በተለይም ከመሞታቸው በፊት የተናገሩት ቃል ትዝ አለው::

ይሄውም “አንድ ቀን እኔ ስሞት ታየኝ ይሆናል; ከዚያም በሬሳዬ ላይ ቆመህ ይህን ደካማ ሰው በመቅበር ፋንታ ከሜዳው ላይ እንደወደቀ በስብሶ መቅረት አለበት በማለት ትረግመኝ ይሆናል”ብለው የተናገሩት ትዝ እያለው በሃዘን ተውጦ ይታይ ነበር::

የአፄ ቴዎድሮስ መሞት በይፋ እንደታወቀ የእንግሊዝ ወታደሮች ደስታ በተመላበት ሁኔታ ባንዲራቸውን በማውለብለብ በመቅደላ ተራራ ላይ ጩሃታቸውን አስተጋቡት:: ብሔራዊ መዝሙራቸውንም አሰሙ::በቴዎድሮስ እጅ ታስረው የነበሩትም እስረኞች ሟቹ ሬሳ አካባቢ

የፈንጠዝያ ግብዣ ለማድረግ ከያሉበት ተጠራሩ:: ሕዝቡም ሬሳውን በደምብ ለማየት እንዲችል ወደ ሜዳ ተጎትቶ ተቀመጠ:: ዙሪያውንም በመክበብ እርቃነ ስጋቸው እስኪታይ ድረስ የለበሱትን ልብስ በብዙ ቦታ ተለተሉት::

በወቅቱ የአይን ምስክር በመሆን ያረጋገጠው አሜሪካዊ ሪፖርተር ሕይወታቸው ስላለፈችው የመቅደላ ጀግና ሲያብራራ “የተለየ ክብር ሳይደረግላቸው ጠባቂ ዘብ በአጠገባቸው ሳይቆም በቃሬዛ ላይ ለብዙ ሰዓት ያህል ከመሬት ተዘርረው፤ፀጉራቸው ተሸልቶ ልብሳቸው ተገፎ እና ተቀዳዶ ከፊል እርቃነ ሥጋቸውን በማየቴ የቀድሞው ቴዎድሮስ መሆናቸው አጠራጠረኝ” ይልና “ራቅ ብዬ ስመለከት ብዙ ኦፊሰሮች በደም የተበከለውን የቴዎድሮስን ሸሚዝ ለኔ ይገባኛል በማለት ሲሟገቱ እና ሲጣሉ ተመልክቼ ነበር::”ብሎ ንግግሩን ይደመድማል::

ስለሆነም በዚያን ጊዜ ቴዎድሮስ ሲነግሱ ለብሰውት የነበረው የክብር ልብስና በአንፃሩ ደግሞ ከሞቱ በህዋላ የተወሰደባቸው በደም የተበከለ ሸሚዝ በእንግሊዝ አገር ራቅ ባለ ሰሜናዊ ክፍል ባንክ ፊልድ ሙዚየም ተብሎ በሚጠራው መዘክር ውስጥ ሲገኝ የተሸለተው ፀጉራቸው ግን ለንደን ከተማ ናሽናል ዋር ሙዚየም ውስጥ እንግሊዞች አጉል ጀብደኝነታቸውን ለማስታወስ ብለው አስቀምጠውታል::

ይህንን አስነዋሪ ድርጊት ያስተዋለ አንድ ታዛቢ የቴዎድሮስ ሬሳ ከፊል እርቃኑን ስለነበረ የሰው መሳቂያ ሆኗል በማለት ለናፒር ተናገረ:: ናፒር ግን የተሰራው ሥራ አንድ ወታደር ከሚያደርገው የዲስፕልን ስነስርዓት ውጪ መሆኑን እየተገነዘበ አንዳችም የቅጣት እርምጃ ሳይወስድ ቃሬዛው እንዲለብስና በማግስቱ ለቀብር እንዲዘጋጅ የሚል ትዕዛዝ ሰጠ:: ሆኖም ይህ ከመፈፀሙ በፊት በስዕል መልክ ፎቶግራፍ እንዲነሱ ተደረገ:: ከመጣበት ተልዕኮ ሌላ በስዕል በመሳል ልዩ ሙያ የነበረው የብሪትሽ ሙዚየም ተወካይ ሪቻርድ ሆምስ በደረቅ አርሳስና ብሩሽ አማካኝነት ስሎ አቀረበ::

የሳለውም ስዕል ትክክለኛውን የቴዎድሮስ መልክ የያዘ እንደነበረ የቴዎድሮስን አሟሟት ለመመርመር ከተገኘው ሐኪምና በሚስተር ራሳም ተረጋገጠ:: ከዚያም በህዋላ ቀደም ሲል ጠቅላይ የጦር አዛዤ እንዳዘዘው ሁሉ በሚስተር ራሳም አማካይነት ቃሬዛው ከስፍራው ተነስቶ የእንግሊዝ እስረኞች ይኖሩበት ከነበረው ግቢ ፒትሮ ተብላ ከምትጠራው ጎጆ ውስጥ ለቀብር እንዲዘጋጅ ተደረገ::

የቀብሩ ስነ ስርዓት ከመፈፀሙ በፊት ስለአሟሟታቸው በሃኪሞች የተደገፈ ማስረጃ ማግኘት ያስፈልግ ስለነበረ ዶ/ር ብላንክና የአፄ ቴዎድሮስ የንስሐ አባት በተገኙበት ዶ/ር ለምስዳይን አስከሬኑን መርምረው ያገኙት ውጤት “በጥይት የተመታ ቁስል ከበስተህዋላ በኩል ጭንቅላታቸው ላይ ሲታይ፤ እንዲሁ ከአፋቸው ውስጥ ጠቆር ብሎ ጉድጉድ ያለ ቁስል ይታይበት እንደነበረ፤ የሽጉጣቸውን አፈሙዝ ከአፋቸው አጉርሰው የተኮሱት ጥይት በአፋቸው ጣራ በኩል አድርጋ የሁዋላ ጭንቅላታቸውን አልፋ የወጣች በመሆኗ ንጉሡ ራሳቸውን በራሳቸው እንደገደሉ የሚመሰክር ነው በማለት አረጋገጡ::

”የምርመራው ውጤት ካበቃ በህዋላ ዶ/ር ሄንሪ ብላንክ እንዲህ ብለው ተናገሩ:: “ስሜቴን በጣም የሟቹ የቴዎድሮስ ሬሳ ነበር:: የቴዎድሮስ ሬሳ ፈገግ ብሎ ይታያል፤የዚህ አይነቱን ደስታ የተመላበት ከአፄ ቴዎድሮስ በቅርብ ጊዜ በሕይወት እያሉ አይታይባቸውም ነበር:: ይህም ሁኔታ ፀጥታ የተመላበት ብዙ አስደናቂ ስራዎችን ያከናወኑ; ታላቅነትና ጨካኝነታቸውም በታሪክ ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለውን የሰው ቅርፅ የያዘ በሕይወታቸው ማለፊያ ጊዜ የወጣትነታቸውን ወራት, በጀግንነት ያደርጉዋቸውን ውጊያዎች አሁንም ራሳቸውን በራሳቸው መግደላቸውን አስበው መደሰታቸውን ያሳያል::”

ምንም እንኯ ጄኔራል ናፒር የአፄ ቴዎድሮስን ሬሳ ለቀብር እንዲዘጋጅ ብሎ ትዕዛዝ የሰጠ ቢሆንም የት ቦታና በእንዴት ያለ ሁኔታ ቀብሩ እንደሚከናወን ገና አልተወሰነም ነበር:: ይህም ጉዳይ ለሟች ባለቤት ለእቴጌ ጥሩቀርቅ በጥያቄ መልክ ቀርቦላቸው ሲመልሱ “በግል ቤተክርስቲያናቸው ውስጥ ፍትሃተ ፀሎት እንዲደረግላቸው ይፈቀድ ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ”በማለት የተናገሩት በጄኔራል ናፒር ተቀባይነት በማግኘት የአፄ ቴዎድሮስ ሬሳ በጎጆው ውስጥ እንዳለ በነጭ ጨርቅ እንዲጠቀለል ተደረገ:: ከዚያም በወርቀ ዘቦ ያሸበረቀ የሀገር ልብስ ከለበሰ በህዋላ በአልጋ ላይ ተደርጎ ወደ ቀብር አመራ::

የአፄ ቴዎድሮስ የውስጥ ጠላቶች አደጋ ሊያደርጉባቸው ይችላሉ በሚል ስጋት ባለቤታቸው እቴጌ ጥሩወርቅና ልጃቸው ደጃዝማች አለማየሁ በቀብሩ ስነ ስርዓት ላይ አልተገኙም ነበር:: ይሁን እንጂ የቅርብ ዘመዶቻቸውና ጥቂት መኮንኖች በተገኙበት በሕይወታቸው ሳሉ መቅደላ ላይ አሰርተውት በነበረው በመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ስርዓተ ፀሎት ተደርጎላቸው ከአቡነ ሰላማ መቃብር አጠገብ በተወለዱ በሃምሳ አመታቸው ሚያዚያ 6/1860 ዓ.ም.(እ.ኤ.አ.ሚያዚያ 13/1968) የቀብር ሥነ ስርዓታቸው ተፈፀመ::

ዋቢ መጽሐፍት~የኢትዮጵያ ታሪክ ከመጀመሪያው እስከ አሁኑ ዘመን

(አንድርዜይ ባርትኒስኪና ዮዓና ማንቴል ኒያችኮ)

1 COMMENT

  1. Has Ethiopia ever had a king who was named. ” Kedamawi Theodros” before Atse Theodros Meyesaw Kasa?
    Why you call him Dagmawi Atse Theodros?

LEAVE A REPLY