/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- በሞያሌ ከተማ በደረሰ የቦንብ ፍንዳታ በሰው ይህወት ላይ ጉዳት አደረሰ። በሞያሌ መናሐሪያ አከባቢ ዛሬ እኩለ ቀን ላይ በደረሰ የቦንብ ፍንዳታ ሦስት ሰዎች ሲሞቱ ከ60 በላይ ደግሞ ከባድ ጉዳት ማድረሱን የአካባቢው ምንጮች ገለጹ።
ከአይን እማኞች እንደነገሩን በ“ኦሮሞና ሶማሌ የጎሳ አባላት መካከል ግጭት ከተከሰ በኋላ ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ የእጅ ቦንብ እንደተወረወረና ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን” አረጋግጠዋል። በቦንብ ፍንዳታውና በጥይት የቆሰሉ ሰዎች በሞያሌ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እያገኙ እንደሆነ የገለጸ ሲሆን የአብዛኞቹ የጉዳት መጠን ከፍተኛ በመሆኑ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር ይችላል የሚል ስጋት እንዳደረባቸው የህክምና ባለሙያዎች “ሲፋ” ለተባለ ለኬንያ ራዲዮ ገልጸዋል።
የሞያሌ ከተማ አስተዳድር የህዝብ ግንኙነት መስሪያ ቤት ለጥቃቱ የኢትዮ-ሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስን ተጠያቂ ማድረጉን አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል።
ባለፈው የካቲት ወር በሞያሌ ከተማ የወያኔ መከላከያ ሰራዊት አባላት በጸራራ ጸሀይ በህዝብ ላይ በከፈቱት ተኩስ ከ15 ሰዎች በላይ መሞታቸውንና ከ20 በላይ መቁሰላቸውን ተከትሎ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የአካባቢው ነዋሪዎች ህይወታቸውን ለማትረፍ ወደ አጎራባች ኬንያ ተሰደው እንደሚገኙ ይታወቃል።