ሰንደቅ ጋዜጣ ቆይታ ከቀድሞ የአየር ኃይል አዛዥ ሜጄር ጄኔራል አበበ ተ/ኃይማኖት ጋር

ሰንደቅ ጋዜጣ ቆይታ ከቀድሞ የአየር ኃይል አዛዥ ሜጄር ጄኔራል አበበ ተ/ኃይማኖት ጋር

የቀድሞ አየር ኃይል አዛዥ ሜጄር ጄኔራል አበበ ተ/ኃይማኖት በኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ያደረጉት ቆይታ።

________

“የኢህአዴግ የፖለቲካ ማዕከል ህወሓት መሆኑ ከቀረ ቆይቷል” ሜጄር ጄኔራል አበበ ተክለኃይማኖት

የኢትዮጵያ አየር ኃይል የቀድሞ አዛዥ ሜጄር ጄኔራል አበበ ተክለኃይማኖት በ1993 ዓ.ም ከመንግስት የስራ ኃላፊነት ከተለዩ በኋላ በመምህርነት አገራቸውን እያገለገሉ ይገኛሉ። እኒህ የቀድሞ ታጋይ በተለያዩ ጊዜያት ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቀት ያለው ማብራሪያ በመስጠት የሚታወቁ ሲሆን ሃሳባቸውን ወደ መገናኛ ብዙሃን በተለይም በህትመት ሚዲያው በኩል ለህዝብ በማድረስ ተጠቃሽ ናቸው።

የሁለተኛ ዲግሪያቸውን የመመረቂያ ጥናታዊ ጽሁፍ የባህር በር ላይ ትኩረት አድርገው የሰሩ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያ የባህር በር አልባ መሆኗ ከሚያስቆጫቸው ኢትጵያዊያን መካከል አንዱ ናቸው። በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ፣ በኤርትራ እና ኢትዮጵያ መካከል ሊኖር ስለሚችለው ግንኙነት፣ ስለ ዶክተር አብይ አሕመድ ካቢኔ፣ ስለ ህወሓት እና የተለያዩ ጉዳዮች ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ሰፋ ያለ ቃለ ምልልስ አድርገዋል። የቃለ ምልልሱን ሙሉ ክፍል እነሆ!!

ሰንደቅ፡- ውይይታችንን በወቅታዊ ጉዳይ እንጀምረው። በኢትዮጵያ የተደረገውን የአመራር ለውጥ ከሂደቱ ጀምሮ እስከ ርክክቡ እንዴት አዩት?

ጄኔራል አበበ፡- ኢትዮጵያ ለውጥ ያስፈልጋት ነበር። አጠቃላይ የነበረው የሰላም ማጣት ሁኔታ ለውጥ፣ ዴሞክራሲን፣ ፍትህን እና የህግ የበላይነት እንዲኖር የሚጠይቅ ነው። ተፈጥሮ የነበረው ሁኔታ ጸረ ዴሞክራሲ የተስፋፋበት፣ የህግ የበላይነት የማይከበርበት፣ ፍትህ የታጣበት ስለነበር ለውጥ ያስፈልግ ነበር። ለውጡ ከየት ይምጣ እና በማን ይነሳ የሚለው ነገር የአገሪቱ ሁኔታ እና ታሪካዊ ሁኔታ ይወስነዋል።

በመሰረታዊነት የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ በጸረ ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ አንመራም እያሉ ቢሆንም በዋናነት የተነሳው ግን ኦሮሚያ አካባቢ ነው። በመሰረታዊነት የኦሮሞ ህዝብ በተለይም የኦሮሞ ወጣት አጠቃላይ ያደረገው እንቅስቃሴ አልገዛም ባይነት ያሳየበት ሁኔታ ነበር፤ እንደሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ። በእርግጥ እዚህ ላይ አንዳንድ ወንጀለኞች ከለውጡ ጋር ተደባልቀው ብሔር ተኮር ጥቃት የታየበት፣ ንብረት የወደመበትና በአጠቃላይ ብዙ ጥፋት የተፈጸመበት ቢሆንም በዋናነት ግን የኦሮሞ ወጣት እንቅስቃሴ ለፍትህ እና ለዴሞክራሲ የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው የሚል እምነት አለኝ። ስለዚህ ለውጥ ያስፈልግ ስለነበርና የለውጡ ማዕከል ደግሞ ኦሮሚያ በመሆኑ የለውጥ መሪ ከየት ይመጣል የሚለውን ብዙ ጥያቄ እናነሳ ለነበረው ጥያቄ መሪዎች ከኦሮሚያ እየመጡ መሆኑን ማየት ጀመርን።የለማ ቡድን የምንለው መምጣት ጀመረ።

ከዚያም ምናልባት ኢትዮጵያን የሚያድናት እና መምራት የሚችል ከዚህ ይመጣል ብዬ ማሰብ ስለጀመርኩ መከታተል ጀመርኩ። ስለዚህ በአንድ በኩል ከነበረው የኢህአዴግ ጸረ ዴሞክራሲ ስርዓት ብዙ ንክኪ ያልነበራቸው፣ በአንጻራዊነት ጎልማሳ የምንላቸው እና የተማሩም ናቸው። ስለዚህ አሁን የሚመጣው ለውጥ ዋናዎቹ መሪዎች ከኦህዴድ ይመጣል ብዬ ሳነሳ ነበር። አሁን ሲታይም የለውጡ መሪዎች እነሱ ናቸው የሆኑት።

ህወሓት እና ብአዴን በነበሩበት ላይ ነው የቆሙት። እነሱ ግን (ኦህዴድ) ተቀይረው ፌዴራሊዝምን እና ኢትጵያዊነትን አንድ ላይ አድርገው የኢትዮጵያ አንድነትን አጠናክረው የሚቀጥሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ስለዚህ በተለይ ደግሞ የምርጫ ሂደቱ ሲጀመር ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በተለያየ መንገድ የምርጫ ቅስቀሳውን ስራ (Campaign) በደንብ ሰርተውታል። ይህ ደግሞ በ21ኛው ክፍለ ዘመን እንደዛ መሆን አለበት።

እኔም ጓደኞቼም በእነሱ ላይ (የለማ ቡድን) ተስፋ ስናደርግ ነበር። እሳቸው በመመረጣቸውም በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ ተገቢም ነው ብዬ አምናለሁ። በእሳቸው መመረጥ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የሰላም አየር መተንፈስ ጀምረናል። በኢትዮጵያ ሁኔታ የሰላም አየር ከለውጥ ውጭ ሊሆን አይችልም።

ሁለተኛ በፓርቲያቸው ግምገማ የነበራቸው ጥንካሬ ለወጣቱም ትልቅ አርአያ ነው የሚሆኑት። ከሁሉም በላይ የኢህአዴግ ዋና በሽታ የሆነውን አግላይነት ሁሉን አቀፍ በሆነ አስተሳሰብ እየቀየሩት ነው። በተለይ ከተመረጡ በኋላ ያደረጓቸው ንግግሮች (ጎንደር እና ባህር ዳር ላይ ተገኝተው ንግግር ከማድረጋቸው በፊት የተደረገ ቃለ ምልልስ ነው) ድሃውን፣ ሴቶችን፣ ወጣቱን ማዕከል የሚደርግ እና የለውጥ አቅጣጫ የሚያሳይ ንግግር ነበር ሲያደርጉ የነበሩት። እንዳጋጣሚ ይህ መጽሐፍ የእሳቸው ነው (ለሁለተኛ ጊዜ እያነበቡት የነበረውን እርካብና መንበር መጽሐፍ እያመለከቱ) አሁን በቴሌቪዥን የሚናገሩት እዚህ መጽሃፋ ላይ ያለውን ነው። ስለዚህ የሚናገሩት ድንገት የመጣላቸውን ሳይሆን ያሰቡበትን እና የራሳቸውን አስተያየት ይዘው ይህችን አገር ለመለወጥ የመጡ ይመስለኛል።

ሰንደቅ፡- ዶክተር አብይም ሆኑ አጠቃላይ የለማ ቡድን የሚባለው ቡድን እናንተ አዲስ አበባን ስትይዙ ገና ታዳጊ የነበሩ ልጆች ናቸው። እድገታቸው በኢህአዴግ ቤት ውስጥ በመሆኑና የኢህአዴግን ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት እና የውስጥ ግምገማ አልፈው ሂስና ግለሂስ እያወረዱ የመጡ ስለሆነ ከእነዚህ ሰዎች ለውጥ መጠበቅ የዋህነት ነው ሲሉ የሚናገሩ አሉ። እርሰዎ በዚህ ላይ ያልዎት አስተያየት ምንድን ነው?

ጄኔራል አበበ፡- ጥያቄው ተገቢ ነው። ኢህአዴግን የምንቃወምበት ምክንያት ህገ መንግስቱን ተግባራዊ ስላላዳረገ እና ጸረ ዴሞክራሲያዊ አየር በመፍጠሩ ነው። የለማ ቡድን ከመጀመሪያው ጀምሮ ህገ መንግስቱን የማክበር፣ ፌዴራሊዝሙን የማክበር ነገር እና ኢትየጵያዊነትን የማክበር ነገር ነበራቸው። ስለዚህ ከኢህአዴግ ውስጥ አዲስ ኃይል እየተፈጠረ ነው፤ ሊፈጠርም ይችላል።

በሌሎች አገሮችም የሚታዩት እንኳን እንደ ኢህአዴግ ከፊል ዴሞክራሲያዊ የሆነ ድርጅት ጭፍን የሆነ ጸረ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ገዥ መደቦች ውስጥም ቢሆን ከእነሱ የሚወጣ ለውጥ ፈላጊ ሊኖር ይችላል። የኢህአዴግ ፕሮግራም ከሞላ ጎደል ዴሞክራሲያዊ ነው። እነሱም ህገ መንግስቱን አክብረው ፌዴራሊዝሙ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሆኖ የኢትዮጵያ አንድነት መጠበቅ አለበት ብለው ነው የተነሱት። በዚህ ሌሎቹም የኢህአዴግ ድርጅቶች ለውጥ ያስፈልጋል የሚለውን የተሟላ ነገር ሳይዙ ለውጥ ያስፈልጋል ብለው ነው የመጡት።

የምርጫ ሂደቱን ስታየው ራሱ የኢህአዴግን ኋላቀር የሆነ ነገር በጣጥሰው ነው የመጡት። ለምሳሌ ዶክተር አብይ እንዲመረጡ በተለያየ መንገድ ብዙ እንቅስቃሴ ተደርጓል። ራሳቸውም ሊሆኑ ይችላሉ ወይም ሌሎች ሊያደርጉት ይችላሉ ዶክተር አብይ እንዲመረጡ በተለይ ሶሻል ሚዲያውን ተጠቅመውበታል።

የኢህአዴግ አመራረጥ ግን ፊውዳል አትለው ምን አትለው በጣም ኋላ ቀር ሲሆን እሳቸው ግን ይህን እየበጣጠሱ ነው እዚህ የደረሱት። ከተመረጡም በኋላ ቢሆን የተለየ ራዕይ እና አስተሳሰብ ያላቸው መሆናቸውን ነው ያሳዩት። በእርግጥ በተግባር ብዙ የሚታይ ነገር ይኖረዋል። እስካሁን ያለው አቅጣጫ ግን የሚያስደስትና እኛም ሁላችንም ደግፈን ለውጡን ማቀላጠፍ ያለብን ይመስለኛል።

ሰንደቅ፡- ቀደም ሲል ህወሓት በነበረበት ቆሟል ብለዋል። ፓርቲውም ከምስረታው ጀምሮ እስካሁን ድረስ በሊቀመንበርነት የሚመሩት ሰዎች ታጋዮች ናቸው። ሌሎቹ የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች ከዚህ በተለየ መንገድ ነው የሚጓዙት። ይህን በማንሳትም ፖለቲከኞች ህወሓት መውለድ አይችልም (ተተኪ አያፈራም) ሲሉ ይናገራሉ። ህወሓት ለውጥ ያላመጣበት ችግሩ ምንድን ነው ብለው ያስባሉ?

ጄኔራል አበበ፡- እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ የምለው ህወሓት በ1993 ዓ.ም ቆስሎ ነበር። አሁን ያ ቁስል አመርቅዞ የማይድን ቁስል (ጋንግሪን) ሆኗል። ህወሓት ድሮ መማር የሚወድና በመማር የሚያምን ድርጅት ነበር፤ አሁን ግን እንደዛ አይደለም። ስልጣን የተጠሙ ሰዎች የተሰባሰቡበት ስለሆነ የተማረውን ወጣት ክፍል እንዳይቀላቀላቸው የመከልከልና የማራቅ ስራ ይሰራሉ። ምክንያቱም የተማረው ወጣት ወደእነሱ ከገባ ይገዳደርና የእነሱንም ቦታ ይነጥቃል። የህወሓትን ስራ አስፈጻሚ ስትመለከት ከሁለት አባላት በስተቀር ሁሉም ታጋዮች መሆናቸው ይህን ይነግርሃል።

አሁን በአንድ በኩል የእነ ዶክተር ደብረጽዮን የእነ ጌታቸው ረዳ ቡድንን ከእነ ለማ ቡድን ጋር ታነጻጽራለህ። እነ ለማ አሸንፈው ሲወጡ እነዚህ (ህወሓቶችን) መስራች ነን በሚሉ ሰዎች ታፍነዋል አልወጡም። ስለዚህ ህወሓት ጋንግሪን ያለው…

LEAVE A REPLY