/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የመጀመሪያውን የውጭ ሀገር የስራ ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ ከሰዓት ጅቡቲ ገብተዋል ተባለ።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተመራው የልዑካን ቡድንም የውጭ ጉዳይ፣ የትራንስፖርት፣ የኮሙኒኬሽን ጽፈት ቤት ሚኒስትሮች እንዲሁም የሶማሌና አፋር ክልል ፕሬዝዳንቶች፣ የድሬደዋ ከተማ ከንቲባና ሌሎች የስርዓቱ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ያካተተ መሆኑ ታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እንደሚያደርጉ የተገለጸ ሲሆን በቆይታቸውም ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌህ ጋር በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል።
ከዚህ ቀደም የነበሩ መሪዎች(ገዥዎች) የመጀመሪያ የስራ ጉብኝታቸውን በምዕራባዊያን ሀገራት መጀመር የተለመደ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባልተለመደ ሁኔታ በጎረቤት ሀገር የመጀመሪያ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው መልካም ጅምር መሆኑን አስተያየቶች እየተሰጡ ይገኛል።