ኣፋን ኦሮሞ በግዕዝ /ከኣንጋፋ ኦሮሞ ጀነራሎች/

ኣፋን ኦሮሞ በግዕዝ /ከኣንጋፋ ኦሮሞ ጀነራሎች/

ጀነራል ካሳዬ ጨመዳና ጀኔራል ዋሲሁን ንጋቱ ኢትዮጵያን የሚወዱ ለኢትዮጵያ መስዋትነትን የከፈሉና አሁንም በጦር ሜዳ ባይሆን ለኢትዮጵያ ብልጽግናል ለሰላም፣ ለፍቅርና ለአንድነት የሚተጉ ጀግና የኢትዮጵያ ልጆች ናቸው።

ጀነራሎቹ በኣማራ ክልል ኦሮምኛ ትምህርት እንዲሰጥ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ጥሪ ያቀረቡ ምሁራንና አክቲቪስቶችን በመደገፍ ለኣቶ ገዱ ኣንዳርጋቸው ኦሮምኛ በኣማራ ክልል በግዕዝ ፊደል እንዲጻፍ ጥሪ ኣቅርበዋል። ስለ ግዕዝ ሲናገሩ ጀነራሎቹ ግዕዝ የኣገር ቅርስ መሆኑን ገልጸው የኣገር ቅርስም ተበብቆ የቆየው በቀላሉ እንዳልሆነና ብዙ ዋጋ እንዳስከፈለም ያሳስባሉ።

የጀነራሎቹ ደብዳቤ እነሆ

ግልጽ ደብዳቤ

ለተከበሩ ኣቶ ገዱ ኣንዳርጋችው
ለኣማራ ክልላዊ መንግሥስት ሊቀመንበር

በቅድሚያ የከበረ ሰላምታችን ይድረስዎት። እርስዎና የክልል መንግሥትዎ በእዚህ ወሳኝና ፈታኝ ወቅት የኣገርንና የሕዝብን ችግር ለመፍታት እያደረጋችሁት ስላለው ትልቅ መረባረብ ያለንን ትልቅ ምስጋና ለማቅረብ እንወዳለን።
በኣማራ ክልል የኦሮምኛ ቋንቋ እንደ ትምህርት እንዲሰጥና መጠቀሚያ ፊደሉም የግዕዝ ፊደል እንዲሆን የሚጠይቅ ከጥናታዊ ዝርዝር መረጃ ጋር የተጻፈ ደብዳቤ ለክቡርነትዎ ምሁራንና ታዋቂ ሰዎች መጻፋቸውን ስንሰማ እኛም ለኣገር እንደሚያስቡ ዜጋዎች ድጋፋችንን ልንሰጥ ኣሰብን።

ክቡር ሊቀመንበር፣

ከኣፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ወታደሮች ኣገራችንና ሕዝባችንን ባለን ኣቅም ለማገልገል ሞክረናል። የኣገርን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ ደማችንን ኣፍስሰናል። ኣጥንታችንን ከስክሰናል። ከእኛ በበለጠ ቍጥራቸው ቀላል የማይባሉ ወገኖቻችን የመጨረሻውን የሕይወት መስዋትነት ከፍለዋል። የእኛ የምንለው፣ ባህላችን፣ ቋንቋችን፣ ቅርሳችን፣ ነጻነታችን ተጠብቆ የኖረው በነጻ አይደለም። ትልቅ ዋጋ ተከፍሎበት ነው።

ይህ እንዳለ ሆኖ የኣገር ቅርስ የሆነው እና ሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ የሚናገረው የኦሮምኛ ቋንቋ በኣማራ ክልል እንደ ኣንድ ትምህርት ቢሰጥ ሕዝብን ከሕዝብ ከማስተሳሰሩም ባሻገር የኣማራ ክልል ዜጎቻችን የኦሮምኛ ቋንቋ ማወቃቸው በሰፊው የኦሮሞ ክልል በቀላሉ የሥራ ዕድል ይፈጥርላቸዋል።

ቋንቋ መግባቢያ ነው። ቋንቋ ማወቃችን ይጠቅመናል እንጅ አይጎዳንም። ቋንቋ የልዩነት ምክንያት ሊሆን አይገባም። ኣቅምና ጊዜ ከፈቀደ ዜጎች ተጨማሪ ቋንቋዎች እንዲያውቁ ማበረታት ኣስፈላጊ ነው። የበለጠ መቀራረብና የበለጠ መግባባትን የሚያመጣ ነው።

ከውጭ ወራሪዎች በደማችን ኣገራችን ተከላክለናል። ሆኖም ግን ልናሸንፋቸው ያልቻልናቸው ጠላቶች ኣሉን። የውስጥ ጠላቶች የሆኑ ዘረኝነት፣ ድህነት፣ መከፋፈልና ጥላቻ ኣሉ። እነዚህን ጠላቶቻችን ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ አማራ …..ሳንባባል፣ እንደ ኢትዮጵያውያን ኣንድ ሆነን ለማሸነፍ ተረባርበን ካልሠራን እንደ ኣገር የትም ኣንደርስም። ኣገር የምትገነባው በፍቅርና በኣንድነት ነው። ኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ ስንቀራረብ፣ ስንከባበርና ስንያያዝ ነው የሚያምርብን። አዎን ኦሮምኛ የእኛ ነው። ኣማርኛ የእኛ ነው። ትግርኛ የእኛ ነው። ከኢትዮጵያ የሆነ ሁሉ የእኛ ነው። የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው።

ውድ የተከበሩ ኣቶ ገዱ

ከዳር ሆኖ መተቸት ቀላል ነው። ኣገርን ማስተዳደር ግን ከባድ ነው። መናገር ቀላል ነው። ተግባር ግን ከባድ ነው። ማፍረስ ቀላል ነው። መገንባት ግን ከባድ ነው። መለያየትና መከፋፈል ቀላል ነው። ማቀራራብና ኣንድ ማድረግ ከባድ ነው። መጥላት ቀላል ነው። መውደድ ግን ከባድ ነው። ያለብዎት ሃላፊነት ከባድ መሆኑን ጠንቅቀን እናውቃለን። ብርታቱን፣ ጥበቡንና ጥንካሬውን ፈጣሪ ኣብዛቶ እንዲችርዎት እየተመኘን፣ ላቀረብናቸው ጥያቄዎች ትልቅ ትኩረት እንደሚሰጡት ተስፋ እያደረግን ለሚሰጡን ቀና ምላሽ ከወዲሁ ልናመሰግን እንወዳለን።

ከታላቅ ኣክብሮት ጋር

ብ/ር ጄነራል ካሳዬ ጨመዳ
ብ/ር ጄነራል ዋሲሁን ንጋቱ

LEAVE A REPLY