“ካምብሪጅ አናላቲካ የተሰኘው የፖለቲካ ጉዳዮች አማካሪ ቡድን ከፌሰቡክ መረጃ በርብሯል ተብሎ ወቀሳ ሲበዛበት ሰንብቷል። ይህንን ተከትሎም ነው ድርጅቱ ሊዘጋ እንደሆነ ተገለጧል።ፌስቡክ የተሰኘው የማሕበራዊ ትስስር ዘዴ የ87 ሚሊዮን ደንበኞቼ መረጃ ሕቡዕ በሆነ መልኩ ተመዝብሮኛል ሲል ከተደመጠ ወዲህ ነው አማካሪ ድርጅቱ ላይ ትችት ይበረታ የያዘው።
ለመረጃው መሹለክ የኔም ‘ዝርክርክነት’ አለበት ሲል ያመነው ፌስቡክ ምርመራ ማካሄዴን እቀጠላለሁ ይላል። “መሰል ምዝበራ መልሶ እንዳያጋጥመን የማንፈነቅለው ድንጋይ የለም” የፌስቡክ አፈ ቀላጤ ቃል ነው።
ካምበሪጅ አናሊቲካ በአውሮጳውያኑ 2016 ለተከናወነው የአሜሪካ ፕረዝደንታዊ ምርጫ ይሆን ዘንድ የበርካታ ሚሊዮን የፌስቡክ ተጠቃሚያንን መረጃ በርብሯል፤ ብሪታኒያ ከአውሮፓ ሕብረት በምትገነጠልበት ወቅት የበኩሉን ሚና ተጫውቷል፤ አልፎም በኬንያና ናይጄሪያ በተካሄዱ ምርጫዎችን ላይ እጁን አስገብቷል በሚል ነው ትችትና ክስ የወረደበት።
ድርጅቱን መዝጋት ለምን አስፈለገ ብሎ ቢቢሲ ቃል አቀባዩን በጠየቀ ጊዜ “ምላሻችንን በድረ-ገፃችን ታገኙት ዘንድ ይሁን” ብለዋል። በተጠቆመው ድር ላይ የተለጠፈው መግለጫ “ድርጅቱ ተገቢነት በሌላቸው ውንጀላዎች ሲዋከብ የቆየ ቢሆንም ይህን ለማቅናት ያደረገው ጥረት ሊሳካ ባለመቻሉ፤ ደንበኞቻችንም በመገናኛ ብዙሃን ስማችን ሲጎድፍ በማድመጣቸው ምክንያት እምነት ስላጡብን ልንዘጋ ተገደናል” ሲል ይነበባል። ቢሆንም በርካታ ተንታኞች ይህ ጉዳይ የተዋጠላቸው አይመስልም። ድርጅቱ ስሙን ቀይሮ አሊያም ከሌላ ድርጅት ጋር በማበር ብቅ ማለቱ አይቀርም ይላሉ።
በአንድ የቴለቪዥን ጣቢያ ላይ ስለሚሰሩት የመረጃ ምዝበራ ሲናገሩ የተያዙት የድርጅቱ የበላይ ሰው ከሥራቸው መታገዳቸው የሚታወስ ነው። ከድርጅቱ ባለሃብቶች መካከል አንዱ አሜሪካዊው ቱጃር ሮበርት መርሰር እንደሆነ ሲታወቅ 15 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ እንዳፈሰሱም ተዘግቧል። ድርጅቱ የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን መረጃ የመበርበሩ ወሬ ከተሰማ ወዲህ ፌስቡክ ‘በኔ ይሁንባችሁ፤ ከእንግዲህ ለመረጃችሁ ጥንቃቄ ማድረጉን ተክንነበታል’ ሲል አትቷል።
የፌስቡክ አለቃ ማርክ ዙከርበርግም በአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ፊት ቀርበው የእምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸው ከቶም የሚዘነጋ አይደለም።”
ምንጭ ቢቢሲ አማርኛ