ሀይ ባይ ያጡት የሐሰት ነቢያት /በእውቀቱ ስዩም/

ሀይ ባይ ያጡት የሐሰት ነቢያት /በእውቀቱ ስዩም/

በሃይማኖት ስም፤ ህዝብን ማታለልና መበዝበዝ የነበረና ያለ ነገር ነው፤ በማህበረሰብ ውስጥ ማምረት የተሳናቸው ነቀዞች “የግዜር ወኪል ነን ” ብለው አምራቹን ባላገር ሲዘርፉት ኖረዋል፤ ሰሞኑን ያየሁት ቪድዮ የዚህ የቅጥፈት ልማድ ቅጥያ መሰለኝ፤ አንዱ ጮሌ በመለኮታዊ ተአምር ሽፋን፤ አዳራሽ ሙሉ ህዝብ በነፍሱ ይጫወትበታል፤ ታምረኛው ሰውየ ዐይኑን በጨው አጥቦ፤ የምእመናንን እጅ አስረዝማለሁ እያለ ሲያጭበረብር ይታያል፤

አንድ የእጅ መሰበር አደጋ የገጠመው ምስኪን ፤የፈዋሽ ደጅ ቢጠና አይገርምም፤ ጤነኛ እጅ ያለው ምእመን እጁን ማስረዘም የሚፈልበት ምክንያት ምንድር ነው? ጎበዝ ጉዳዩን ፤የማያምን ሰው ነቆራ አድርጋችሁ አትውሰዱብኝ፤ እንድያው ከእምነት አንፃር እንኩዋን ካየነው ነገሩ ያስኬዳል ? የፈጣሪውን ክቡር ስራ ነቅፎ ለማረም መሞከር አይሆንም ? የተሰበሰበው ህዝብስ በዚህ መጠን ተላላ መሆኑ “ምድር ተከፍታ ብትውጠኝ” አያሰኝም? ወይስ ሁሉም የቀሽም ተውኔቱ ተካፋይና ተጠቃሚ ነው? “አንድ ሰው ከቤቱ ይዞት የሚመጣው እጅ ስንት ኢንች ነው?፤ በፀሎት ከረዘመ በሁዋላ በስንት ኢንች አደገ? ብሎ የሚጠይቅ አንድ ጠርጣሪ ይጥፋ?

የሚገርመው፤ ሁሌም አንድ “ተአምር” ከታየ በሁዋላ ታምረኞች ሩምታ መዝሙር ከመድረክ ይለቃሉ፤የሩምታው መዝሙር አላማ ምእመኑ ተረጋግቶ እንዳያስብ፤እንዳይመዝን ልቡን መስለብ ነው፤

ባገራችን ፤የእምነት ተግባር ዜጎች መልካም ምግባር እንዲላበሱ ማድረግ መሆኑ ተረስቱዋል፤ የተእምራት ስራ ባብዛኛው ፤ አጋንንትን በማውጣትና በሽተኛ በመፈወስ ዙርያ ታጥሮ ቆይቱዋል፤ እኒህ ነገሮች ለማጭበርበርና ለማደናገር የተመቹ ናቸው፤ ፤ ባለፈው እንዱ ነቢይ አንዲት ምስኪን ሴት መስማት የተሳነው ህፃን ልጁዋን ይዛ ወደ መድረክ እንድትቀርብ ጠራት፤ ነቢዩ ለጥቂት ደቂቃዎች፤ ልጁን ሲያንገላታው ከቆየ በሁዋላ “በስድስት ወር ውስጥ ጆሮው ተከፍቶ ማዳመጥ ይችላል”ብሎ አሰናበታት፤ አዳራሹም በእልልታ ተናወጠ፤የሰለጠነ አገር ውስጥ ቢሆን፤አንድ እሳት የላሰ መርማሪ ጋዜጠኛ፤ የልጁን እናት አፈላልጎ፤ በስድስት ወራት ውስጥ መፈወስ አለመፈወሱን ተከታትሎ ማረጋገጥ ይችል ነበር፤

በከተማችን እንደ ክረምት ሙጃ የፈሉት ነብያት የሚሰሩት ብቸኛ ታእምር ካለ፤ አንድ ማይክ እና የላብ ማበሻ ቁራጭ መሃረብ ይዘው ፤ባጭር ጊዜ ውስጥ ሃብታም መሆናቸው ነው፤ በተረፈ ምንም አይነት ልእለ-ስብ ችሎታ የላቸውም፤አለን ካሉ ደግሞ የሚከተሉትን ነገሮች ሰርተው ያሳዩኝ!

-አምስት እንጀራውን ባርከው በአምስት ሚሊዮን አባዝተው ፤ የተራቡ ወገኖቻችንን ሲመግቡ ያሳዩኝ!

-ኢየሱስ በቃና ዘገሊላ እንዳደረገው፤ ውሃውን ወደ ወይን ጠጅ ይቀይሩልን፤ ኢትዮጵያ የለገዳዲን ወንዝ እንደ ስሙ ፤ወደ ወይን ጠጅ ቀይራ ለውጭ ገበያ እንድታቀርብና እንድትከብር ያድርጉ!

-ሙሴ እንዳደረገው በውሃ ላይ ሰልጥነው ያሳዩን፤ አባይን በነፋስ አውታር አስረው ይገድቡልን፤

-ኢየሱስ እንዳደረገው፤ ፤ሙታንን ያስነሱልኝ! ለናሙና ያክል ይድነቃቸው ተሰማን፤አበበ ቢቂላን፤ ድምፃዊ ንግስት አበበን ፤ ተስፋየ ካሳን ይቀስቅሱልኝ ፤ ሌላው ቀስ ብሎ ይደርሳል

LEAVE A REPLY