ማዕከላዊ አልተዘጋም! /ጋዜጠኛ ውብሸት ታየ/

ማዕከላዊ አልተዘጋም! /ጋዜጠኛ ውብሸት ታየ/

ጠ/ሚ/ር አብይ አሕመድ በጎረቤት አገራት ለዓመታት በአስከፊ እስር ላይ የቆዩ ኢትዮጵያውያንን እያስፈቱ ይገኛሉ። ከእስሩ አስከፊነትና በባዕድ አገር መታሰር ከሚፈጥረው ድርብ ሰቆቃ አንፃር እርምጃው ይበል የሚያሰኝ ነው። ተፈችዎችንና የተፈቺ ቤተሰቦችን እንኳን ደስ ያላችሁ የምንለውን ያህል ለዚህ ውጤት መገኘት የደከሙትን ዶ/ር አብይንና በቀናነት ከጎናቸው የነበሩትን ሁሉ እናመሰግናለን እንላቸዋለን ።

እነዚህ የጎረቤት አገራት ቀደም ባለው የፖለቲካ ባሕላቸውና ውላቸው ሲያከናውኑ የቆዩት ዋንኛ ተግባር ተሰደው በካምፕ የሚገኙ የሙጥኝ ባይ ዜጎችን ሳይቀር እያፈኑ አሳልፎ መስጠትና ለመከራ መሸጥ እንጂ ሌላ አልነበረም።

በዚህ ሁኔታ ጅቡቲ ካፕቴን በሃይሉ ገብሬንና ረ/ካፕቴን አብዮት ማንጉዳይን፣ ኬንያ ኢንጅነር መስፍን አበበንና ኢንጂነር ተስፋሁን ጨመዳን(በቃሊቲ ለዓመታት ተገልሎ በቆየባት ጠባብ ክፍል ውስጥ ራሱን ሰቀለ የተባለ)፣ ሱዳን አንዱዓለም አያሌውንና ሼህ ዑመር ሙሳን፣ የመን አንዳርጋቸው ጽጌን፤ ወዘተ ጭካኔ በሞላበት ሁኔታ አሳልፈው በመስጠትና በሺህ የሚቆጠሩ ዜጎቻችንን ለሰብዓዊ ፍጡር በማይገባ አስነዋሪ አያያዝ በየእስር ቤቶቻቸው በማጎር ይታወቃሉ። በሌሎች የአረብ አገራት የነበረውንና አሁንም የቀጠለውን ግፍና እንግልትም ልንረሳው ወይም ቸል ልንለው አይቻለንም።

ይህን ካልን በሁዋላ ግን ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ የሆንንበትን የውስጣችንን ገመና መለስ ብለን መፈተሽ ይኖርብናል። መጀመርያ መከራ የሚዘራበትን፣ ግፍ የሚኮተኮትበትንና ጥላቻ የሚያብብበትን ማዕከለላዊን ለምን አንዘጋም? ተቋሙን እንዘጋለን ተብሎ ለሕዝብ በይፋ ቃል ከተገባ በሁዋላ በተጨባጭ ግን ለምን ገርበብ ብቻ ተደረገ? ኬኒያና ሱዳን ድረስ ተዘርግቶ ተፅዕኖ ማድረስ የቻለ በጎ እጅ በራሳችን ጓዳ ሲሆን ለምን ሰብሰብ አለ?!

ማዕከላዊ ምርመራ ከተገነባበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 40 ያህል ዓመታት የሕዝብ ልጆች በጭካኔ ተገርፈውበታል፣ አካላቸውን አጥተውበታል እንዲሁም ውድ ህይወታቸውን ሰውተውበታል። ማዕከላዊን እንዘጋለን ሲባል የዚህ ሁሉ ሰቆቃ ምዕራፍ ሊዘጋ ነው ብሎ ብዙ ሰው ተስፋ ቢያደርግ አይፈረድበትም። ማዕከላዊ የደም አበላ ጎርፍ ሲጎርፍበት የኖረና የእናት ኢትዮጵያ የትንሳኤዋ ሃዋርያት እንደወጡ የቀሩበት የታሪካችን ቤርሙዳ በመሆኑ ተምሳሌታዊና ተያያዥ ሁነቶቹ በሙሉ ተቋጭተው ወደ ወመዘክርነት ካልተቀየሩ ፣ ህንጻው ብቻ ሳይሆን በውስጡ ያለፉት ዜጎች የእንግልት ፋይል አብሮ ካልተዘጋ ለተገረበበው በር ዕውቅና አንሰጥም።

አራቱ የኢህአዴግ ድርጅቶች ማዕከላዊንና በውስጡ ያለፉ እስረኞችን ለመፍታት ውሳኔ

ላይ የደረሱት ከብዙ መቋሰል በሁዋላ እንደነበር ክቡር አቶ ለማ መገርሳ የገለጹትንና የገለጹበትን መንገድ አንረሳውም ። በታሪክነቱም ተመዝግቦ ይኖራል። ከዚያ የብዙዎችን ስሜት ሰቅዞ የያዘና ተስፋ ያጫረ የመሪ ንግግር ማግስት የተተገበረው አፈፃፀም ባለሁለት ሚዛን መሆን፤ ከህንፃው ገርበብ ብሎ መቅረት ባሻገር ጥርጣሬንና ስጋትን ይፈጥራል።

ለፖለቲካው ምህዳር መስፋትና ለዴሞክራሲው ማበብ በሚል የተወሰነ ውሳኔ ነው ተብሎ ለኢትዮዮጵያ ሕዝብ ተገልጾ እንደነበር ዳግም ማስታወስ ያስፈልጋል። ለዚህም ሲባል በተግባር የተተረጎሙ ጅምሮች ነበሩ። አሁን ባለንበት ሁኔታ ግን የተባለውን ነገር የበለጠ እውን ሊያደርጉት የሚችሉት ዓይነተኛ መገለጫ ያላቸው ዜጎች የማዕከላዊን መዘጋት በኢቲቪ እየሰሙ በቃሊቲ፣ በቂሊንጦ፣ በዝዋይና በሌሎችም ቦታዎች የመከራውን ዳገት እየገፉት ይገኛሉ።

ይህም አንሶ እንደፍቅረ ማርያም አስማማው ዓይነቶቹ ባልዋሉበት የተጠየቅ ዕዳ ወርዶባቸው በሕግ ሽፋን የወጣትነት ዕድሜያቸውን በመከራው ጣራ ስር እያሳለፉ ነው። ይህ እንደምሳሌነት የጠቀስኩት የ26 ዓመት ወጣት ቂሊንጦ ከመቃጠሉ ከወር በፊት ዝዋይ እኔ ወደነበርኩበት ልዩ ጥበቃ ዞን መጥቶ ስለነበር ከአደጋው በሁዋላ ለምርመራ ሸዋሮቢት ሲወሰድ ብዙዎቻችን “ልትፈታ ነው እየመጣህ ጠይቀን” ብለነው ነበር።

ካፕቴን በሃይሉ በ1997 ዓ.ም ሲታሰር የ25 ዓመት ወጣት የነበረ ሲሆን ዛሬ 40 ዓመት ሊሞላው ወራት የቀሩት ጎልማሳ ሆኗል። ከአስር ዓመት በላይ የቆዩት እነ መስፍን፣ እነከድር ዝናቡ፣ እነነጅብ ጠሃ፣ እነ ኢብሳ ለሚ፣ ወዘተ ገርበብ ብሎ የቀረው ማዕከላዊ ፍሬዎችና የአንዲት ኢትዮጵያ ልጆች ናቸው። አዎ ማዕከላዊ አልተዘጋም። ማዕከላዊ በተጨባጭና ሙሉ ለሙሉ ይዘጋ!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ያስብ፤ ሕዝቧንም ይባርክ!

LEAVE A REPLY