የተሰጠውን ብይን ተከትሎ በችሎቱ ፊት ረብሻ ተነስቷል
/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- የቂሊንጦ እስር ቤት የእሳት ቃጠሎ ተከትሎ በእነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ በ“ሽብር” ክስ ተመስርቶባቸው በነበሩት 38 ሰዎች ላይ ብይን ተሰጠ።
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ በሰጠው ብይን ከ31ኛ እስከ 34ኛ ያሉ ተከሳሾች እንዲከላከሉ፤ 8 ተከሳሾች በነጻ እንዲሰናበቱ እንዲሁም መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤን ጨምሮ ዶክተር ፍቅሩ ማሩ፣ ፍቅረማርያም አስማማው፣አግባው ሰጠኝና ሌሎች 24 ሰዎች በመደበኛ የወንጀል ህግ እንዲከላከሉ መወሰኑ ተገልጿል።
በመጨረሻው የችሎቱን ብይን የተቃወሙ ተከሳሾች ባሰሙት ተቃውሞ ምክንያት ከፍተኛ ረብሻ ተነስቶ ችሎቱን የሚታደሙ ሰዎች መሳሪያ ተደግኖባቸው ከአዳራሽ የወጡ ሲሆን ከፍተኛ ድብደባም ተፈጽሞባቸዋል። ተቃውሞ ያሰሙት ተከሳሾችም ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈጸመባቸውና አንዳንዶቹም ደም እየፈሰሳቸው እንደተመለከተ አንድ የአይን እማኝ ገልፆልናል።
በተሰጠው ብይን መሰረት፦
31ኛ ተከሳሽ ጌታቸር እሼቴ
32ኛ ተከሳሽ ቶፊቅ ሽኩር
33ኛ ተከሳሽ ሸምሱ ሰኢድ
34ኛ ተከሳሽ ፍፁም ጌታቸው በቂሊንጦ ቃጠሎ ሰበብ በተገደሉት ሰዎች ነፍስ እንዲከላከሉ ተበይኖባቸዋል።
6ኛ ተከሳሽ አብዱሉሂ አልዩ
7ኛ ተከሳሽ እስማኤል በቀለ
11ኛ ተከሳሽ ቃሲም ገንቦ
18ኛ ተከሳሽ አንጋው ተገኘ
21ኛ ተከሳሽ ሰይፈ ግርማ
27ኛ ተከሳሽ ዲንሳ ፉፉ
28ኛ ተከሳሽ ናስር ደጉ
29ኛ ተከሳሽ ናኦል ሻሜሮ በነፃ እንዲሰናበቱ ተበይኗል።
መቶ አለቃ ማስረሻ፣ ዶክተር ፍቅሩ ማሩ፣ አግባው ሰጠኝ፣ ወልዴ ሞቱማ፣ ሚስባህ ከድር፣ ፍቅረማርያም አስማማው፣ ደረጀ መርጋ፣ ከበደ ጨመዳ፣ ደሴ አንዳርገው፣ ፍፁም ቸርነት ጨምሮ 28 ተከሳሾች እስር ቤት ውስጥ አመፅ በማደራጀት፣ በመምራት፣ በመሳተፍ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ አንቀፅ 464/2/ሀ፣ ለ፣ 461/ሀ እና 494 /2 ስር እንዲከላከሉ ተበይኖባቸዋል።