በጉጂ ዞን የሰዎች ህይወት እየጠፋ ነው፤ በሞያሌ ግጭቱ ተባብሷል

በጉጂ ዞን የሰዎች ህይወት እየጠፋ ነው፤ በሞያሌ ግጭቱ ተባብሷል

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን የሻኪሶ ወርቅ ማዕድን ኮንትራቱ መራዘሙን ተከትሎ በተቀሰቀሰ ህዝባዊ ተቃውሞ በርካታ ሰዎች ተገደሉ።

በሻኪሶ ጉታ ከተማ አንድ ተዋቂ ባለሀብት በመኪናቸው ውስጥ እያሉ በአጋዚ ወታደሮች በጥይት ተደብድበው ዛሬ ጠዋት መገደላቸው ታውቋል። ትናንት በነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ 3 ሰዎች እንደ ሞቱና ከ7 በላይ ሰዎች ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።

የሚድሮክ ኩባንያ አካል የሆነው ሻኪሶ ወርቅ አምራች ድርጅት ባለፉት 20 ዓመታት የተጠቀመው ኬሚካል የአካባቢውን ማህበረሰብ ለከፍተኛ የጤና ችግር ዳርጎታል በሚል የድርጅቱ ውል ዳግም መታደሱ ተቃውሞ ገጥሞታል። ድርጅቱ ወርቅ በማውጣት ሂደቱ የሚጠቀምበት ኬሚካሎች በተለይም በህፃናት አዕምሮና አካል ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን በፎቶ የተደገፈ ማስረጃዎች እየወጡ ነው።

የሻኪሶ ወርቅ አምራች ኩባንያ የስራ ፈቃድ አሳድሶ ወርቅ የማውጣት ተግባሩን ለመቀጠል ቢሞክርም ማህበረሰቡ የኤሌክትሪክ መስመሮችን ከመጣጠስ ጀምሮ በድርጅቱ ንብረቶች ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን በመወሰዳቸው ለጊዜው ስራ ማቆሙም ተሰምቷል።

በሌላ በኩል በሞያሌ ከተማ ሰሞኑን እንደ አዲስ የተቀሰቀሰ ግጭት የሰው ህይወት አጥፍቷል፤ በርካታ ሰዎችንም ከቀያቸው አፈናቅሏል።

ከሞያሌ ከተማ ነዋሪዎች በስልክ ባገኘነው መረጃ መሰረት “ከተማዋ ዛሬና ትናንት ፀጥ ረጭ ብላለች። ዛሬ እንደ ሰሞኑ የተኩስ ድምፅ አይሰማም። ነዋሪው ከፍተኛ ፍርሃትና ጭንቅ ውስጥ ነው ያለው፤ ማንም ከቤቱ አይወጣም። ሁሉም ሰው በቤት ውስጥ እያሳለፈ ነው፤ ስለ ነገ የምናውቀው ነገር የለም።” ሲሉ አስተያየታቸውን በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ሆነው አካፍለውናል።

LEAVE A REPLY