የላቲኑን ድክመት ለመግለፅ የግድ ላቲኑን ማከል ይኖርብኛል። በዚኽም ላቲኑ ራሡን ይገልፃል ብዬ አምናለሁ። አንዳንድ ሰዎች አማርኛ ራሡን ለመግለፅ እንኳን አይችልም ሲሉ ይደመጣሉ። እንደ ምሣሌም “በላ”ን ያነሣሉ፡ ሌሎችም ምሣሌዎች ዐሏቸው። እንግዲኽ ነገሩ “በላ ልበልሃ” እና “እሡ በላ” ዓይነት ስለኾነ እኔ “በላ ልበልሃ”ን መርጫለሁ።
አማርኛን ደካማ ቋንቋ ለማስመሠል መሞከር ሰዎች በየቋንቋዎቻቸው ሊገልፁ የሚፈልጉትን አጠቃላይ ሃሣብ አለመረዳት ይመስለኛል። ምንጊዜም ከምሣሌዎቼ አንዱ የኾነውን ጀግናው አበበ ቢቂላን ዛሬም ላነሣው እወድዳለሁ። ከኢትዮጵያውያን በስተቀር (ምናልባት ጥቂት በጣት የሚቆጠሩ ሊገኙ ይችላሉ) ስሙን በትክክል ሊጽፉትና ሊጠሩት የሚችሉ የሉም ማለት እችላለሁ። የአገሩ ተወላጅ ግን “XYZ ABC” ማለት “አበበ ቢቂላ” ማለት ነው ለማለት ይችላል። እንደዚያም ብሎ በትክክል ያነብበዋል። ሌላውን ላቲን አንባቢ “አበበ ቢቂላ” ነው ብሎ ያነብበዋል ብሎ መጠበቁ ግን ትክክል አይመስለኝም። ምክንያቱም ላቲን ተጠቃሚዎቹ “ABEBE BIKILA” ብለው ጽፈው (በምንም መንገድ ቢጽፉት በትክክል የሚያነቡበት ዘዴ የላቸውም) “አቢቢ ቢኪላ” ብለው ነው የሚያነቡትና የሚጠሩት። የላቲኑ ፈጣሪዎች ችግራቸው ላቲኑ ያለው ተፈጥሯዊ ችግር ነው።
እንደ “በላ” የመሣሠሉ በርካታ እንግሊዝኛ ቃላት ዐሉ። የቋንቋ ሊቃውንቶቻቸው ማንነታቸውን በደረጃ በደረጃ ለያይተው አስቀምጠዋቸዋል። አንድ ዓይነት ኆኄያት ኖሯቸው የተለያየ ትርጕም ያላቸውን እንደ “t-e-a-r” (ዕንባ ወይም መቅደድ) ኾሞግራፍስ ብለው ይጠሯቸዋል። ኼትሮኒምስ የሚባሉት ደግሞ እንደ ኾሞግራፍ ኾነው ድምፃቸው የተለየ የሚመስሉ ናቸው።
ኾሞኒምስ ማለት እንደ “በላ” ኆኄያቱና ድምፁ አንድ ኾኖ በርካታ ትርጕሞች ያሉት ቃል ማለት ነው። “bear”, “bark”, “write” and “right” ትርጕሙን ለመለየት አብሮት የሚነገር አንቀፅ እንዲኖረው ያስፈልጋል።
ቀጣዩ ምሣሌ ይኽንን ያሣያል።
• read: (ያነባል/አነበበ) She is going to read the book later./He read the book last night.
• bow: (ደጋን/እጅ ንሣ) She put a bow in her daughter’s hair./Please bow down to the emperor.
• minute: (ኢምንት/ደቂቃ) That is only a minute problem./Wait a minute!
• learned: (ተረዳ/ዐዋቂ) The class learned that information last week./He is a very learned individual.
• wind: (ነፋስ/ጠምዝዝ) The wind swept up the leaves./Wind the clock up before you go to bed.
• sow: (ሴት አሣማ/መዝራት) A sow is a female pig./We’ll sow the seeds in springtime.
http://grammar.yourdictionary.com/for-students-and-parents/words-with-multiple-meanings.html
አንድ ቃል እንደ “በላ” ከአንድ ትርጕም በላይ ሲኖረው ፖሊሴሞስ ይባላል። እንደ ኦክስፎርድ የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ገላጭነት ከኹለት በላይ ትርጕም ያላቸው ቃላት በእንግሊዝኛው ውስጥ ዐሉ ይለናል። ከነዚኽም “Set” 464, “Run” 396, “go” 368, “take” 343, “stand” 334, “get” 289, “turn” 288, “put” 268, “fall” 264, እና “strike” 250 እንዳላቸው ይገልፃል።
289 ፍቺዎች ያሉትን የ“get”ን ትርጕሞች ለአብነት ላቅርብ።
“get” ተቀበልኩኝ፣ ተሠማኝ፣ ተቀጣሁ፣ ማግኘት፣ አምጣ፣ ፈልግ፣ አንሣ፣ አገኘሁ፣ መቀበል፣ ገባኝ፤ አለብህ፣ ደረስኩኝ፣ ብቅ በል፣ መግባት፣ ያዘው፣ አሠረው፣ እቀጣሃለሁ፣ አስከፍልሃለሁ፣ ይከፈልሃል፣ አገኘኸኝ፣ አልገባኝም… እያለ ይቀጥላል። ስለዚኽ ይኽንን ያኽል ትርጕሞች ያላቸውን ቃላት በጥሬ ቃላቸው ምን ለማለት እንደተፈለገ ለመግለፅ አናባቢዎችን በማደራረብም ኾነ ነቍጥና ጭረቶችን በመጠቀም ለመለየት ቢሞክር ፈፅሞ የማይቻለው ነው። ለዚኽ ችግር መፍትኄው ግን የቃሉን ትርጕም እንድንለይ የሚያስችለን አረፍተ ነገሩ ነው።
እርግጥ አማርኛን ሊጠቅሙ የሚችሉ ኹለት ፍቺ ያላቸው ቃላት ለሰምና ወርቅ ያገለግላሉ። እንግሊዝኛው እንደ አማርኛው የዳበረ ባይመስለኝም ይኽንን መሠል ቃላት እንዳሉትም ይታወቃል። “A double entendre is a figure of speech in which a spoken phrase is devised to be understood in either of two ways. Often the first (more obvious) meaning is straightforward, while the second meaning is less so: often risqué or ironic.” “Got it” (ተረዱኝ?)
በኆኄያት ተለያይተውና አንድ ዓይነት ድምፅ ያላቸው ቃላት እንደ carat, caret, and carrot፣ ወይም to, two, and too፣ ሌላም “break” ለመስበር “brake” ለልጓም. “ate” and “eight.” rose (ለአበባ) and rose (ለተነሣ), ወይንም “flour” ለዱቄት “flower” ለአበባ ኾሞፎንስ ይሏቸዋል።
ቀጣዩ ምሣሌ የእንግሊዝኛ ውስብስብነትን ለማሣየት የቀረበ ነው።
Seven meanings sounding like “raise”
“… (W)e thought you might like to see it to give you an idea of just how complex the English language can be!”
Raise – to lift something up
Rays – sunbeams
Rase – to erase something
Raze – to knock something down
Rehs – sodium salt mixtures
Réis – plural of real (the currency of Portugal and Brazil)
Res – plural of re, as in the musical scale (doh re mi, for fans of The Sound of Music)
የላቲን ፈጣሪዎች የሚቻላቸውን ያኽል አድርገዋል። የአናባቢዎች ብዛት ምን ያኽል አመቺ እንዳልኾነ በሚገባ ተረድተዋል። ልጆቻቸውን ከወጣትነታቸው ጊዜ ጀምሮ ቃላትን በሽምደዳ እንዲያውቁ ያደርጋሉ። እያወዳደሩም ሽልማት ይሠጣሉ። ምክንያቱም “ኤ.ቢ.ሲ”ን አስተምረው ማንም የተናገረውን በትክክል ለመጻፍም ኾነ የተጻፈውን በትክክል ለማንበብ ሙሉ ለሙሉ አይችልምና ነው። በዚኽ ከግእዝ ጋር ሊወዳደር አይችልም። ስንቶች የቋንቋው ባለቤቶች ይኼ ቃል እንዴት ነው የሚጻፈው ብለው ጠይቀዋችሁ አያውቁም? መዝገበ ቃላት ውስጥ ለማረጋገጥ ጊዜያቸውን አያጠፉም?
ግእዝ እስካሁን ምላስ እየተነከሰ ለምትጠራዋ “the” አዲስ ኆኄ ባይደቅልላትም “ዘ” የምትለዋን ቃል ያለ ችግር መጠቀም ይችላል። በእኔ አመለካከት ምላስን በጥርሶች መካከል አውጥቶ መናገር ብቻ ነው የሚጠይቀው። በተረፈ ላቲኑ የሚያወጣቸውን ድምፆች በሙሉ አካትቶ ላቲኑ ከራሡ ችግር አልፎ “ቀ” “ጠ” “ጨ” “ጸ” “ፀ” እና “ጰ”ን በምንም መልኩ ሊያስተናግድ የሚችል አይደለም።
አማርኛን አማርኛ ያሠኘው የግእዝን ኆኄያት ወርሦና ለራሡ አስፈላጊ የኾኑትን ግእዝ ያላካተታቸውን እንደ “ሸ” “ኘ” “ኸ” “ዠ” “ጀ” እና “ጨ”ን አክሎባቸው ነው። ማናቸውም ቋንቋ ደግሞ ይኽንን ዘዴ በመጠቀም ሊኰራበት የሚችልም አፍሪቃዊ በቀል ኆኄያትን መጠቀም ይችላል።