በጠዋቱ የፕሮፌሰር ገፅ ላይ አንድ ፅሁፍ አነበብኩ። “የአማራ ፋሽዝም” ይላል። ጥቅስ ውስጥ እንኳን አላስገቡትም። እንደተረጋገጠ ሀቅ የፃፉት ነው። አላመንኩም። ደግሜ አየሁት። ከሌላ ሰው ጋር አየሁት። ያው ነው!
ፋሽዝም ወንጀል ጭምር ነው። ሌሎች ላይ የዘመተ፣ የፈጀ ርዕዮት አለም ነው። በጀት ብቻ ሳይሆን በመርዝ ጋዝ፣ የሰውን ልጅ ታይቶ በማይታወቅ ጭካኔ የጨረሰ ርዕዮት አለም ነው። ፋሽዝም ፋሽስቶቹ የእኛ ነው ብለው የወሰዱት ርዕዮትም ጭምር እንጅ ፍረጃ ብቻ አይደለም።
ፕሮፌሰር ርዕዮቱን እንደ ህዝብ የለም ለሚሉት አማራ ጠቅልለው ሲሰጡት አይቼ ማመን አቃተኝ። ለዚህ ደግሞ መነሻቸው ስሙን ያልጠሩት ግለሰብ ነው። ምን አልባት በማይታወቅ ስም ፌስቡክ ላይ ፅፎ አንብበው ይሆናል። እኔ ጠይቄ ማን እንደሆነ አላወኩም።
እሽ ይሁን!
ፕሮፌሰር በግለሰብ ማንነት አምናለሁ የሚሉ ሰው ናቸው። አንድ ሰው ተነስቶ ስለ ፈለገው ሊፅፍ ይችላል። ለምሳሌ አንዱ የውጭ ሀገር ቱሪስት ስለ ወደደው ሕዝብ አሞካሽቶ ሊፅፍ ይችላል። ያ የውጭ ሰው ስለ ሌላ ሀገር ሕዝብ ስለፃፈ በዛ አንድ ፀሀፊ ስም ሕዝብ ይፈረጃል? ያውም ወንጀል በሆነ ርዕዮት አለም?
እሽ! ያ ግለሰብ ከፃፈለት ሕዝብ የወጣ ይሁን። አንድ ግለሰብ ከፃፈው የግል አስተያየት ተነስቶ ሕዝብ ወንጀል በሆነ ርዕዮት ይፈረጃል? ወኪልነቱም ይቅር! ያ ሰው ሆን ብሎ በህዝብ ስም የሚጠቀም (ደህንነት) ይሁን ታጋይ ሳያረጋግጡ? ስሙን ሳይጠቅሱልን ህዝብ ይወነጀላል? የህዝብ ርዕዮት ዓለም ይሆናል?
ሰውየው ህዝብን ወክያለሁ የሚልም ይሁን። ህዝብን ወክያለሁ ብሎ የተናገረ ሁሉ የፃፈው ሕዝብን ለመፈረጅና ለመወንጀል ያበቃል? “አማራ ነን፣ የአማራ ወኪል ነን” የሚሉ ቡድኖችን “አማራ የለም” ብለው ሲሞግቱ የኖሩ ሰው እንዴት ስሙን መጥራት ባልደፈሩት ግለሰብ አቋም ሕዝብን ይፈርጃሉ? ይወነጅላሉ?
ፕሮፌሰር ያን ለሕዝብ መፈረጃ ያደረጉትን የማይታወቅ አካል ያወዳደሩት ከጨፍጫፊው፣ ከአሳሪው መለስ ዜናዊ ጋር ነው። መለስ ዜናዊ የፓርቲም፣ መንግስት የሚለውም አናት ነበር። ይህኛውም ግለሰብ ነው። ያውም ስሙን መጥራት ያልቻሉት። በምን መስፈርት ነው መለስና አንድ ግለሰብ እኩል የሚወዳደሩት?
ፕሮፌሰር ሕዝብን ለመፈረጅ የደፈሩባቸው ቃላት የአማራን ሕዝብ የሚያሞካሹ እንጅ ሌላውን የሚያዋርዱ፣ የሌላውን ህዝብ ስብዕና የሚነኩ አይደሉም። ዶ/ር አብይ ጎንደር ላይ የተናገሩት ከዚህም በላይ ነው። ዶ/ር አብይ ሕዝብን አሞካሽተው በመናገራቸው አማራ ፋሽስት ይባላል? ነው ፋሽዝም ትርጉሙ ተቀይሯል?
ፋሽዝም የገዥዎቹ፣ የጨፍጫፊዎች እንጅ የግፉአን ርዕዮት አይደለም። ይህ በዳስ ትምህርት ቤት የሚኖር፣ ከቀየው የሚፈናቀል፣ የሚኮላሽ፣ የሚገረፍ፣ በጅምላ የሚታሰር፣ ገዥዎች በፖሊሲ የሚያሰቃዩት ሕዝብ በምን መመዘኛ የሁለተኛውን የዓለም ጦርነት በመሩት ጥጋበኞች ስም ይፈረጃል? ፕሮፌሰር ምን ነክቷቸዋል?
ብሔርተኞች ጠርዝ ሊይዙ ይችላሉ። ይይዛሉም። በእኛ ሀገር ብሔርተኛ ሞልቷል። ይህን ፕሮፌሰር ባለፉት 26 አመት ከዛም በላይ አይተውታል። ግለሰቦች የወጡበትን ሕዝብ ሲያሞከሹ ኖረዋል። በብዙ ነገር። ያም ፋሽዝም ስላልሆነ መፈረጅ አልነበረበትም። አይገባምም። ፕሮፌሰርም አልፈረጁም። ጥሩ ነው። ቢፈረጅም ሌላ ስም ይኖረዋል። አለውም። ታዲያ ለምን የለም የሚሉት አማራ ላይ?
በጣሊያን ትልቁ የከፋ በደል ከደረሰበት ሕዝብ አንዱ የአማራ ሕዝብ ነው። ፋሽቶቹ በቀደዱት ቦይም ስልጣን እንደያዙ ከእነ ፕሮፌሰር ጋር ቁጭ ብለው በይፋ ስለ አማራ ሕዝብ ያወሩት እነ መለስ አማራን አሰቃይተዋል።
የፋሽዝም ሰለባ ከሆነው ሕዝብ መካከል የአማራ ሕዝብ ይጠቀሳል። በውጭም በሀገር ውስጥም ፋሽስቶች። እንዴት የፋሽዝም ዋነኛ ሰለባ የሆነ ሕዝብ በዚህ ገዳይ ርዕዮት፣ የገዥዎች ርዕዮት አለም ስም ይፈረጃል? ኧረ ፕሮፌሰር ምን ነካቸው? በእርግጠኝነት ግን እርጅና አይደለም!