/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ግዕዝ ቋንቋን ማስተማር መጀመሩን አስታወቀ። በሀገሪቱ ታሪክ የግዕዝ ቋንቋ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርሲቲያን አልፎ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ሲሰጥ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ መሆኑንም ጨምሮ ገልጿል።
ዩኒቨርሲቲው በየትኛውም የትምህርት መስክ የመጀመሪያ ድግሪ ያላቸውን ተማሪዎች ተቀብሎ በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ-ግብር ማስተማር መጀመሩን ገልፆ እስካሁን ከ32 በላይ ተማሪዎችን መቀበሉንም አስታውቋል።
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት (School of Humanity dean) ክፍል ሀላፊ የሆኑት ዶክተር ዳዊት አሞኘ እንደገለጹት ትምህርቱ ለጥናትና ምርምር በሚያስችል መንገድ እንደሚሰጥ ገልጸዋል። በመሆኑም በግዕዝ ቋንቋ በተፃፉ ሰነዶች፣ በቋንቋው የአጻጻፍ ዘይቤ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ምርምር ይካሄዳል ብለዋል።
ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የግዕዝ ቋንቋን በሦስተኛ ዲግሪ ለማስተማርም ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል። ዩኒቨርሲቲው የኦሮምኛ ቋንቋን ለማስተማር መዘጋጀቱንም ባለፈው የካቲት ወር መግለጹ ይታወሳል።