ዶ/ር አብይ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስራቸውን ከጀመሩ ሰባት ያህል ሳምንታት ተቆጥረዋል። ወደ ስልጣን የመጡበት መንገድ ከተለመደው እጅግ የተለየ መሆኑ እንኳን ለወገን ለባዳም ግልፅ ነው። ወያኔ እንደከዚህ በፊቱ በአምሳሉ ጠፍጥፎ ያወጣቸው፤ አልያም ህዝብ ይሆኑኛል ብሎ በድምፁ የመረጣቸው ሹም አይደሉም። አብይ በገዛ ቤታቸው ውስጥ በተፈጠረ ፍትጊያ መሀል የተከሰቱ ናቸው። አመጣጣቸው በፓርቲያቸው ውስጥ ያለውን ትርምስ ገሀድ ማውጣቱ እንዳለ ሆኖ ሰውየው የኢህአዴግ ፍሬ ከመሆናቸው ጋር ሲታሰብ ራሳቸውን ለህዝብ ያቀረቡበት መንገድ ብዙዎችን አስደምሟል። ህዝብ መርጦ በቦታው ባያስቀምጣቸውም ህዝብን ለማዳመጥ ራሳቸውን ያዘጋጁ ለመሆናቸው የእስካሁን ጉዟቸው የሚመሰክር ይመስለኛል።
በነዚህ ሰባት ሳምንታት አብይ በሩጫ ተጠምደው ሰንብተዋል። ሀገሪቱን በአራቱም አቅጣጫ ከጫፍ እስከጫፍ አዳርሰዋታል። ከአዲስ አበባ ጀምሮ ጅጅጋ፣ አምቦ፣ መቀሌ፣ ጎንደር፣ ባህር ዳር፣ አሶሳ፣ ባሌ ሮቤና ሌሎችም ቦታዎች በመሄድ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር መክረዋል፣ የህዝቡንም ብሶት አዳምጠዋል። በየሄዱበት ለ27 ዓመታት በወያኔ የዘረኝነት፣ የጥላቻና የልዩነት ጦር የቆሰለውን ህዝብ ኢትዮጵያዊነትን፣ ፍቅርንና አንድነትን እየሰበኩ ለማከም ሞክረዋል። የነበረውን ውጥረት አርግበው ለመበታተን ጫፍ ደርሳ የነበረችውን ሀገር በአንፃራዊ ሁኔታ አረጋግተዋል። ከተመረጡበት ሁኔታና ለዝግጅት ከነበራቸው አጭር ግዜ አንፃር ከጅማሬው አንስቶ ያደረጓቸው ንግግሮች ስፋትና ጥልቀት እንዲሁም ትከሻ ለትከሻ የሚታከኳቸውን የወያኔ ጀሌዎች ተቋቁመው የሚሄዱበት መንገድ የሚደነቅ ነው። በንግግሮቻቸው የሚያነሷቸው ነጥቦችና ከህዝብ ጋር የሚያካሂዷቸው ውይይቶች የዝግጅታቸውን ጥልቀትና ትጋታቸውን ይመሰክራሉ።
ወያኔ ከኛው አልፎ ለባዕድ በሚታይ መጠን ያደረሰብንን ውርደት ለመጥረግ በአጎራባች ሀገራት ያደረጓቸው ጉብኝቶችና መልካም ተርባራትም ይበል የሚያሰኙ ናቸው። ከሀገራቸው በግፍ መሰደዳቸው አልበቃ ብሎ በባዕድ ሀገር ወህኒ ተወርውረው አስታዋሽ ያጡና በህይወት ይኑሩ አይኑሩ የማይታወቁ በርካታ ወገኖች ከሱዳን፣ ከኬንያና አሁን ደግሞ ከሳዑዲ እስር ቤቶች እንዲለቀቁ አስደርገዋል። በሊቢያ ወገኖቻችን ሀይማኖትና ሀገራቸው ተወግዞ በአደባባይ አንገታቸው ሲቀላ ‘ቆይ ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ላጣራ’ እያለ ሲያላግጥ በነበረ አረመኔ ቦታ የወገኑ መጎዳት የሚያንገበግበው ሰው ተቀምጦ ማየት ልብን በተስፋ ይሞላል። ያዝልቀው!
አንዳንዶች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጉዞ እንደሽርሽር፣ ንግግሮቻቸውንም እንደ ልታይ-ልታይ ባይነት ሲቆጥሩ ይስተዋላል። ይህንንና መሰል አስተያየቶች የሚሰጡ ሰዎች አብይ በነዚህ ሰባት ሳምንታት መስራት
የነበረባቸውና ያልሰሩት ምን እንደሆነ በግልፅ ሲገናሩ ብሰማ ደስ ባለኝ ነበር። በበኩሌ ግን ትችታቸውን ለመቀበል ይቸግረኛል፤ ምክንያቱም ለህዝብ የሚበጅ ነገር ለመስራት በቅድሚያ ህዝብን ማድመጥ የግድ ይላልና። አብይም እያደረጉ ያሉት ይህንኑ ይመስለኛል። በዙሪያቸው በተኮለኮሉት የወያኔ ባለሟሎች ላይ ሊጥሉ የሚችሉት ተስፋና እምነት ባለመኖሩ ለስኬት ያላቸው ብቸኛ አማራጭ ህዝብን አጥብቆ መያዝ ነው። ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የሚያደርጉት ውይይት ሀሳባቸውን ለህዝቡ ይፋ የሚያደርጉበትና በዙሪያቸው ኃይል የሚያሰባስቡበት ብሎም ተቀባይነታቸውን የሚያሳድጉበት መሳሪያ ነው። ከህዝቡ የሚያገኙት ሀሳብና ጥቆማ አካሄዳቸውን ለማስተካከል ግብዐት ይሆናቸዋል። አብይ በበርካታ አመለካከቶቻቸው ከወያኔ ጋር በእጅጉ እንደሚራራቁ እያስተዋልን ነው። ወያኔ ለ40 ዓመታት እያመነThከ ያለውን የዘረኝነት ፖለቲካ አብይ ‘የትንሽነት መገለጫ’ ሲሉ ያንቋሽሹታል። ኢትዮጵያዊነት በወያኔ እንዳልተራከሰ ሁሉ አብይ ዘንድ ነግሷል፣ ኢትዮጵያና ታሪኳም እንዲሁ። ወያኔ ‘ከዕድገት በኋላ ይደረስበታል’ የሚለው ዴሞክራሲ ለአብይ ግዜ የማይሰጥና አጣዳፊ ነው። አብይ የሚሰብኩት የግለሰብን መብት የማክበር ጉዳይ ወያኔ ከተጠመቀበት አብዮታዊ ዴሞክራሲ ጋር ፈፅሞ አይተዋወቅም። አብይ እነዚህንና ሌሎች መልካም አመለካከቶቻቸውን እውን ሊያደርጉ የሚችሉት ህዝብን ሲይዙ ብቻ መሆኑን ጠንቅቀው ያወቁ ይመስላል።
ጠ/ሚ አብይ ስልጣን ከተረከቡበት ዕለት ጀምሮ ባደርጓቸው ንግግሮች በርካታ ነገሮችን ለማከናወንቃል ገብተዋል። ወያኔ ለ27 ዓመታት እንቅልፍ አጥቶ ሲያፈርስና ጥላሸት ሲቀባ የኖረውን ጉድ ማስተካከልና ማፅዳት የሚወስደው ግዜና የሚጠይቀው ትዕግስት ቀላል ባይሆንም ትኩረታቸው ቅድሚያ ሊሰጣቸው በሚገቡ አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ቢያርፍ መልካም ነው እላለሁ። የፍትህ ስርዐቱንና የምርጫ ተቋሙን ነፃ ለማድረግ መስራት፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ተሳታፊ የሚያደርግ እውነተኛ የፖለቲካ መድረክ መዘርጋት፣ ዘረፋና ሌብነትን ማስወገድና የሀገርና የህዝብ ሀብት ሲዘርፉ የኖሩትን ለፍትህ ማቅረብ፣ እንዲሁም በልዩነት አለንጋ ሲገረፍ የኖረውን ህዝብና ሀገራችንን ከጥፋት ለማዳን በሀገራዊ አንድነት ላይ ይበልጥ መስራት ፋታ ሊሰጣቸው የማይገቡ ጉዳዮች ይመስሉኛል። በውጭ ሀገራት እንዳደረጉት ስፍር ቁጥር የሌላቸውን የፖለቲካ እስረኞች ከሀገሪቱ የማሰቃያ ቤቶች ነፃ ማስወጣት ሌላው ጠ/ሚ አብይ ከሚፈተኑባቸው ጉዳዮች አንዱ ነው። በእነዚህ ወሳኝና አጣዳፊ ጉዳዮች ላይ በተወሰነ ደረጃ ለውጥ ማምጣት የሚችል ስራ ከሰሩ ለሀገራችንና ለህዝቧ እንዲሁም ለራሳቸው ትልቅ ስኬት ይሆናል። ትግሉ ቀላል ባይሆንም በህዝብ ድጋፍ የመከላከያ፣ የደህንናትና የኢኮኖሚ መዋቅሩን ከወያኔ ማነቆ ማውጣት ሌላው አብይን የሚጠብቃቸው ስራ ነው።
እርግጥ ነው ራሳቸው አብይ የሚወክሉት ፓርቲ በልዩነት እየታመሰ ሌሎች የፖለቲካ ሀይሎችን ሰብስቦ በጋራ ለመስራት መምከር አስቸጋሪነቱ የሚታይ ቢሆንም ተፎካካሪዎችን ተሳታፊ ማድረግ በቋፍ ያለውን ወያኔ ከነግልገሎቹ ቅርቃር ውስጥ ለመክተት አንዱ መንገድ ሊሆንላቸው ይችላል። በዚህ በኩል ለውይይት በሚጋበዙ ሀይሎች ላይ አድሎና ልዩነት ማድረግ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ ቀላል ስለማይሆን ሁሉንም ሀይሎች ያሳተፈ ውይይት ላይ ማተኮር ምርጫ አይኖረውም። ጠ/ሚ አብይ በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን አለመግባባት ለመቅረፍ እንደሚጥሩ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። ሀሳቡ መልካም ቢሆንም የሚከተሉት መንገድ እስከዛሬ ከተሄደበት የተለየ ካልሆነ ውጤቱ ‘ውሀ ቢወቅጡት እምቦጭ’ መሆኑ አይቀሬ
ነው። ኤርትራ ‘ባድመ ካልተሰጠችኝ አሻፈረኝ’ እንደምትለው ሁሉ እኛም ታሪክና ህግ በሚደግፉት መልኩ የሚገቡንን ቦታዎች በአግባቡ መጠየቅ ይኖርብናል። በነመለስ ውስልትናና ቁማር ያጣነው የአሰብ ጉዳይ ለውይይት የሚቀርብበት ግዜ አሁን ነው።
የአብይ ወደ ስልጣን መምጣት ጠቀሜታው ለኢትዮጵያና ለሀገር ወዳድ ህዝቧ ብቻ ሳይሆን ለወያኔና ለግልገሎቹም ጭምር ሊሆን እንደሚችል የሚናገሩም አልጠፉም። ወያኔ ሀገር ድምጥማጧ ቢጠፋ የሚገደው ባይሆንም፤ ይህ በዚህ ወቅት እንዲሆን የፈለገና የተዘጋጀ ግን አይመስለም። ከዚህ አንፃር ወያኔ ከእጁ አምልጣ ልትከሰከስበት የነበረችውን እንቁላል አብይ አድነውለታል ለማለት ይቻላል። በሌላ መልኩ ይህ አጋጣሚ የዘረፉትን ሀብት ይዘው ድምፃቸውን ሳያሰሙ ራሳቸውን ገለል ለማድረግ ለሚያስቡ የወያኔ ግልገሎች ልዩ እድል የተፈጠረላቸው አድርገው እንደሚያስቡ መገመት ይቻላል።
ሳጠቃልል – በርካታ የታሪክ ምዕራፎችን እየተሻገረች እዚህ የደረሰችው ሀገራችን አሁንም ወሳኝ ከሆነ ሌላ ምዕራፍ ላይ ደርሳለች። ይህን ታሪካዊ አጋጣሚ በአግባቡ ተጠቅሞ ሀገራችንን ከጥፋት ማዳን የሁላችንም ሀላፊነት ነው። አንድ ግለሰብ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል እኩል የሚያስደስት ነገር እንዲያከናውን መጠበቅ የዋህነት ቢሆንም አብይ ለሀገራችን የሚበጀውን እንዲሰሩ ማገዝ፣ ሲሰሩ ማወደስ፣ ሲሳሳቱ መገሰፅ፣ ሲረሱም ማስታወስ የኛ የዜጎች ሀላፊነት ነው።
እግዚዐብሔር ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይጠብቅ!