ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ ፖለቲካዊ አቋሞች በእስር ላይ የነበሩ ኢትዮጵያውያን በመፈታት ላይ ይገኛሉ። ሁነቱ እንደሚቀጥልም እየተገለፀ ይገኛል።
በተስፋ እየጠበቅን ነው። በእርግጥ የሚያስጨንቅ ስጋትም አለን። ለዚህ በአጭሩ ሶስት ምክንያቶችን ማስቀመጥ እንችላለን።
1ኛ ፦ በቅርቡ ክሳቸው ከተቋረጠውና እነ ፍቅረማርያም አስማማው ካሉበት ስብስብ ውስጥ የተወሰኑት ቢወጡም አብዛኞቹ አሁንም በእስር ላይ ይገኛሉ።
2ኛ ፦ ጠ/ሚ/ሩን ጨምሮ በጉዳዩ ዙርያ መረጃው ሊኖራቸው የሚችሉ ወገኖች ፍችን አስመልክቶ በይፋ ተስፋ ከተሰጠባቸው አቶ አንዳርጋቸው ፅጌና የተወሰኑ ዜጎች ውጪ ስላሉት ወንድሞቻችን እጣ ፈንታ ማረጋገጫ ማግኘት አልተቻለም።
እንደሚታወቀው ጅቡቲ ሄዶ የፖለቲካ ጥገኝነት ብቻ የጠየቀው ካፕቴን በሃይሉ ዕድሜ ልክ ተፈርዶበት እስካሁን ለ14 ዓመታት ቆይቷል። ኢንጂነር መስፍን አበበ ከኬንያ ተላልፎ ከተሰጠ ጊዜ ጀምሮ(ጓደኛው ኢንጂነር ተስፋሁን ጨመዳ በእስር ቤት ተሰውቷል) እስካሁን ለ12 ዓመታት ቆይቷል። ነጅብ ጠሃ(የክስ አባሪው ባለፈው በይቅርታ የተለቀቀች በመሆኑ የይቅርታ ሕጉ በመርህ ታሳቢ የሚያደርገው)፣ ከበበ ግርማ፣ ዳንኤል አያና፣ ከድር ዝናቡ፣ ወዘተ(እዚህ ላይ የጠቀስኳቸው በቅርብ የማውቃቸውንና ለተምሳሌታዊነቱ እንጂ በመሰል ሁኔታ ውስጥ ያሉትን ሁሉ ታሳቢ ያደረገ ነው) ጉዳያቸው በዚሁ ወቅት በጎ ውሳኔ ያገኛል ከሚል ምኞት የዘለለ ምልክት ማየት አልተቻለም።
3ኛ ፦ ከሶማሌ ክልል የመጡ ወንድሞቻችን ጉዳይ ነው። ከ1999 ዓእነዚህ.ም ጀምሮ በእስር ላይ ናቸው። እነዚህ የመከራውን ቀን አብረውን የገፉ ዜጎች ባገባደድነው ዓመት ወርሃ የካቲት መባቻ ላይ ከእስር እንደሚለቀቁ የምስራች ከተነገራቸው በሁዋላ አብዛኞቹ ከዝዋይ ወደቃሊቲ ከዚያም ወደኦጋዴን ክልል ሄደው (የነበሩበት ሁኔታ ተባብሶ ከቤተሰብ ጋር እንኳ መገናኘት ተከልክለው እንዳለ ቤተሰቦቻቸው ቅሬታቸውን እያሰሙ ይገኛሉ።)
አሁንም በእስር ላይ ይገኛሉ። “መንግስት ይቅርታ አድርጎላችሁዋል ዕቃችሁን አዘጋጁ” የተባሉ ቀን የኢትዮጵያን ሕዝብ ውለታ ከፍለው እንደማይጨርሱ፤ በአዲሱ አስተዳደር ላይም በጋራ አገርን የመገንባት ተስፋ እንዳላቸው ሲያወጉን ነበር። መጨረሻቸው ምን ይሆን?
በስም የማውቃቸውን የተወሰኑትን ልጥቀስ፦ መሐድ ሼህ ኢብራሂም ሐሰን መሐመድ መሐመድ ዩሱፍ ከማል ሼህ አብድናስር ከድር ሹግሪ አረብ ሲአኔ ሐሰን አሐመድ ሙክታር መሐመድ(የሞት ፍርደኞች)..ኢርሻድ አቂብ አብዱላህ ዑመር አብዲ አሕመድ አብዱረዛቅ ሼህ ዩሱፍ እና መሐመድ የሱፍ እያንዳንዳቸው የዕድሜ ልክ ፍርደኞች ናቸው። ሌሎች እንደነ አህመድ ያሲንና ከድር አደን ያሉ እስከ 20 ዓመት የተፈረደባቸውም አሉ።
ስለእስሩ መንስኤ በእስሩ ወቅት ስለሚፈፀሙት ግፎችና የመሳሰሉት ለጊዜው እንተወውና በተጠቀሰው ጉዳይ ዙርያ የሚደረግ የይቅርታ ፍች ዓላማ ከዚህ በፊት እንደተባለው ለፖለቲካዊ ምህዳሩና ለዴሞክራሲው መስፋት ነው በሚለው መርህ መሰረት ይህን በጎላ ሁኔታ ዕውን ሊያደርጉ የሚችሉት ከላይ የጠቀስናቸውና ሌሎችም ናቸውና ሁሉም ወገኖቻችን ተፈተው ስለቀጣዩ በጎ ነገር በቀጣይ ለመነጋገር እንዘጋጅ።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ያስብ፤ ሕዝቧን ይባርክ!