የስፖርት ፌዴሬሽኑ የስብሰባ ውሎ እና የነገው ቀጠሮ! /ዳዊት ከበደ ወየሳ እንደዘገበው/

የስፖርት ፌዴሬሽኑ የስብሰባ ውሎ እና የነገው ቀጠሮ! /ዳዊት ከበደ ወየሳ እንደዘገበው/

በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በዶ/ር አብይ አህመድ የቀረበውን ጥያቄ አስመልክቶ 5 ሰአት የፈጀ ውይይት አድርጎ ነበር። በዚህ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ከተለያዩ የአሜሪካ ክፍለ ግዛት የሚወከሉ የ31 ቡድን ወኪል የሆኑ የቦርድ አባላት ተገኝተው፤ በዶ/ር አብይ አህመድ በኩል የቀረበውን ሃሳብ በሰፊው ተወያይተውበታል። ይህን አስቸኳይ ስብሰባው የመራው የስፖርት ፌዴሬሽኑ ፕሬዘዳንት አቶ አብይ ኑርልኝ ሲሆን፤ ስብሰባው በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ያደረገውን ጥረት አባላቱ አድንቀውለታል።

የስፖርት ፌዴሬሽኑ  ቅድሚያ በመስጠት የተወያየው፤ የፌዴሬሽኑ ደጋፊዎችን በማያስቀይም መልኩ ውሳኔ ላይ መደረስ እንዳለበት ስምምነት ላይ ደርሷል። “ህዝቡ ከፌዴሬሽኑ የሚጠብቀው ምንድነው? ደጋፊዎችን ማስደሰት የምንችለው በምን መልኩ ነው?” በሚሉት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ቅድሚያ በመስጠት ውይይት አድርጓል።

ከዚያም የፌዴሬሽኑ የቦርድ አባላት ሃሳባቸውን የሚገልጹበት መድረክ ተከፍቶ፤ “ዶ/ር አብይ አህመድ መገኘት አለበት” የሚሉትና “አሁን መምጣት የለበትም” የሚሉት ሁለት ወገኖች ሃሳባቸውን በነጻነት አንሸራሽረዋል።

በአንድ ወገን… “በተጨባጭ ህዝቡ ፍትህ እያገኘ አይደለም። አሁንም ሰዎች እየተፈናቀሉ፤ እየታሰሩ እና እየተገደሉ ናቸው። ስለዚህ ምን ስራ ሰርቶ ነው የምንጋብዘው?” በማለት ሃሳባቸውን የገለጹ የቦርድ አባላት የመኖራቸውን ያህል፤ በሌላ በኩል ደግሞ፤ “አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረው የዲሞክራሲ ጭላንጭል ሊዳፈን አይገባም። ለዚህ ጅምር ደግሞ ዶ/ር አብይን ማበረታታት አስፈላጊ ነው። በፌዴሬሽኑ ‘የኢትዮጵያ ቀን’ ዝግጅት ላይ መገኘት አለበት” እስከሚሉት ድረስ ውይይቱ ተጠናክሮ ቀጥሎ ነበር።

በመጨረሻ ላይ ተሰብሳቢዎች የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር፤ ዶ/ር አብይ አህመድ ለጻፈው ደብዳቤ እና ስላቀረበው ጥያቄ በኢትዮጵያዊ ጨዋነት አመስግነው፤ እንደአስታራቂ ሆኖ በቀረበው ሃሳብ ላይ የመደምደሚያ ውይይት አድርገዋል። አስታራቂ ሆኖ የቀረበውም ሃሳብ፤ “ዶ/ር አብይ አህመድ የሚገኝ ከሆነ፤ ከሌሎች ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶችም የሚወከሉ መሪዎች በኢትዮጵያ ቀን ዝግጅት ላይ ሊገኙ ይገባል።” የሚለው ነው።

ነገ ድምጸ ውሳኔ የሚሰጠው በዚህ የመጨረሻው አስታራቂ ሃሳብ  ይሆናል። ይኸውም፤ “ዶ/ር አብይ አህመድ የሚገኝ ከሆነ፤ ከሌሎች ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶችም የሚወከሉ መሪዎች በኢትዮጵያ ቀን ዝግጅት ላይ ሊገኙ ይገባል።”  በሚለው ሃሳብ ላይ መስማማት ወይም አለመስማማታቸውን ያሳውቃሉ። የድምጽ አሰጣጡ በ24 ሰአት ውስጥ ይከናወናል።

በነገራቹህ ላይ… የስፖርት ፌዴሬሽኑ የቦርድ አባላት ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የተመረጡና ለየቡድኑ ሁለት ሁለት ተወካይ በመሆን፤ ቡድን እና ክፍለ ግዛታቸውን የሚወክሉ ናቸው። እነዚህ የቦርድ አባላት  የሚያቀርቡት ሃሳብ እና የሚሰጡት ድምጽ የመጨረሻ ይሆናል። ወደ አሁኑ ሁኔታም ስንመለስ፤ የቦርድ አባላቱ ከዛሬው ስብሰባ በበቂ ሁኔታ ጉዳዩን ተረድተዋል ተብሎ ይገመታል። በመቀጠል ማድረግ የሚጠበቅባቸው ከወከላቸው ህዝብ ጋር በመነጋገር በነገው እለት የውሳኔ ድምጽ መስጠት ይሆናል።

የድምጹ አሰጣጡ የቦርድ አባላቱ ባስመዘገቡት ኢሜይል አማካኝነት የሚላክላቸው ሲሆን፤ ድምጻቸውን በ24 ሰአት ውስጥ መስጠት ይኖርባቸዋል። በመጨረሻም ግልጽ በሆነ መንገድ የተሰጠው ድምጽ ይቆጠራል። ውጤቱንም የፌዴሬሽኑ ስራ አስኪያጅ ለህዝቡ ይፋ ያደርጋል።

በመጨረሻም… ውሳኔው ምንም ሆነ ምን የፌዴሬሽኑ አባላት በዲሞክራሲያዊ መንገድ ተነጋግረውና ተማክረው የሚሰጡት ድምጸ ውሳኔ ሊከበር ይገባል። የፌዴሬሽኑ አባላት በአብላጫ ድምጽ ውሳኔ የሚያምኑ ናቸው። በሰለጠነው አለም የምንገኝ ሰዎች የአብላጫውን ድምጸ ውሳኔ የምናከብር እንደመሆናችን መጠን፤ የነገውን ውሳኔ ብንወደውም ሆነ ብንጠላው ልናከብር ይገባናል  – መልእክታችን ነው

LEAVE A REPLY