የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ የግንቦት 20 ክብረበዓልን አስመልክተው ካደረጉት ንግግር በዘሪሁን ገመቹ ተቀጭቦ የተተረጎመ፦
“ከአሁን ወዲህ ተገቢውን የህዝብ ድምጽ ሳያገኙ እዚህ ወንበር ላይ መቀመጥ አይቻልም” “ሶስት ሰዓት አንብቤ 30 ደቂቃ ድንቅ ንግግር ማድረግ ቀላል ነው፤ መስራት ነው የሚከብደው ።ዴሞክራሲ በወሬ ብቻ አይመጣም፤ የሚሰባበረውን መሰባበር የሚነቀለውን መንቀል ያስፈልጋል።
ባህላችንም ዴሞክራሲን እንዲሰፋ የሚያግዝ ሳይሆን በተቃራኒው እንዲቀጭጭ የሚያደረግ ስለሆነ እሱ ላይም መስራት አለብን።
እስረኛውን እንደወራጅ ወንዝ እየለቀቅን ያለነው እስርቤት ለመዝጋት እቅድ ስላለን ሳይሆን አዲስ የፖለቲካ አየር ለመፍጠር ስለምንፈልግ ነው።
በኦሮሚያ በአንድ አመት ውስጥ 40ሺ እስረኛ በላይ የለቀቅነው ግለሰብን ብቻ ነፃ ለማውጣት ስለምንፈልግ እንዲሁም ለመወደድ ወይም እንዲጨበጨብልን ስለፈለግን ሳይሆን የመጠላለፍ እና የመጠፋፋት ባህላችንን ለመቀየር ነው።
ሰዎችን ከእስርቤት ብቻ አይደለም ነጻ ያወጣነው . . . ተሰደው የዜግነት መብታቸውንም ካጡበት የስደት ኑሮ ነው . . . ከባዕድ ሀገር እስር ቤት ጭምርም ነው ።
ታሪክ እየቀየርን ነው . . . ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲ ከያሉበት ግቡና አብረን እንሥራ የምንለው የፖለቲካ ገበያ ለመክፈት ሳይሆን በእውነት እና በሀቅ የሀገሪቱን ታሪክ ለመቀየር ስለምንፈልግ ነው። በቦረና በኩል በስደት የወጡትን በቦሌ በኩል እንዲገቡ ያደረግነው ሞተው ሬሳቸው ተጭኖ ከሚመጣልን ይልቅ በህይወት መጥተው ለህዝባቸው እንዲሰሩ እና እንዲያገለግሉ ነው። የሀገሪቱ ዜጋ መሆናቸው እንዲረጋገጥላቸው ነው። እነዚህ አካላት ሀገር ውስጥ ሆነው በህዝባቸው መሀከል ሆነው ሲሰሩ ነው የሚያወሩትን ለውጥ በተግባር ሊያመጡ ሚችሉት።
ኦህዴድ “ኦፒዲኦ” ስለሆን ለዘመናት ይጠየፉን እና ይንቁን የነበሩትን እና ከእናንተ በላይ ነን የሚሉትንም ነፃ አውጥተን ለሀገራቸው አብቅተናቸዋል።
እኔ ምኞቴን ነግራችኋለሁ . . . እዚህ ወንበር ላይ ለመቆየት አይደለም ዕቅዴ፤ ለዚህ ህዝብ ነፃነት ማምጣት ከቻልን ድላችን ወደኋላ የማይመለስበት ደረጃ መድረሱን ካረጋገጥን ለመልቀቅ ደስተኞች ነን።
ከአሁን ወዲህ ተገቢውን የሕዝብ ድምጽ ሳያገኙ እዚህ ወንበር ላይ መቀመጥ አይቻልም።
ሶስት ሰዓት አንብቤ 30 ደቂቃ ድንቅ ንግግር ማድረግ ቀላል ነው . . .። መሥራት ነው የሚከብደው። ጥሮ ግሮ ትንሽም ሆን ትልቅ ውጤት ማምጣት ነው ከባዱ። ማውራትም ሺዎች አሳምረው ያወራሉ።
እኛ የተሰደደውን ብቻ ነፃ ማውጣት ሳይሆን ሀገሪቱንም ከመበተን አድነናታል፤ . . . እኛ ወደ ስልጣን ስንመጣ ብዙዎቹ አሳንሰው እንዳዩን ሳይሆን ከኦሮሞ ህዝብ የወጣን ቢሆንም ለመላው ኢትዮጵያ የምንተርፍ መሆናችንን አረጋግጠናል። በዳቦ ከሆነ ወደ ሥልጣን በመምጣታችን አንድ ዳቦ እንኳን ለኦሮሞ የጨመርነው የለም፣ ሀገራችን እንድትከበር ግን ማድረግ ችለናል። ክብር ደግሞ ከዳቦ ይበጣል። በቀጣይ ዳቦውን በላባችን ሠርተን እናገኘዋለን።
አሁን ተንሰንሰፍስፈው የሚያናግሩን እና በአጀብ አቀባበል የሚያደርጉልን የዓለም ሀገራት ከወራት በፊት በአማላጅ አንኳን ለማናገርም ተጠይፈውን እና እንቢ ብለውን ነበር፤ . . . በአንድነታችን ኦሮሞን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያንም ነው ያስከበርነው፤ በቀጣይም አፍሪካንም ጭምር ለማስከበር ነው የምንሰራው። አሁንም ህዝባችን ብዙ መከራ አለበት። ዋናው ሰንሰለት ግን ከላያችን ላይ መበጣጠስ ችለናል።
ዛሬም በሀሳብ ልዩነትን ተቻችለን አብረን ለህዝባችን መስራት የማንችል እና ልክ እንደ ትናንቱ በመሳሪያ የምንጫረስ ከሆን ምንም ያልተማርን መሀይሞች ነን ማለት ነው።
ወንበርን ሀብትን ለማፍሪያነት ፈልገነው የተቀመጥንበት ሲሆን ብቻ ነው ለመልቀቅ የምናንገራግረው . . . ለመቆየትም ስንል ሌላውን የምናጠፋው . . . ፍላጎታችን የሕዝባችንን ኑሮ ለመቀየር ከሆነ ግን ወንበር ላይ ውሎ ለማደር የምንጫረስበት ምክንያት አይኖርም።
በፌስቡክ “እከሌን ያስፈታነው እኛ ነን” ብለው የሚፎክሩ አሉ። ይፎክሩ ለህዝብ እስከጠቀመ ድረስ ይሁን ክሬዲቱን ለመውሰድ የሚሰጠው ሰርተፍኬቱ አያልቅም . . . ግን የዛሬ ሶስት ዓመት ለምን አላሰፈቱም? የዛሬ አራት አመትስ . . .? ዛሬም ሁሉ ነገር አልተፈታም፤. . . ብዙ ችግሮቻችን ገና በሂደት ላይ ናቸው። ግን በመደማመጥ መስራት አለብን . . . ነገም ተነስተን በገጀራ ምንጨፋጨፍ ከሆነ እና በዱላ ምንደባደብ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ በቅርብ ህዝባችንን መልሰን ወደ ባርነት እንመልሰዋለን ማለት ነው። በንግግር የምንስማማበት የመቻቻልና የአንድነት ዘመን ይሁን።”