የተቃውሞው ጎራ ለምን ደነገጠ? (What to do next?) /በፈቃዱ ዘ ኃይሉ/

የተቃውሞው ጎራ ለምን ደነገጠ? (What to do next?) /በፈቃዱ ዘ ኃይሉ/

ኦሕዴድ እና ብአዴን በሕወሓት የበላይነት ይመራ የነበረውን የኢሕአዴግ ፖለቲካ ከውስጥ መነቅነቅ ሲጀምሩ ተቃዋሚዎች ተደስተው ነበር። ኦሕዴድ በክልሉ አንፃራዊ የተቃውሞ-ነጻነት ሲፈቅድም እንዲሁ ተደስተዋል። ነገር ግን የዐብይ ጠቅላይ ሚኒስትርነት እና የተቃዋሚውን ቋንቋ መነጋገራቸው ድንጋጤ ፈጥሯል። ባጭሩ ተቃዋሚዎች ከኢሕአዴግ ጋር “መደራደር ይገባናል” ሲሏቸው የነበሩት ጉዳዮች – የፖለቲካ እስረኛ ማስፈታት እና አንዳንድ አዋጆችን ማሻሻል፣ በጥቅሉ የፖለቲካ ምኅዳሩን የማስፋት ጥያቄ እና ተቋማትን ከፖለቲካ ጥገኝነት ማላቀቅ – የመሳሰሉትን ነገሮች በራሳቸው በኢሕአዲጉ ሊቀ መንበር ሲቀነቀን፣ ተቃዋሚዎች አጀንዳ አጥተዋል። የድንጋጤያቸው ምንጭም ይኸው ይመስላል። በርግጥ የፖለቲካ ድርጅቶቹ ሲያልፉበት ከነበረው ፈታኝ ሁኔታ አንፃር በመዳከማቸው የፖለቲካ ለውጦችን እያዩ ከወቅቱ ጋር የሚሔድ ፖለቲካ መጫወት ቢያቅታቸው የሚገርም አይደለም።

የፖለቲካ ድርጅቶቹ “የአኩራፊዎች እና የጡረተኞች መሰብሰበቢያ” እየተባሉ ሲተቹ ከርመዋል። ምንም እንኳን ከላይ ያሉ ቢመስልም ውስጣቸው በብዛት ባዶ ነው። ለኢትዮጵያ (100 ሚሊዮን ሕዝብ) የሚመጥን የመምራት አቅም ያላቸው ሰዎች ስብስብ የላቸውም። በመገናኛ ብዙኃን በሚራገቡ አጀንዳዎች ላይ የመንግሥትን አቋም ካወቁ በኋላ ተቃራኒውን ይዘው ከመሟገት በላይ ርዕዮተ ዓለማዊ አቅጣጫ የሌላቸው ድርጅቶች ቀላል አይደሉም። አንዳንዶቹ ከላይ ያሉትን ታዋቂ ሊቀ መንበሮቻቸውን የሚተኩ አባላት እንኳን አላፈለቁም። ኢትዮጵያን መምራት የሚችሉ በርካቶች ድግሞ ወይ የፖለቲካውን ትኩሳት እየፈሩ አንገታቸውን ደፍተው ‘ዝምተኛ-ብዙኃን’ መሐል ተቀብረዋል፤ አልያም ተሰድደዋል። በዚህም ምክንያት ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶቹ የኢሕአዴግ የፖለቲካ አጨዋወት ሲቀየር፣ የራሳቸውን አጨዋወት በመቀየር ፈንታ ድንጋጤ ውስጥ መግባታቸውን የሚያሳብቁ ነገሮች ናቸው አሁን የሚታዩት። “እስረኛ የፈቱት ወደው ሳይሆን ተገደው ነው”፣ “ሰውዬው ኢሕአዴግ ናቸው፣ ኢሕአዴግ ከሚቀየር ግመል በመርፌ ቀዳዳ…”፣ “ጥቂት ሰዎች ተቀየሩ ማለት ነገሮች ተቀየሩ ማለት አይደለም”፣ “ይች ይቺ ተቃውሞ ለማስቆም የተፈጠረች የኢሕአዴግ ሴራ/ድራማ ናት”… እነዚህ ንግግሮች ለቀጣዩ የፖለቲካ ጫወታ ፋይዳቸው ምን እንደሆነ ሊገባኝ አይችልም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእያንዳንዱ ንግግራቸው እና ድርጊታቸው የብዙዎችን ቀልብ እየገዙ እና “አለቀለት” ለተባለው ኢሕአዴግም አዲስ ነፍስ እየዘሩበት ነው። ይህ የገባቸው ተቃዋሚዎች የማጥላላት እና የማጣጣል ትርክት ለመፍጠር እየተፍጨረጨሩ ነው። ይህ ፖለቲካዊ ኪሳራ ሊያስከትል ይችላል። የሴራ ፖለቲካዊ ትንተና እና ጫወታም መሬት ላይ ጠብ የሚያደርገው እንደሌለ ከበቂ በላይ ታይቷል። የብሽሽቅ ፖለቲካም ጉንጭ ከማልፋት በላይ ትርፍ የለውም። ሕዝብን “ተታልላችኋል” እያሉ መውቀሱም አግባብ አይደለም። ምክንያቱም ሕዝቡ የሚያየውን መዳኘት ይችላል።

ይልቁንም (በፖለቲካ ምኅዳሩ መጥበብ ምክንያት የተከተለው እና ሁለተኛው ደረጃ) “የማማረር ፖለቲካ” ተላቅቆ፣ ወደ አንደኛው ደረጃ ፖለቲካ ማለትም አማራጭን የማሳየት እና ሕዝባዊ መሠረት የመጣል ፖለቲካ መጫወት ያስፈልጋል። የፖለቲካ ምኅዳሩ ለይቶለት ሳይዘጋ በፊት ለእስር እና ስደት የተዳረጉት ፖለቲከኞች ጥያቄ ምንድን ነበር? የሕዝቦች ጥያቄ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ደኅንነት እንዴት ነው የሚጠበቀው? ድንቁርና እና ድህነትን እንዲሁም ኢፍትሓዊነትን ለመቀነስ አገራችን ምን ዓይነት የፖለቲካ ስርዓት መከተል አለባት? አሁን ሰዐቱ ይህንን የመመለስ ነው።

የፖለቲካ ድርጅቶች የሚሠሩት ሥራ በየአደባባዩ ሰልፍ ከመውጣት እና የተቃውሞ መግለጫዎችን ከማውጣት በላይ ነው። አብላጫ የምክር ቤት ወንበር አግኝተው መንግሥት ሲመሠርቱ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አማራጭ በመኖራቸው ብቻ የሚሠሯቸው ሥራዎችም ብዙ ናቸው። በዋነኝነት አማራጭ የአገር አመራር አቅጣጫ ማሥመር አለባቸው። አገሪቱ ወዴት ነው መሔድ ያለባት? እንዴት ነው ወደዚያ መሔድ የምትችለው? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችሉ የማኅበረ–ኢኮኖሚያዊ ፍልስፍናቸውን ለሕዝብ ማስተዋወቅ አለባቸው። ለዚህ ደግሞ ብቁ የሆኑ አመራሮችን መሰብሰብ እንዲሁም እየኮተኮቱ ማሳደግ አለባቸው። አለበለዚያ እንደሥማቸው ተቃዋሚ ብቻ ሆነው ይቀራሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ “ተፎካካሪ” የሚለውን መጠሪያ እንደአስታራቂ መርጠዋል። እኔ እስካሁን ያለውን ፖለቲካ የገዢ እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፖለቲካ ብለው እመርጣለሁ። ምክንያቱም ገዢው ፓርቲ አገር ለመምራት ወይም ሕዝብ ለማገልገል ሳይሆን ፈላጭ ቆራጭ ገዢ ለመሆን ነው ሲተጋ የኖረው። ተቃዋሚዎች ደግሞ የገዢውን አገዛዝ ሲቃወሙ እዚህ ደርሰናል። ኢሕአዴግ መቀ:የር እፈልጋለሁ ብሎ ጭላንጭል ሲያሳይ፣ የነገውን ለነገ ትተው ተቃዋሚቹም መቀየር አለባቸው። እውነተኛ አማራጭነታቸውን ለማሳየት አጋጣሚውን መጠቀም ይኖርባቸዋል። አለበለዚያ ነገ ኢሕአዴግ ስህተት እስኪሠራ ጠብቆ “ይኸው ይሄንኑ ፈርተን ነበር” ማለት አያዋጣም፤ በሥሙ ብዙ ነገር ለሚፈፀመው ሕዝብም የሚያተርፍለት ነገር የለም። ምንም እንኳን ወደፊትም የመሔድ ወይም ወደ ኋላ የመመለስ ዕድሉ ዕኩል ቢሆንም አሁን (በዚህ ቅፅበት) ከሞላ ጎደል ሰፊ የፖለቲካ ምኅዳር አለ። የፖለቲካ ምኅዳሩ ስፋት ወደኋላ እንዳይመለስ ሕጋዊ እና ተቋማዊ መሠረት አፍርቶ ለዘለቄታው ዋስትና እንዲያገኝ ከመሥራት ጎን ለጎን አማራጭ የፖለቲካ መፍትሔን ለሕዝብ ማስተዋወቅ ያስፈልጋል። ሕዝብ ውስጥ የሰረፀ ፖለቲካዊ የመፍትሔ ሐሳብ ካለ፣ አመንጪዎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች ባይኖሩም እንኳን የግዜ ጉዳይ ቢሆን ነው እንጂ ግቡን ይመታል።

አማራጭ የፖለቲካ ሐሳብ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ካሉ እኛም “ገዢ” እና “ተቃዋሚ” እያልን ከመፈረጅ እንገላገላለን። “ተፎካካሪ” ከሚለው እና የሥልጣን ሽሚያን ብቻ ከሚጠቁመው ቃልም ይልቅ “አማራጭ” የፖለቲካ ድርጅቶች የሚለውን እንጠቀማለን። አማራጭ የፖለቲካ ድርጅቶች ካሉ፣ የድርጅቶቹን ሥም ስንሰማ የገዢውን ሐሳብ በመቃወማቸው ሳይሆን፣ በአማራጭ ሐሳባቸው እናስታውሳለቸዋለን። ‘ምረጡን’ ብለው ሲመጡም እንደተቃዋሚ “ተቃውሟቸውን” ወይም እንደ ተፎካካሪ “ፉክክራቸውን” ሳይሆን አማራጭ ሐሳባቸውን እንመርጣለን።

Time to move on, and choose your place in the board.

LEAVE A REPLY